ቪላ አርