በጎላን ተራራማ አካባቢ ምን የተለየ ነገር አለ? እስራኤል ቦታውን ለምን ትፈልገዋለች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል ኃይሎች በጎላን ተራራማ አካባቢ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆኑ አካባቢዎችን ጨምሮ ሌሎችንም የሶሪያ ግዛቶችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአገሪቱን መከላከያ ኃይል ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ወደሆኑ አካባቢዎች እና "በአቅራቢያ ወደሚገኙ መቆጣጠሪያ ቦታዎች" እንዲገባ ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።
ይህም ውሳኔ ጊዜያዊ እንደሆነ እና እስራኤልን ከሶሪያ አማጺያን ጥቃት ለመጠበቅ በሚል መሆኑን ተናግረዋል።
የሶሪያ አማጺያን ፕሬዝዳንት በሻር አል-አሳድን ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ ነው እስራኤል እነዚህን አካባቢዎች የተቆጣጠረችው።
በርካታ የአረብ አገራት ድርጊቱን ኮንነዋል።
ጎላን ተራራማ አካባቢ የሚገኘው ከሶሪያ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ነው። የእስራኤልን ግዛት በሰሜን ምሥራቅ ያዋስናል።
በእስራኤል ወታደሮች ቁጥጥር ሥር ይገኛል።

እአአ በ1967 በስድስት ቀናት ጦርነት እስራኤል በሶሪያ ኃይሎች ከዚህ ተራራማ አካባቢ ጥቃት ተፈጽሞባታል።
እስራኤል በመልሶ ማጥቃት ወደ 1,200 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆን ቦታ በቁጥጥሯ ሥር አስገብታለች።
በአውሮፓውያኑ 1973 በተደረገው 'ዮም ኪፑር' ጦርነት ሶሪያ ግዛቱን መልሳ ከእስራኤል ለመውሰድ ሞክራ አልተሳካላትም።
በ1974 ሶሪያ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል።
ሁለቱም አገራት ወደ የግዛታቸው 80 ኪሎ ሜትር ርቀው እንዲገቡ ስምምነቱ ያስገድዳል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቦታውን የሚቃኝ ኃይል አሰማርቷል።
በ1981 እስራኤል የጎላን ተራራማ አካባቢን ጠቅልላ በግዛቷ ውስጥ አካተተች። ሰፋሪዎች በቦታው ቤት መሥራት ጀመሩ።
ነገር ግን ይዞታው የእስራኤል መሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና አልሰጠም። ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ግን በ2019 ይዞታው የእስራኤል መሆኑን ተናግረዋል።
እስራኤል ከአጠቃላይ ጎላን አካባቢ ለቃ ካልወጣች የሰላም ስምምነት እንደማይኖር ሶሪያ አስታውቃለች።
እአአ ኅዳር 2024 ላይ እስራኤል ከሶሪያ ጋር የሚለያትን አካባቢ በማለፍ ግንባታ እያደረገች ነው የሚል ቅሬታ በሶሪያ እና በተባበሩት መንግሥታት ቀርቦባታል።
አካባቢው ለምን አስፈላጊ ሆነ?
ሶሪያ የጎላን ተራራማ አካባቢዎችን ከ1948 እስከ 1967 በምትቆጣጠርበት ወቅት በሰሜናዊ እስራኤል አቅራቢያ ጥቃት ለማድረስ ያላት ቁልፍ ቦታ ነበር።
ከእስራኤል አንጻር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት የሶሪያ መዲና ደማስቆን መመልከት የሚቻለው ከጎላን ተራራዎች ነው።
የሶሪያን ወታደሮች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርም ትጠቀምበታለች።
ሶሪያ በ1973 ጦርነት እንዳደረገችው እስራኤል ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም መከላከል የምትችልበት ሥፍራ አድርጋ እየተጠቀመችበት ነው።
አካባቢው ውሃ የሚገኝበት ቁልፍ ቦታም ነው።
ውሃ ውድ በሆነበት በመካከለኛው ምሥራቅ በጎላን ተራራ የሚገኘው የዝናብ ውሃ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ይገባል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አካባቢው ለም የሆነው፣ እንስሳትም የሚጠጡት ውሃ የሚያገኙት ከዚሁ አካባቢ ነው።
እስራኤል ከ1967 በፊት ወደነበረው ይዞታዋ ትመለስ የሚለው የሶሪያ ጥያቄ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም እንዳይወርድ ምክንያት ሆኗል።
ይህ ከሆነ ሶሪያ በገሊላ ባሕር ምሥራቃዊ ዳርቻ ይዞታ ይኖታል። እስራኤልም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ምንጭ ታጣለች።
ይህን ባሕር እስራኤላውያን ኪናሬት ሲሉት አረቦች ቲቤሪየስ ይሉታል።
እስራኤል ድንበሩ ወደ ምሥራቅ እንዲገፋ ትሻለች።
እስራኤላውያን አገራቸው የጎላን ተራራማ አካባቢን ይዛ እንድትቆይ ይፈልጋሉ።
በቦታው ማን ይኖራል?
