20 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ግቡ ያደረገው አረንጓዴ አሻራ እና አፍሪካ

የፎቶው ባለመብት, AFP
- ፀሐፊ, በሶራያ አሊ
- የሥራ ድርሻ, ከቢቢሲ ኒውስ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ 20 ሚሊዮን ዛፎችን ለመትከል ዕቅዷን ይፋ አድርጋ በጀመረችበት ጊዜ በዓለም ደረጃ መነጋገሪያ ሆና ነበር።
እስካሁንም የተያዘው ዕቅድ ከታሰበው በላይ መሳካቱንና ይህም የእጽዋት ልማት እንደሚቀጥል አሳውቃለች።
ከዚህ ልማት ጋር ተያይዘው የሚወጡት አሐዞች አስደናቂ ናቸው። በዘመቻው ጅማሬ ላይ መንግሥት እንዳለው በአንድ ቀን ውስጥ 350 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞች ተተክለዋል።
ነገር ግን ከድርቅ፣ ከግጭት እና እየጨመረ ከሚሄድ የሕዝብ ቁጥር ጋር እየታገለች ባለችው አገር ውስጥ፣ ይህ በከፍተኛ መጠን የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ምን ያህል ውጤታማ እና የተሳካ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የሚካሄደውን፣ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ዘመቻን የሚደግፉ ሰዎች፣ የችግኝ ተከላው የአገሪቱን የአረንጓዴ እጽዋት ሽፋንን እንዳሳደገ፣ የአየር ንብረት ለውጥን እየተከላከለ እና የሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ እያመጣ ነው ይላሉ።
በእርግጥም ይህ እንቅስቃሴ የደኖች መመናመን የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ ግንዛቤን የጨመረ ሲሆን፣ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ የብዙኃን ተሳትፎን ለመሳብ ችሏል።
ምን ያህሎቹ ችግኞች ጸደቁ?
በመንግሥት የሚደገፈው የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የቴክኒክ ኮሚቴ እንደሚለው በአውሮፓውያኑ 2019 ከተተከሉት ውስጥ 83.4 በመቶው እንዲሁም በ2020 ከተተከሉት ውስጥ ደግሞ 79 በመቶው ችግኞች ጸድቀዋል።
ተቀማጭነቱን ለንደን ያደረገው የዓለም አቀፍ የልማትና የአካባቢ የጥናት ተቋም (አይአይኢዲ) ባልደረባ የሆኑት ጄምስ ሜይርስ ግን እነዚህ አሐዞች አስተማማኝ አይደሉም ይላሉ።
ጄምስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ችግኞቹ ከተተከሉ በኋላ ስላላው ሁኔታ የሚከታተልበት ሂደትን ማዘጋጀት አለበት ይላሉ።
“ዘመቻው ከተጀመረ ጥቂት ዓመታትን ብቻ ነው ያስቆጠረው። ስለዚህም ዋናው ነገር በረዥም ጊዜ ውስጥ የችግኞቹ መጽደቅ ነው” ብለዋል።
ከዚህ በፊት በዓለም ዙሪያ የተካሄዱ ተመሳሳይ የችግኝ መትከል እንቅስቃሴዎች ፈተና ገጥሟቸዋል።
በሳይንቲስቶች ቡድን ተካሂዶ በ ‘ሮያል ሶሳይቲ ጆርናል’ ላይ በዚህ ሳምንት የታተመ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፣ በእስያ ውስጥ ደን ለማልማት የተካሄደ ፕሮጀክት ከአምስት ዓመታት በኋላ መቀጠል ሳይችል ቀርቷል።
ነገር ግን የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የቴክኒክ ኮሚቴን የሚያስተባብሩት አቶ አደፍርስ ወርቁ እንደሚሉት፣ ከየአካባቢው ማኅበረሰብ በተሰበሰበው አሐዝ ላይ እምነት አላቸው።
“ይህም በገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል እንደሚረጋገጥ ተስፋ እያደረግን ነው” ሲሉ አቶ አደፍርስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሚተከሉ ዛፎች ዓይነት
በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ ደን የማልማት ሥራን ማከናወን ቀላል የሚባል ተግባር አይደለም።
በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የችግኝ ተከላን ከግብርና ጋር በማቀናጀት ማካሄድ እና አቮካዶን እንዲሁም ፓፓያን የመሳሳሉ ፍራፍሬዎችን ጨምሮ የተለያዩ ችግኞች ተተክለዋል።
“ትክክለኛውን ዝርያ፣ በትክክለኛው ቦታ፣ ለትክክለኛው ዓላማ መትከል አስፈላጊው ነገር ነው” ይላሉ መቀመጫውን ኬንያ ያደረገው የግብርና እና የደን ልማት ማዕከል ባለሙያ የሆኑት ላርስ ግሩዳል።
