የሐማስ መሪዎች ከተገደሉ በኋላ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የማይደረገው ለምንድነው?

ጦርነት ይቁም የሚል ፅሑፍ መዳፏ ላይ ያሰፈረች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ አንዳንዶች ጦርነቱ እንዲቆም ጠይቀዋል

የሐማሱ መሪ ያህያ ሲንዋር ከተገደሉ በኋላ መግለጫ የሰጡት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የጋዛው ጦርነት ገና “አልተቋጨም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ብዙዎች የሲንዋር መገደል የጋዛው ጦርነት እንዲጠናቀቅ ምክንያት ይሆናል የሚል ግምት ነበራቸው። የኔታኒያሁ ንግግር ግን ይህንን ተስፋ ያጨለመ ነው።

የዩናይት ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የምዕራባዊያን አገራት መሪዎች የሲንዋር መሞት ለጦርነቱ መቋጨት ምክንያት ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።

ነገር ግን በርካታ ታዛቢዎች የጋዛው ጦርነት በሰላም ስምምነት የመጠናቀቁ ነገር ተስፋ ያለው አይመስልም ይላሉ። እስራኤልም ሆነች ሐማስ ለሰላም ስምምነት እጃቸውን የሚዘረጉ አይመስሉም።

እስራኤል የሲንዋር መገደልን ካረጋገጠች ከሰዓታት በኋላ ነው ኔታኒያሁ “ትልቅ እርምጃ” ብለው፤ ነገር ግን ጦርነቱ እንደሚቀጥል የተናገሩት።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ጦርነቱ እየተባባሰ ሄዷል። በጋዛ ከሐማስ ጋር የሚደረገው ጦርነት የተፋፋመ ሲሆን፣ በወረራ ሥር በምትገኘው ዌስት ባንክ እና ደቡባዊ ሊባኖስም የአየር ድብደባዎች እንደቀጠሉ ናቸው።

በተያያዘ የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። የሄዝቦላህ እና የሐማስ ደጋፊ የሆነችው ኢራን የሲንዋር ግድያ “የትግሉን መንፈስ ያነቃቃዋል” ትላለች።

በሐማስ የተያዙ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሐማስ የተያዙ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፈኞች

የመስከረም 26 ጥቃት አቀነባባሪ

ሲንዋር በእስራኤል ከሚፈለጉ ሰዎች መካከል ቁንጮው ነበር። ሐማስ እስራኤል ላይ የፈጸመው ጥቃት አቀነባባሪ እንደሆነም ይነገርለታል። ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎችን ገድሎ 251 አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል።

በለንደን የኢኮኖሚክስ እና ፖለቲካ ሳይንስ ኮሌጅ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት ፋዋዝ ገርግስ በቅርቡ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረጋል የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰሩ አክለው “ኔታኒያሁ የሲንዋርን ግድያ ካበሰሩ በኋላ ጦርነቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ምክንያቱም ዓላማቸውን አላሳኩም። እንደ ኔታኒያሁ ከሆነ ድል የሚመጣው ታጋቾችን በማስመለስ እና ሐማስን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ነው” ይላሉ።

በኢራን ዋና መዲና ቴህራን በሚገኘው የፍልስጤም አደባባይ የተሰቀለው የሲንዋር ቢልቦርድ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በኢራን ዋና መዲና ቴህራን በሚገኘው የፍልስጤም አደባባይ የተሰቀለው የሲንዋር ምሥል

“የጋዛው ጦርነት አልተቋጨም”

በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው የቪድዮ መልዕክት ያስተላለፉት ኔታኒያሁ “ሲንዋር ሞቷል። ምንም እንኳ ይህ በጋዛ ያለው ጦርነት መቋጫ ባይሆንም የመጨረሻው መጀመሪያው ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሮፌሰር ገርግስ እንደሚሉት “ኔታኒያሁ ማለት የፈለጉት ጦርነቱ የሚያቆመው ሐማስ ትጥቁን ሲፈታ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን የበለጠ እንዲታገል ምክንያት ሊሆን ይችላል።”

ኢስራኤሊ ስትራቴጂክ ሴንተር በተባለው ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ኤዲ ኮኸን በጋዛ ስላለው ጦርነት የተለየ አመለካከት ነው ያላቸው። እሳቸው እንደሚሉት ኔታኒያሁ በጋዛ ያሉ ታጋቾችን ከማስለቀቅ ያለፈ ዓላማ ነው ያላቸው።

ኔታኒያሁ እንደሚሉት አንዱ ዓላማቸው “ሐማስ በፍፁም ጋዛን እንዳያስተዳድር ከማድረግ ባለፈ ሌላ የትኛውም አካል ጋዛን እንዳይቆጣጠር ማድረግ” ነው።