በ1967 ጦርነት አረብ ሶሪያውያን የጎላን ተራራማ ሥፍራ ነዋሪዎች ከቦታው ሸሽተዋል።
አሁን በአካባቢው ከ30 በላይ የእስራኤል ሰፋሪ ይዞታዎች ይገኛሉ።
20 ሺህ ነዋሪዎች እንዳሉ ይገመታል።
ከ1967 ጦርነት በኋላ እስራኤል በአካባቢው ግንባታ ጀምራለች።
ሰፈራው በዓለም አቀፍ መርህ ሕገ ወጥ ነው።
ሰፋሪዎቹ የሚኖሩት ወደ 20 ሺህ ሶሪያውያን ከሚኖሩበት አቅራቢያ ነው።
ከሶሪያውያኑ አብዛኞቹ የድሩዝ ጎሳ አባላት ናቸው። ጎላንን እስራኤል ስትቆጣጠር ቦታውን ጥለው አልወጡም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል በጎላን ተራራማ አካባቢ ምን ትሠራለች?
የሶሪያ ወታደሮች ከጎላን ተራራማ አካባቢዎች መውጣታቸውን ተከትሎ እስራኤል ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነውን አካባቢ በቁጥጥር ሥር አውላለች።
"ዘላቂ አካሄድ እስከምንዘረጋ በጊዜያዊነት ቦታውን እንደ መከላከያ ሥፍራ ኃይላችን ይይዘዋል" ብለዋል ኔታንያሁ።
"በሶሪያ ካለው አዲስ ኃይል ጋር ሰላም ማውረድ እና የጉርብትና ወዳጅነት መመሥረት ነው ፍላጎታችን። ይህ ካልሆነ ግን እስራኤል እና ድንበሯን ለማስጠበቅ ማንኛውንም እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል።
በሶሪያ በኩል የወጡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት እስራኤል በደማስቆ እስከ 25 ኪሎ ሜትር ዘልቃ ገብታለች።
እስራኤል ግን ያን ያህል ርቀት ኃይሏ አለመጓዙን ትናገራለች።
የአረብ አገራት እስራኤልን እየወቀሱ ነው።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "የሶሪያን ግዛት በቁጥጥር ሥር ማዋል ነው። ይህም የ1974 ስምምነትን ይጥሳል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ግን በሶሪያ ያለው መንግሥት ስለወደቀ በ1974 የተደረሰው ስምምነት አሳሪ አይደለም ትላለች።
በለንደን ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ጊልበርት አካር "እስራኤል የጥቅምት 7 ዓይነት ጥቃት በሶሪያ በኩል እንዳይከሰት ለመከላከል ነው ትላለች። በይዞታ ሥር ባለው ድንበር በኩል ሌላ ኃይል እንዳይጠጋ ለማስቆም ነው ዕድሉን የተጠቀመችው" ይላሉ።
እስራኤል ወደ ሶሪያ ግዛት መግባቷ ለወደፊት በሶሪያ ከሚኖረው መንግሥት ጋር ወዳጅነት ለመፍጠር እንደሚያስቸግርና "እስራኤል የከፋ ቀን ቢመጣ በሚል ዕሳቤ ነው የምትንቀሳቀሰው። ይሄም አፍራሽ ነው" በሚል እንድትታይ እንደሚያደርግ ያክላሉ።
ብዙ ተንታኞች የእስራኤልን ማብራሪያ አሳማኝ አድርገው አልተቀበሉትም።
ለንደን ባለው የተንታኞች ስብስብ 'ቻተም ሐውስ' የሚሠሩት ፕሮፌሰር ዮሲ ሜክልበርግ "ሶሪያ በስምምነቱ አልገዛም አላለችም። እስራኤል ደኅንነቷን ለማስጠበቅ የወሰደችው ቅድመ ጥንቃቄ ነው። ግን ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ምንም አሳማኝ ምክንያት የለም" ይላሉ።
ለንደን ባለው ሌላ ስብስብ 'ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት' የሚሠሩት ዶ/ር ሀይ ሄይለር "የሶሪያ አማጺያን የጎላን ተራራማ አካባቢዎችን መልሰው የመውሰድ ዕድላቸው ጠባብ ነው። በአገር ውስጥ ጉዳይ ይጠመዳሉ። ከእስራኤል ጋር አዲስ ግጭት ውስጥ መግባትንም አያስቡም" ይላሉ።