ማዕከሉ ለኢትዮጵያ የደን ልማት እንቅስቃሴ ችግኝ እና ዘር ለሚያቀርቡ የችግኝ ማፍያዎች ስልጠናን ይሰጣል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራውን በጀመረበት ዓመት ላይ ደካማ ዕቅድ እንደነበረው ትችት ገጥሞት ነበር።
በወቅቱ ገበሬዎች በአንድ ቀን ተነግሯቸው ወደ ችግኝ ተከላ የገቡ ሲሆን፣ ችግኞችም በድንጋያማ እና በማያመች ሁኔታ ውስጥ እንዲተተከሉ ተደርጓል ይላል በአይአይኢዲ እና በአንድ የአገር ውስጥ አማካሪ ድርጅት በጋራ ያወጡት ዘገባ አመልክቷል።
ጨምሮም ለምሳሌ የባሕር ዛፍ ችግኞች “አካባቢውን ሊጎዱ በሚችሉበት አካባቢዎች መተከላቸው” ተገልጿል።
ባሕር ዛፍ በፍጥነት ስለሚያድግ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ስለሚውል በአንዳንድ ገበሬዎች ይመረጣል።
ነገር ግን ባሕር ዛፍ ለማደግ በርካታ ውሃን የሚፈልግና ጠቃሚ የአፈር ንጥረ ነገሮችን አሟጦ ስለሚጠቅም በአካባቢው ሌሎች ሰብሎችን ለማብቀል አስቸጋሪ ያደርገዋል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ የደን እና የግብርና ተቋማት ለደን ልማት ለሚተከልበት አካባቢ ተስማሚ የሆኑ ዛፎችን መጠቀም ተመራጭ እንደሆነ ይመክራሉ።
እነዚህም አገር በቀል ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፤ ነገር ግን ችግኙ የሚተከልበትን አካባቢን ተፈጥሯዊ ይዘት የሚደግፍ ሊሆን ይገባል።
ባሕር ዛፍን የመሳሰሉ ዛፎች ከሌሎች አጋራት የሚመጡ ዛፎች ጠቀሜታ ሊኖራቸው ይችላል፣ ቢሆንም ግን በጥንቃቄ ሊተከሉ እና ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል።
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ቀርከሃን የመሳሳሉ በርካታ የአገር በቀል ዛፎች ችግኞች እንዲተከሉ ለማድረግ ጥረት አድርጓል።
ነገር ግን ትክክለኛውን ውጤት ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ባለፉት ዓመታት የተተከሉትን አገር በቀል የሆኑትን እና ያልሆኑትን የተመለከተ አሐዝ የለም። የአረንገዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴም ይህንን መለየት በቀጣይ የሚያከናውነው ትንተና አንድ እንደሆነ ገልጿል።
“ዓይነታቸው የበዛ የዛፍ አይነቶችን መትከል በአንድ ጀምበር የሚከናወን ሥራ አይደለም” የሚሉት ግሩዳል፣ በአሉታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት መስጠት ትክክል እንዳልሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል።
“ይህንን ለማሳከት ጊዜ ይፈልጋል። ቢሆንም ይህ ሰዎች ሥራቸውን ከማከናወን ሊያግዳቸው አይገባም። ኢትዮጵያ ተጨማሪ አገር በቀል ዛፍ ዝርያዎችን ለመጠቀም ያላትን ሃብት እያዳበረች ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
‘ትሪ ኤይድ’ ለተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚሰሩት ቶም ስኪሮው እንደሚሉት፣ እንጨት እና ምግብን የመሳሰሉ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተጨባጭ ውጤትን የሚያበረክቱ ዛፎችን መትከል አስፈላጊ ነው። ይህም ገበሬዎች ማበረታቻና በዘላቂነት እንዲንከባከቧቸው ያደርጋል።
የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋትን የደቀነው ሌላው ጉዳይ በቀጠናው ባለፉት 40 ዓመታት ካገጠሙት ሁሉ የከፋው ድርቅ መከሰቱ ነው። በዚህም ሳቢያ አንዳንድ አካባቢዎች ከሁለት ዓመት በላይ ዝናብ ባለማግኘታቸው የተተከሉ ችግኞች ላይ አደጋ ደቅኗል።
ከዚህ ባሻገርም ደን አልሚዎች ክስተቱን ከግንዛቤ በማስገባት ድርቅን የሚቋቋሙ ዛፎችን መትከል ይኖርባቸዋል።
“ዛፎችን መትከል ለዛሬ ብቻ ተገቢ የሆኑትን ብቻ ሳይሆን፣ ከመጪው ዘመን የአየር ሁኔታ ጋር እንዲስማሙ ማድረግ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልገናል” ሲሉ ስኪሮው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ትክክለኛ ያልሆኑ የዛፍ ዓይነቶችን የምንተክል ከሆነ ከወዲሁ ስጋት ላይ የወደቀውን የውሃ አቅርቦት ችግርን የሚያባብሰው ሲሆን፣ ትክክለኛውን የምንጠቀም ከሆነ ደግሞ ዘላቂ ጥቅምን ያስገኛል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዝናብ ምንጭ