ኮኸን ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቋጭ ብቸኛው መንገድ ሐማስም ሆነ ሌላ የሲንዋር ተተኪ በጋዛ ዕጣ ፈንታ ላይ እንዳይወስን ማድረግ ነው ብለው ያምናሉ።

ተመራማሪው አክለውም የጋዛ ሰርጥ ድንበር በቁጥጥር ሥር ከሆነ በድንበር በኩል የሚገቡ ሕገ-ወጥ መሣሪያዎችን ማገድ ይቻላል።

ያህያ ሲንዋር በአውሮፓውያኑ 2021 በጋዛ ከተማ በተካሄደ የፀረ-እስራኤል ሰልፍ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ያህያ ሲንዋር በአውሮፓውያኑ 2021 በጋዛ ከተማ በተካሄደ የፀረ-እስራኤል ሰልፍ ላይ

ገርግስ የእስራኤሉ መሪ ኔታኒያሁ በየፊናው ጦርነት ከፍተዋል ይላሉ። በጋዛ ያለውን ጦርነት ጨምሮ፣ በዌስት ባንክ፣ እንዲሁ በሊባኖስ እያካሄዱ ያሉትን ወረራ ያነሳሉ።

“አልፎም ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ወደ ጦርነት እንዲሳቡ እያደረጉ ይገኛሉ” ይላሉ።

ኔታኒያሁ ከሲንዋር ግድያ በኋላ በሰጡት መግለጫ “ይህን የሰይጣን ጥምረት አስቁመን የተሻለ ወደፊት ለመፍጠር ትልቅ ዕድል አለን” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የወረፉት ጥምረት በኢራን የሚደገፉትን በጋዛ፣ በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በኢራቅ እና በየመን ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን ነው።

የሲንዋር ግድያ እና የጋዛ ታጋቾች

ኮኸን የተኩስ አቁም ድርድር እንዳይደረግ ምክንያት የሆኑት ያህያ ሲንዋር ናቸው የሚል እምነት አላቸው። በጋዛ ያሉ ታጋቾች ጉዳይም በሲንዋር ምክንያት ተረስቶ ቆይቷል ይላሉ።

“እስራኤል በጋዛ ሌላ ዓላማ የላትም። ነገር ግን በጋዛ ያሉ ታጎቾችን ማስለቀቅ እንሻለን” የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የሲንዋር ግድያ በቀጣይ ወራት በሚደረጉ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል።

ኮኸን ሁኔታዎች “ቀስ በቀስ ይሻሻላሉ” የሚል ተስፋ ያላቸው ሲሆን፣ በቅርቡ የታጋቾች ጉዳይ መልስ ያገኛል ሲሉም ይገምታሉ።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ሐማስ መደምሰስ አለበት ይላሉ

ኔታኒያሁ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2023 ኤንቢሲ ለተባለው የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ “ሰላም ከፈለግን ሐማስን ማጥፋት አለብን” ሲሉ ተናግረው ነበር።

“ፀጥታ ከፈለግን ሐማስን ማጥፋት አለብን። ለእስራኤል፣ ለፍልስጤም፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ መፃዒ ዕጣ ፈንታ ስንል ሐማስን ማጥፋት አለብን።”

ኔታኒያሁ በሐማስ ሥር ያሉ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል። ነገር ግን የአንዳንድ የታጋቾች ቤተሰቦች የኔታኒያሁን ንግግር አያምኑበትም።

የተኩስ አቁም ድርድር

ገርግስ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የመካከለኛው ምሥራቅን ፖለቲካዊ ምኅዳር አዲስ ቅርፅ ማስያዝ ይፈልጋሉ ብለው ያምናሉ። ለዚህ ነው ሲንዋር ተገድለው እንኳ ኔታኒያሁ ስለተኩስ አቁም ማውራት አይፈልጉም የሚሉት።

እሳቸው እንደሚተነትኑት ኔታኒያሁ ሐማስን ከመርታት እንዲሁም በዌስት ባንክ ያሉ አጋሮችን ከማጥፋት እና ሄዝቦላህን ድል ከመንሳት ባለፈ ኢራንን መጋፈጥ ይፈልጋሉ።

ያህያ ሲንዋር በሐማስ እና በእስራኤል ጦር መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ነበሩ ተብለው ይታማሉ።

ነገር ግን የእሳቸው መገደል በጋዛ እና በሌሎች የቀጣናው ክፍሎች ያለውን ጦርነት ጋብ አላደረገውም።