እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት ሦስት ጋዜጠኞች ተገደሉ

በእስራኤል አየር ኃይል ጥቃት የደረሰበት ስፍራ

በደቡብ ምሥራቅ ሊባኖስ ጋዜጠኞች በሚገለገሉበት ሕንጻ ላይ የእስራኤል ጦር ባደረሰው የአየር ጥቃት ሦስት ሊባኖሳውያን ጋዜጠኞች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ገለፁ።

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በሀስባያ በሚገኝ የእንግዶች ማረፊያ ላይ ሲሆን፣ ቦታውን ቢያንስ የሰባት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች እንደሚጠቀሙበት ተገልጿል።

በግቢው ውስጥ ጋዜጠኛ መሆናቸው በግልጽ የተጻፈባቸው መኪኖችም ቆመው እንደሚገኙ በዘገባው ላይ ተመልክቷል።

ሦስቱ ጋዜጠኞች ለአል ማናር እና አል ማያዴን ቲቪ የሚሠሩ የነበረ ሲሆን፣ ተቋማቱም በባልደረቦቻቸው ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው መግለጫ አውጥተዋል።

የሊባኖስ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ መሆንን ጠቅሶ “የጦር ወንጀል” ሲል ኮንኖታል።

የእስራኤል ጦር በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ አስተያየት ባይሰጥም ከዚህ ቀደም ግን ጋዜጠኞችን ዒላማ እንደማያደርግ ገልጾ ያውቃል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስትር በበኩሉ በዚህ የአየር ጥቃት ሌሎች ሦስት ግለሰቦች መጎዳታቸውን አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት የሮይተርስ ባልደረባ የሆነው ኢሳም አብደላህን ጨምሮ አምስት ጋዜጠኞች መገደላቸው ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእንግዶች ማረፊያውን የሚጋራው አል ጃዲድ ቲቪ ያሠራጨው ተንቀሳቃሽ ምሥል አንደሚያሳየው በአየር ጥቃቱ ጉዳት የደረሰበት ቤት ጣራው የተደረመሰ ሲሆን፣ ወለሉም በፍርስራሽ ተሞልቷል።

ለቴሌቪዥነ ማሠራጫ የሚያገለግል መኪናም ተገልብጦ በአናቱ ላይ የተሰቀለው ሳተላይት ዲሽ ጉዳት ደርሶበታል።

“ሁሉም ባለሥልጣናት ይህ ቤት ጋዜጠኞች የሚቆዩበት መሆኑ ተነግሯቸዋል። ሁሉም ስለጉዳዩ እንዲያውቁ ተደርጓል” ሲል የአልጃዲድ ጋዜጠኛ በቀጥታ ሥርጭት ዘገባው ወቅት ተናግሯል።

በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ግጭቱን እየዘገቡ የሚገኙ የሊባኖስ ጋዜጠኞች ማርጆዮን የሚባለው ስፍራ ለደኅንነታቸው አስጊ በመሆኑ ወደ ሀስባያ ለመቀየር ተገድደዋል።

ዩኡማን ፋዋዝ የተባለች የኤምቲቪ ሊባኖስ ጋዜጠኛ በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በአየር ጥቃቱ ምክንያት መንቃታቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

አክላም “ጣሪያው ላያቸው ላይ ነው የተደረመሰው፤ ተዋጊ አውሮፕላን በላያችን ላይ እየበረረ በአቧራ እና ፍርስራሸ ተከብበን ነው የነቃነው” ብላለች።

እያንዳንዱ የዜና ተቋም በግቢው ውስጥ የራሱ የሆነ ቢሮ ያለው ሲሆን የአል ማያዲን ጋዜጠኞች በቢሯቸው ውስጥ እንዳሉ ወድሟል ስትል ምስክረነቷን ሰጥታለች።

ፋዋዝ ቦታው በእስራኤልም ሆነ በሄዝቦላህ የጋዜጠኞች ቢሮ የሚገኝበት መሆኑ ይታወቃል ስትል ተናግራለች።

“የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ይሁነኝ ተብሎ ነው። በግቢው ውስጥ ያሉት መኪኖች በሙሉ ፕሬስ እና ቲቪ የሚል መለያ በግልጽ ሰፍሮባቸዋል። ማስጠንቀቅያ እንኳ አልተሰጠንም።”

አክላም በጋዛ እንዳደረጉት ሊያሸብሩን ነው የሚፈልጉት። እስራኤሎች ስለ ጥቃቱ እንዳንዘግብ ለመከልከል ሲሉ ነው ይህንን ያደረጉት ብላለች።

የሊባኖስ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የእስራኤል መንግሥት ከዓለም አቀፉ ስምምነት በተቃራኒ ሆን ብሎ ጋዜጠኞችን ዒላማ አድርጓል ሲል ይከስሳል።

በእንግዳ ማረፍያው ከሰባት የመገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ 18 ጋዜጠኞች እንደሚሠሩ አክለው ተናግረዋል።

ይህ የእስራኤል አየር ኃይል ጥቃት የተሰማው መከላከያ ኃይሉ በሰሜን ጋዛ የሚሰሩ ስድስት የአል ጃዚራ ጋዜጠኞች ከሐማስ አልያም ከሌላ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ በወነጀላቸው በቀናት ልዩነት ውስጥ ነው።

አል ጃዚራ በበኩሉ ውንጀላውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎ አጣጥሎታል።

ለጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 123 ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች በጋዛ መገደላቸውን አስታውቋል።

በጋዛ በሐማስ የሚመራው ጤና ሚኒስትር በበኩሉ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ አንስቶ 42,000 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

እስራኤል በጋዛ በምታካሄደው ውጊያ የተገደሉት እስራኤላውያን ጋዜጠኞች ቁጥር ሁለት ብቻ ነው።

የእስራኤል አየር ኃይል የጋዜጠኞች መሰብሰብያ የሆነውን ስፍራ ካወደመ በኋላ