በዴንማርክ የሚገኘው ‘ፎረስት ኦፍ ዘ ወርልድ’ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት የንስ ካንስትረፕ፣ የደን ሽፋን መልሶ እንዲያገግም ማድረግ የአየር እርጥበትን ለመጠበቅ ይረዳል ይላሉ።
“ደን ልማት እና የግብርና ሥራ በሚከናወንባቸው ስፍራዎች ያሉ ማኅበረሰቦች ደረቃማው ወቅት ሲያበቃ የአካባቢያቸው አፈር ርጥበታማ እና ለም ይሆናል። ነገር ግን በገላጣ ቦታዎች የሚኖረው አፈር ግን ሙሉ ለሙሉ ደረቅ ይሆናል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ደን ማልማት የውሃ አቅርቦትን በማሳደግ በኩል ጠቀሜታ እንዳለው የሚያሳየን በአውስትራሊያ የተሰራ ጥናትን በመጥቅስ፣ ትክክለኛ ዛፎችን መትከል ከተቻለ በረዥም ጊዜ ውስጥ የዝናብ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል ይላሉ ግሩዳል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሹ ጦርነት ደን የማልማት ሥራው ላይ ተጽዕኖን አስከትሏል።
በቅርቡ የሰላም ስምምነት የተፈረመ ሲሆን፣ ክልሉ ጦርነቱ በተካሄደበት ጊዜ ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ተነጥሎ በመቆየቱ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴን በተመለከተ ስላለፈው ዓመት ምንም መረጃ የለም።
በትግራይ ክልል የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴን እንዲመሩ ተመድበው የነበሩት አቶ አደፍርስ፣ ሥራው ይጀመራል የሚል ተስፋ አላቸው።
“ከአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴው በፊትም ቢሆን፣ ትግራይ ውስጥ በርካታ ስኬታማ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል” ብለዋል።
“የተፈረመው ስምምነት ከሰመረ፣ ወደ ትግራይ በመመለስ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎቻች ያሉበትን ሁኔታ ለመመልከት የመጀመሪያው ሰው እሆናለሁ።”

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታላቁ አረንጓዴ ግድግዳ
ይህ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ባሻገር ካለው አፍሪካ አቀፍ የታላቁ የአረንጓዴ ግድግዳ ልማት ፕሮጀክት ዕቅድ ጋር የተያያዘ ነው።
ይህ እንቅስቃሴ በአውሮፓውያኑ 2007 ላይ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የተጀመረ ሲሆን፣ በዚህም ከጂቡቲ አስከ ሴኔጋል የሚዘረጋ 8,000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዛፎች ከለላ መፍጠርን አላማ ያደረገ ነው።
እስከ 2030 ድረስ በሚለማው የአረንጓዴ ግድግዳ ደን የሰሃራ በረሃ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንዳይስፋፋ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው።
ዕቅዱ ከውጭ ለጋሾች ግዙፍ የገንዘብ ድጋፍ ቢያገኝም በፍጥነት ስኬትን ለማስመዝገብ ሳይችል ቆይቷል።
በ2017 (እአአ) እንደተገመተው ከሆነ ለፕሮጀክቱ ከተቀመጠው ዕቅድ ውስጥ 15 በመቶውን ብቻ እንዳሳካ የተነገረ ሲሆን፣ አንዳንዶች ይህንን ወደ አራት በመቶ ያወርዱታል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ግዙፍ የደን ሽፋን ለማልማት የተጀመረው ፕሮጀክት “በመላው አህጉሪቱ ያሉትን መልሶ እንዲያንሰራሩ ወደ ማድረግ” ፊቱን አዙሯል።
ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን በማዘጋጀት ትልቅ የሚባለውን ዕቅድ ይዛለች።
ከአፍሪካ ኅብረት እና ከኢትዮጵያው የደን ልማት እንቅስቃሴዎች ጋር የሚሰራው ‘ትሪ ኤይድ’ እንደሚለው ሁለቱ ፕሮጀክቶች የከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ድጋፍ እንዳላቸው አሳይተዋል፣ ይህም በዘላቂነት እንዲሳካ በዝቅተኛ ደረጃ ኅብረተሰብን በማሳተፍ ሊሰራ ይገባል።
“በከፍተኛ ቁጥር ዛፎች ሲተከሉ በርካታ ችግሮች ያጋጥማሉ። ስለዚህም የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴን የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በጋራ ልንደግፋቸው ይገባል” ይላሉ ስኪሮው።
“በደን ልማቱ ሂደት የሚገኙ ልምዶችን ልንጋራ ይገባል፣ ካጋጠሙን ውድቀቶች በመማር በጋራ መሻሻል ይኖርብናል።”












