በታይዋን የመዋዕለ ህጻናት መምህራን ህጻናቱን በማደንዘዝ ተወነጀሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በታይዋን ውስጥ የመዋዕለ ህጻናት ተማሪዎች አደንዛዥ ንጥረ ነገሮችን ወስደው መገኘታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጥሯል።
ህጻናቱ ላይ በተደረገም ምርመራ ነው ይህ ይፋ የሆነው።
በኒው ታይፔ ከተማ በሚገኘው መዋዕለ ህጻናት ውስጥ ያሉ መምህራን በጉንፋን ሽሮፕ ውስጥ የሚገኙ ፌሮባርቢታል እና ቤንዞዲያዜፖፒንስ ባሉ ንጥረ ነገሮች ህጻናቱን በማደንዘዝ ተከሰዋል።
ፖሊስ ለሳምንታት ምርመራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላም ህጻናቱ ለምን ሱስ አስያዥ የሆኑ ሽሮፖች በተደጋጋሚ እንደተሰጣቸው ግልጽ አይደለም ብሏል።
ይህንንም የአደንዛዥ ንጥረ ነገሮች
ውዝግብ ተከትሎ በርካታ ቤተሰቦች ከመንግሥት ህንጻዎች ውጭም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
በኒውታይፔ ከተማ እሁድ እለት በነበረውም የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወላጆች የፖሊስ ምርመራ ውጤት ግልጽነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።
በርካቶችም ባለስልጣናቱን ምርመራውን ለህዝብ ይፋ አላደረጉም ሲሉም ተችተዋል።
ሰኞ ዕለትም በታይዋን ደሴት ሌላኛው ጫፍ በምትገኘው በደቡባዊ የካኦሲዩንግ ከተማም በአንድ የህክምና ማዕከል ተመሳሳይ ጥያቄ ያስነሳ ነገር ተከስቷል።
የአካባቢው ጤና ቢሮ አራት ዶክተሮች 20 በሚሆኑ ህጻናት ላይ ፌኖባርቢታልን አላግባብ በመስጠት ጥፋተኛ ተብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ የጤና ባለሙያዎቹ ከስራቸው ለስድስት ወራት እንዲታገዱና እያንዳንዳቸው 46 ሺህ 121 ዶላርም እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።
ቁጣና ስጋት በማህበረሰቡ ዘንድ ተንሰራፍቶ ባለበት በአሁኑ ወቅት የታይፔ ከተማ ሆስፒታል ለመዋዕለ ህጻናት ተማሪዎች የደም ምርመራዎችን በነጻ ማድረግ ጀምሯል። ይህም ምርመራ ህጻናቱ አደንዛዥ ንጥረ ነገሮች በደማቸው እንዳለም ለመመርመር ነው።
በኒው ታይፔ ከተማ በሚገኝ የግል መዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤት ሰራተኞች የማይታወቁ መድኃኒቶች ለልጆቻችን እየሰጧቸው ነው ሲሉ ወላጆች በግንቦት ወር ክስ አቅርበው ነበር። ይህንንም ተከትሎ ነው ምርመራው በፖሊስ የተከፈተው።
የአምስት ዓመት ህጻን አባት የሆኑት ማይክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የካቲት ወር ላይ በነበረው አዲስ ዓመት በዓል ላይም ልጆች ደንዝዘው ማየታቸውን ወላጆች መታዘባቸውን ገልጸዋል።












