“እብዶች አይደለንም፤ ቀድመን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አንተኩስም” ፑቲን

ፑቲን እኛ አቅላችንን አልሳትንም፤ ኒውክሌር አንተኩስም ይላሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፑቲን እኛ አቅላችንን አልሳትንም፤ ኒውክሌር አንተኩስም ይላሉ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ በዚህ ዘመን አስጨናቂ የዓለም ሥጋት እንደሆነ አምነው፤ ነገር ግን መሣሪያውን ለመተኮስ ሩሲያ ቀዳሚ እንደማትሆን አረጋገጡ።

ፑቲን እንዳሉት ይህን መሣሪያ አገራቸው የምትጠቀመው ጥቃት ከተሰነዘረባት ራሷን ለመከላከል ብቻ ነው።

“እኛ እብዶች አይደለንም፤ ቀድመን የኒውክሌር መሣሪያ የምንተኩሰው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ፑቲን ይህን ያሉት በሩሲያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብት ካውንስል ስብሰባ ላይ ነው።

ፑቱን ከዚህ ሌላ የዩክሬን ጦርነት ለተራዘመ ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።

ይሁንና ምዕራባዊያኑ እንደሚያምኑት ፑቲን ጦርነቱን ሲጀምሩ በአንድ ጀንበር ድልን እንደሚጎናጸፉ አምነው ነበር።

ሩሲያ ስትራቴጂክ የኒውክሌር መሣሪያ ልትጠቀም ትችላለች የሚለው ስጋት ምዕራባዊያንን ሲያስጨንቅ የከረመ ጉዳይ ነው።

በተለይም ፑቲን ባላሰቡት መልኩ ምዕራብ አገራት ለዩክሬን ሁሉን ዓይነት የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ በገፍ ማቅረባቸውን ተከትሎ የዩክሬን ጦር በለስ እየቀናው መጥቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰኑ ከተሞችንም ከሩሲያ ማስመለስ ችሏል።

የሩሲያ ጦር በበኩሉ ያልጠበቀው ሽንፈት ገጥሞት ማፈግፈግ ጀምሯል።

ይህ ሁኔታ ፑቲንን አጣብቂኝ ውስጥ ከከተተ በትንሹ ታክቲካል ኒውክሌር መሣሪያ ሊጠቀሙና አዲስ ዓለም አቀፍ ቀውስ ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች ውስጥ ውስጡን ሲነገሩ ነበር።

ፑቲን ግን ትናንት ይህን አስተባብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ኒውክሌር የዓለም ስጋት ስለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለመው። የሚደበቅም አደለም” ያሉት ፑቲን ነገር ግን አገራቸው መሣሪያውን ለመሳብ "የመጀመርያ አትሆንም" ብለዋል።

ከሞስኮ በቪዲዮ በቀጥታ ስብሰባውን የተካፈሉት ፑቲን “እኛ እኮ አቅላችንን አልሳትንም፤ ኒውክሌርን እንደምላጭ እያወዛወዝን ዓለምን አናስፈራራም። ራሳችንን ለመከላከል ካልሆነ በፍጹም አናደርገውም” ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ፑቲን ይህን ካሉ በኋላ አገራቸው ከየትኛውም አገር በበለጠ እጅግ የተራቀቁ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች እንዳሏት ተናግረዋል።

አሜሪካንን በተመለከተም ኒውክሌር መሣሪያዎችን ከግዛቷ ውጭ ባሉ ስፍራዎች ትደብቃለች ሲሉ ከሰዋል።

“ታክቲካልም ሆነ ሌላ የኒውክሌር መሣሪያ ሰው አገር ውስጥ የለንም፤ አሜሪካ ግን በቱርክና በሌሎች አገሮች አኑራለች” ብለዋል፣ ፑቲን።

የዩክሬንን ጦርነት በተመለከተ ዘለግ ላለ ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል የተናገሩት ፑቲን ውጤቱ ግን ለሩሲያ ታላቅ ፋይዳ ያለው እንደሆነ አስምረውበታል።

