ሊባኖስ፡ “የልጅ ልጆቼን በእስራኤል ጥቃት አጣኋቸው፤ ለምንድነው ዓለም ይህ እንዲሆን የሚፈቅደው?”

የ74 ዓመቱ ፉአድ ሐሰን

የፎቶው ባለመብት, Aakriti Thapar / BBC News

ባለፈው ሰኞ ምሽት የአየር ጥቃት ሲፈጸም የ74 ዓመቱ ፉአድ ሐሰን ደቡባዊ ቤይሩት ጅናህ መንደር ከሚገኘው ቤቱ በረንዳ ላይ ተቀምጦ ነበር።

የእስራኤል ጦር ጥቃት ሊደርስ ነውና አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ የሚል ማስጠንቀቂያ አልሰጠችም። የተተኮሰው ሮኬት ከመሬት ሲላተም ልጆቹ እና የልጅ ልጆቹ በቅርብ ርቀት ላይ ነበሩ።

“ቦምቡ ሲወድቅ እኔም ራሴን ስቼ ወደቅኩ” ይላሉ ፉአድ።

“ጭሱ በጣም ብዙ ስለነበር አፈነኝ። ኦክሲጅን እንድወስድ ተደርግኩ። ሲሻለኝ እና ነቃ ስል መንደሩ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተመለክትኩ።”

በጣም በርካታ መኖሪያ ቤቶች ከጥቅም ውጪ ሆነው የፍርድሳሽ እና የብረት ቁልል ተከምሯል። በከፊል የተጎዱ ሕንፃቸው እርቃናቸውን ሆነው መኖሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ዕቃዎች ከውጭ ይታዩ ነበር።

የአካካቢው ማኅበረሰብ ተሰባስቦ ፍርስራሽ ውስጥ በነብስ ያሉ ሰዎችን ይኖሩ እንደሁ ፍለጋ ጀመሩ።

“እየው እስቲ የሆነውን? አንድ መንደር ሙሉ ነው የወደመው፤ ነዋሪዎች ሞተዋል” ይላል ፉአድ። “የልጅ ልጄ ሞታለች። ሌላኛው የልጅ ልጄ ደግሞ አሁንም ‘ኮማ’ ውስጥ ነው። ሁለቱ ዕድሜያቸው 23 ነው።”

ፉአድ በአካባቢው ሰው ዘንድ ትልቅ ስም አለው። ኮሜዲያን እና ተዋናይ ነው። በሊባኖስ ቴሌቪዥኖች ቀርቦ ብዙዎች አይተውታል። ፉአድ የሕንፃዎች ፍርስራሽ ላይ ሲራመድ የአካባቢው ሰው እየመጣ እጁን እየሳመ ሐዘኑን ይገልጽለታል።

ፉአድ ስልኩን ከኪሱ አውጥቶ የልጅ ልጁ አላን ፎቶ ተመለከተ። ወርቅማ ጥለት ያለው ነጭ ልብስ ለብሳ ፎቶው ላይ የምትታየው አላ በሦስት ወራት ውስጥ ትዳር ልትመሠርት ታጭታ ነበር።

“የሊባኖስ የቁንጅና ውድድር ልትወዳደር ተመዝግባ ነበር። አሁን ግን ይኸው ሰውነቷ ተበሳስቶ ሞተችብኝ። ለምን? ለምንድነው ዓለም ይህ እንዲሆን የሚፈቅደው?”

የፉአድ የልጅ ልጅ አላ

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, አላ በአየር ጥቃቱ ከተገደሉ የፉአድ የልጅ ልጆች አንዷ ናት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል ካለፈው መስከረም ጀምሮ በሄዝቦላህ ላይ የምትወስደውን እርምጃ አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ ለሊባኖሳውያን የአየር ጥቃት የዕለተ ዕለተ ኑሯቸው ከሆነ ሰነባብቷል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት በዚህ ጦርነት ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራሮችን መግደላቸውን እንደ ትልቅ ድል ያዩታል። ነገር ግን በጦርነቱ ሳቢያ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በሊባኖስ ጦርነት በእስራኤል አየር ድብደባ ብቻ ከ1900 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ይገልፃሉ። ምን ያክሉ ሰላማዊ ዜጎቹ የትኞቹስ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ናቸው የሚለው ግልፅ አይደለም።

ሰኞ ምሽት የእስራኤል ጦር ኃይል ያለ ማስጠንቀቂያ የአየር ድብደባ ከፈጸመ በኋላ ዒላማ ያደረገው “የሄዝቦላህ አሸባሪዎችን ነው” ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ አላቀረበም።

መጀመሪያ የወጡ ዘገባዎች በዋና ከተማዋ የሚገኘው ራፊክ ሀሪሪ የተባለው ግዙፉ ሆስፒታል እንደተመታ ጠቁመው ነበር። እስራኤል ግን ይህ አስተባብላለች።

ሆስፒታሉ ላይ የደረሰው ጉዳት ይህን ያህል ባይሆንም መንገድ ተሻግሮ የሚገኘው መንደር ግን ክፉኛ ተጎድቷል።

የፉአድ ልጅ አሕመድ ወደ ፍርስራሹ መጣ። የአሕመድ ልጅ በአየር ድብደባው ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ተኝቷል። ደም የሞላው ፊቱ በፋሻ ተጠቅልሏል።

አሕመድ ስልኩን አውጥቶ “ይሄ ቤቴ ነበር። አሁን ግን የለም። የምንጠለልበት፣ የምንለብሰው የለንም። ይህ ጅምላ ግድያ ነው። ይሄ ወታደራዊ ሠፈር አይደለም፤ ሄዝቦላህም የለም። ምንም የለም” ሲል በምሬት ተናገረ።

ፉአድ ወደ ሰፈሩ ሲመጣ የአካባቢው ሕፃናት አጅበው ይቀበሉት ነበር።

“እየሮጡ መጥተው 'አባባ፤ አባባ' ይሉኝ ነበር። 'ምን ይዘህልን መጣህ?' ሲሉኝ ከረሜላም፣ ፈንዲሻም እሰጣቸዋለሁ። አሁን ሁሉም ሞተዋል። እነሱን ማጣቴ ልቤን በሐዘን ሰብሮታል። እናታቸው አሁንም ፍርስራሽ ውስጥ ናት።”