የቶኪዮ ነዋሪዎች ኃይል ለመቆጠብ ሲባል ‘አንገተ ሙሉ’ ሹራብ እንዲለብሱ ተጠየቁ

አንገተ ሙሉ ሹራብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቶኪዮ አገረ ገዢ ዩሪኮ ኮይኪ፣ በመጪው የአገሪቱ የክረምት ወቅት የኃይል ፍጆታን ለመቆጠብ ሲባል የከተማዋ ነዋሪዎች ‘አንገተ ሙሉ’ ሹራብ እንዲለብሱ አሳሰቡ።

ሙሉ አንገትን የሚሸፍኑ ሙቀት ሰጪ ልብሶች እየናረ የመጣውን የኃይል አቅርቦት ወጪ ለመቆጠብ እንደሚረዱ ባለሥልጣኗ ገልጸዋል።

የቶኪዮ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች ለነዋሪዎች ትምህርት ምሳሌ ለመሆን አንገተ ሙሉ ሹራቦችን መልበስ ይጀምራሉ።

የኃይል አቅርቦት ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረባት የጃፓኗ መዲና፣ በመጪው ክረምት ኃይል ለመቆጠብ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።

የኃይል ፍጆታን እንዴት መቀነስ እንደሚቻል ለነዋሪዎች መመሪያ እየተሰጠም ነው።

ውሳኔውን ለማሳለፍ በተጠራው ስብሰባ የተገኙ አመራሮች አንገተ ሙሉ ሹራብ ለብሰው ታይተዋል።

የቶኪዮ አገረ ገዢ “ነዋሪዎች ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በመማር አንተ ሙሉ ሹራብ ይልበሱ” ብለዋል።

ማክሮን አንገት የሚሸፍን ሹራብ በመልበስ ይታወቃሉ። በእርግጥ የፋሽን ምርጫ ይሁን ለኃይል ቁጠባ የተደረገ ግልጽ አይደለም።

“ሙሉ ሹራብ ያሞቃል። ኃይል ይቆጥባል። የካርበን ልቀትንም ይቀንሳል። ይህም በክረምት ወቅት በብልሀት የኃይል ፍጆታ ከምንቆጥብበት መንገድ አንዱ ነው” ብለዋል አገረ ገዢዋ።

ጨምረውም “ስለተፈጠረው የኃይል አቅርቦት መዋዠቅ አዝናለሁ። ግን በመጪው ክረምት እየዘነጥን ስለ ኃይል ቁጠባም ማሰብ አለብን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ባለፈው ወር የጃፓን መንግሥት ዜጎች አገልግሎት እየሰጡ ያልሆኑ መብራቶችን እንዲያጠፉ ጠይቀዋል።

ለማሞቂያ ማሽን የሚወጣውን ኃይል ለመቆጠብ ሲባል ቤት ውስጥ ደራርቦ መልበስንም መንግሥት መክሯል።

ፈረንሳይ እና ሌሎችም የአውሮፓ አገራትም ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፈዋል።

ጀርመን የንግድ ተቋማትና ሕንጻዎች አላስፈላጊ መብራት እንዲያጠፉ ወስናለች።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በዓለም ዙሪያ የጋዝና የነዳጅ አቅርቦት በመስተጓጎሉ ዋጋቸው ንሯል።

በዚህም ሳቢያ በርካታ የምዕራባውያን አገራት ነዋሪዎች በቀዝቃዛው የክረምት ወራቶቻቸው ወቅት ቤቶቻቸውን እና የሥራ ቦታቸውን ለማሞቅ የሚጠቀሙበትን የኃይል አቅርቦት እንዲቆጥቡ እየተመከሩ ነው።