አራቱን ክልሎች በመቆጣጠራቸውም የአዞቭ ባሕርን የሩሲያ አካል እንዲሆን አስችለናል ብለዋል።

አዞቭ ባሕር በደቡብ ምሥራቅ ዩክሬንና በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ የሚገኝ ባሕር ነው።

“ይህን ባሕር የሩሲያ አካል ማድረግ የታላቁ ቄሳር ፒተር ሕልም ነበር፤ ይህን አሳክተናል” ሲሉ ድሉን አሞካሽተዋል።

ፑቲን ራሳቸውን ከ17ኛውና 18ኛው ክፍለ ዘመን ቄሳር ታላቁ ፒተር ጋር ሲያወዳድሩ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም።

ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶች የነበሩትን አወዛጋቢዎቹን አራት ክልሎች ማለትም ኬርሶን፣ ዛፖሬዥያ፣ ሉሃንስክ እና ዶኔስክን የይስሙላ ሕዝበ ውሳኔ ካስደረጉ በኋላ ወደ ሩሲያ ጠቅልለዋቸዋል።

ይሁንና አሁን በነዚህ አራት ክልሎች ላይ ሩሲያ ሙሉ ቁጥጥር የላትም።

የሩሲያ ወታደሮች የዛሬ ወር ነበር ከኬርሶን ከተማ የሸሹት።

ኬርሶን ከጦርነቱ ወዲህ ብቸኛው በሩሲያ የተያዘ የዩክሬን ትልቅ ከተማ ነበር።

ኬርሶን ከተማ በዩክሬን ወታደሮች ቁጥጥር ሥር መግባቷን ተከትሎ ከፍተኛ ሽንፈት የደረሰበት የሩሲያ ሠራዊት በፍጥነት ከከተማዋ ወጥቷል።

ይህን መራር ሽንፈት ተከትሎ ሩሲያ ያደረሰችደው የበቀል ጥቃት የዩክሬንን የኃይል አቅርቦት ያሸመደመደ ነበር።

ዛሬም ድረስ በዩክሬን በርካታ ከተሞች ሚሊዮኖች ያለ ቤት ማሞቅያ መሣሪያ በውርጭ ለመቀመጥ ተገደዋል።

በተለይም የብርቱው ክረምት (ዊንተር) ወቅት መግባት በዩክሬን ሕይወትን ያለ ኃይል አቅርቦት ይበልጥ ከባድ አድርጎታል።

የቅዝቃዜ መጠኑ ከዜሮ በታች በሆነበት በዚህ ወቅት የመብራት፣ የሙቀት፣ የውሃ አቅርቦት ለሚሊዮን ዩክሬናዊያን እጅግ የሚናፈቅ ውድ ነገር ሆኖባቸዋል።

የኪየቭ ከንቲባ ቫይታሊ ክሊችኮ በከተማዋ የመሞቅያ ማዕከላት ለማቋቋም እየሠሩ እንደሆነ ተናግረው ነገር። ግን ሰዎች አማራጩ ካላቸው ወደ ሌሎች የተሻሉ አካባቢዎች እንዲሄዱ ጠይቀዋል።

ሩሲያ ስትራቴጂክና ታክቲካል የኒውክሌር መሣሪያ ልትጠቀም ትችላለች የሚለው ስጋት አሁንም ጨርሶ አልጠፋም።

ስትራቴጂክ ኒውክሌር መላ ከተማን ወደ ምንምነት የመቀየር ኃይል ያለው መሣሪያ ነው።

መጪ ትውልዶች ላይም ጠባሳው የሚታይ አጥፊና አውዳሚ መሣሪያ ነው።

ታክቲካል የሚባለው የኒውክሌር መሣሪያ ግን በጦር ሜዳ ላይ አገልግሎት ሊውል የሚችል፤ የጉዳት መጠኑም በዚያው ጥቃቱ ባረፈበት አካባቢ ብቻ የሚወሰን ነው።