የሶሪያ ታጣቂዎች ደማስቆ መግባታቸውን ተከትሎ እስራኤል የጎላን ተራራ አካባቢዎችን ወረረች

የጎላን ተራራዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የሶሪያ አማጺያን እና የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ከእስራኤል ጋር የሚዋሰኑባቸውን አካባቢዎች መልቀቃቸውን ተከትሎ እስራኤል ከወታደራዊ ቀጠና ነጻ የነበሩ የጎላን ተራራ አካባቢዎችን ወራለች።

በጎላን ተራራዎች አካባቢ ከወታደራዊ ቀጠና ውጭ የሆኑ አካባቢዎችን "በጊዜያዊነት መያዟን" የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር አስታውቀዋል።

"አማጺያኑ የአገሪቱን ዋና ከተማ ደማስቆ ሲቆጣጠሩ በ1974 (እአአ) የተፈረመው ግጭትን የማቆም ስምምነት ፈርሷል" ብለዋል የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።

ይህንን ተከትሎም ወታደሮቻቸው ወደ ጎላን ተራራ ከወታደራዊ ቀጠና ነጻ ወደነበሩ ይዞታዎች ዘልቆ በመግባት "እንዲቆጣጠር" ማዘዛቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ገልጸዋል።

"በድንበራችን አቅራቢያ ማንኛውም ስጋት የሚፈጥር ኃይል እንዲደራጅ አንፈቅድም" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ የጦርነት ሁኔታዎችን የሚቃኝ ተቋም ለቢቢሲ እንደገለጸው ከሆነ፣ የሶሪያ ወታደሮች ወታደራዊ ነጻ ቀጠና የሚገኝባትን ቁኔጥራ የምትባለውን ግዛት ጥለው የወጡት ቅዳሜ ፣ ህዳር 28/ 2017 ዓ.ም ነው።

በማግስቱ እሁድ የእስራኤል መከላከያ አምስት የሶሪያ ሰፈር ነዋሪዎችን ተጨማሪ ትዕዛዝ እስኪሰጣቸው ድረስ ከቤት እንዳይወጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የጎላን ተራራ ከሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አለታማ ስፍራ ነው።

ይህንን አካባቢ እስራኤል የተቆጣጠረችው በ1967 በተደረገው የስድስት ቀን ጦርነት መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ1981 ወዲህ ደግሞ በብቸኝነት ተቆጣጥራዋለች።

ቀሪው ዓለም ይህንን የእስራኤል ግዛት ማጠቃለል እውቅና አልሰጠውም። በአንጻሩ አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2019 እውቅና ሰጥታዋለች።

አሁን የሶሪያ አማጺያን የበሻር አል አሳድን መንግሥት ገልብጠው መዲናዋ ደማስቆን ሲቆጣጠሩ እስራኤል ከወታደራዊ ቀጠና ነጻ የሆነውን አካባቢ ወራለች።

በሻር አል አሳድ እና አባታቸው ከአውሮፓውያኑ 1971 ጀምሮ ሶሪያን መርተዋል።

ሃያት ጣሂር አል-ሻም የተባለው እስላማዊ የተቃዋሚ ቡድን የአል አሳድን ስርዓት አሸንፎ እሁድ ህዳር 29/ 2017 ዓ.ም ወደ ዋና ከተማዋ ደማስቆ በመግባት ሶሪያ ነጻ መውጣቷን አውጇል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወታደሮቻቸው ወደ ሶሪያ ዘልቀው በመግባት የወታደራዊ ነጻ ቀጠና እንዲወሩ ትዕዛዝ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ፣ የበሻር አል አሳድን ስርዓት መውደቅ "ለመካከለኛው ምስራቅ ታሪካዊ ቀን" ብለውታል።

"የደማስቆው አምባገነን ሥርዓት መገርሰስ ትልቅ ዕድል ያመጣል፤ ግን ደግሞ የሚጠበቅ አደጋም አለው" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በማብራሪያቸው እሰራኤል የአሳድ ዋነኛ አጋር የሆኑትን ሄዝቦላህ እና ኢራንን በማጥቃቷ ስርዓቱ እንዲወድቅ ትልቅ ሚና መጫወቷን ገልጸዋል። በዚህም ከእስራኤል ጋር በሰላም መኖር ለሚፈልጉ ሶሪያውያን የሰላም መልክት ልከናል ብለዋል።

አሁን ሶሪያ ውስጥ ዘልቀው የተቆጣጠሩት አካባቢ በጊዜያዊነት የተያዘ እና በሶሪያ የመንግሥት ሥርዓት እስኪዘረጋ የሚቆይ መሆኑን ገልጸዋል።

"በሶሪያ አዲስ ከመጣው ኃይል ጋር ተስማምተን ሰላማዊ ጉርብትና መፍጠር ፍላጎታችን ነው። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን እስራኤልን እና የእስራኤልን ዳር ድንበር ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" በማለት ለአዲሱ የሶሪያ ኃይል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለአንድ ዓመት ያህል ጦርነት ውስጥ የነበረችው እስራኤል በቂ የጦር ግንባሮች ተፈጥረውላታል። ነገር ግን በሰሜን በኩል የምትጎራበታት ሶሪያ ሁኔታም ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። መከላከያ ሰራዊቷ ቀድሞ ወደ ጎላን ተራራዎች ገብቶ ወሯል።

እስራኤል በተለይ በሻር አል አሳድ አከማችተውታል የሚባለው የኬሚካል መሣሪያ በማን እጅ ሊወድቅ ይችላል የሚለው በእጅጉ ያሳስባታል።

የሶሪያ አማጺያን መሪ አቡ ሞሃመድ አል- ጃውላኒ ናቸው። የቤተሰቦቻቸው የዘር ሃረግ በእስራኤል ቁጥጥር ከሚገኘው የጎላን ተራሮች የሚመዘዝ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ከ20 ሺህ ሶሪያውያን ጋር ተቀላቅለው ይኖሩበታል።

እስራኤል ያንን አካባቢ የመስጠት ፍላጎት የላትም። ይልቁንም በዚያ የሰፈሩ ዜጎቿን መጠበቅ ትፈልጋለች። በአውሮፓውያኑ 2011 የሦሪያ አመጽ ሲፋፋም ምንም እንኳን በሻር አል አሳድ ከጠላቶቿ ሄዝቦላህ እና ኢራን ጋር ወዳጅ ቢሆኑም ከእርሳቸው በኋላ ከሚመጣው ስርዓት ይልቅ አሳድ ይሻሉኛል የሚል ስሌት ነበራት።

አሁን ደግሞ በሶሪያ ምን ሊመጣ ይችላል የሚለውን ታሰላለች። የሚሆነውን በግልጽ ማወቅ አይቻልም፤ እንደሌላው ተመልካች ሁሉ ስሌቷን ልትሰራ የምትችለው በግምት ብቻ ነው።