የካናዳው ዳቦ ቤት ሆነ ብሎ ዋጋ በመጨመሩ 50 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ተቀጣ

ካናዳ ብሬድ በዋጋ ጭማሪ ወንጀል ቅጣት ደርሶበታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካናዳ ውስጥ ከሚገኙ ዳቦ አምራቾች ቁንጮው ሆነ ብሎ ዋጋ በመጨመሩ የ50 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ቅጣት ተከናንቧል።

ካናዳ ብሬድ ባለፈው ረቡዕ ለዓመታት ይህን ጉዳይ ሲፈፅም እንደነበር አምኗል።

የካናዳ የገበያ ውድድር ቢሮ ዳቦ ቤቱን ጠርጥሮ ለበርካታ ዓመታት ምርመራ ሲያደርግበት ቆይቷል።

ቢሮው ዳቦ ቤቱ ላይ የተጣለው ቅጣት ሲያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም ብሏል።

“የዳቦ ዋጋን ሆነ ብሎ መጨመር፤ ሊያውም የካናዳዊያን የለተ ዕለት ማዕድ የሆነውን ዳቦ? ይህ ትልቅ ወንጀል ነው” የቢሮው ሠራተኛ ማቲው ቦስዌል ናች ይህን ያሉት።

“ዋጋ የሚጨምሩ ሌሎች ሰዎችንም እያሳደድን ለሕግ እናቀርባለን” ሲሉ ማስጠንቀቂያ እክለዋል።

በኦንታሪዮ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰነደው የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው ካናዳ ብሬድ የተሰኘው ድርጅት የዳቦ ዋጋ እንዲንር አድርጓል።

ካናዳ ብሬድ ከተቀናቃኙ ዌስተን ፉድስ ጋር በማበር የሳንድዊችና የቋሊማ እንዲሁም ባለስሙኒው ዳቦ ዋጋ ከፍ አድርጓል።

ድርጅቱ ይህን የፈፀመው በፈረንጆቹ 2007 እና 2011 ዓመተ ምሕረት ነው።

ቀድሞ ማፕል ሊፍ ፉድስ የተሰኘው ድርጅት ንብረት የነበረው ካናዳ ብሬድ አሁን የሜክሲኮው ግሩፕ ቢምቦ አካል ሆኗል።

ግሩፖ ቢምቦ በለቀቀው መግለጫ ድርጅቱን በ2014 የግል ንብረቱ ሲያደርግ ስለወንጀሉ የሚያውቀው አንዳች ሚስጥር እንደሌለ ገልጧል።

“እነሆ አሁን በአዲስ ጥላ ሥር ያለው ካናዳ ብሬድ ለደንበኞቹ መልክና ቁመና ያላነሰው ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ቆርጦ ተነስቷል።

ለካናዳዊያን የዳቦ ቅርጫት ከመሆን የሚያግደን የለም” ይላሉ የድርጅቱ ምክትል ፕሬዝደንት አሊስ ሊ።

ዋጋ እየጨመሩ የካናዳዊያንን ኪስ ያራቆቱት የቀድሞ የካናዳ ብሬድ አስተዳዳሪዎች አሁን ድርጅቱን ለቀው ሄደዋል።

የገበያ ውድድር ቢሮው ሌሎች ዋጋ የጨመሩ ዳቦ ቤቶች ካሉ የእጃቸውን እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

የአንድ ዳቦ ዋጋ ማንም ሳያስተውለው በ16 ዓመታት ውስጥ የ1 ዶላር ከሐምሳ ዋጋ ጭማሪ ማምጣቱን ቢሮው ደርሶበታል።

በርካታ ቸርቻሪዎች ዋጋ ጨምራችኋል ተብለው በቢሮው ዓይን ውስጥ ገብተዋል። ነገር ግን አንዱም ጥፋታቸውን አላመኑም።

ከሰሞኑ ሥራ የበዛበት የውድድር ቢሮ በቅርቡ የትኛው ‘ሱፐርማርኬት’ የሸቀጥ ዋጋ እንደጨመረ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግ ቋምጧል።

ቢሮው ላለፉት ሁለት ዓመታት ምርመራውን ሲከውን ቆይቷል።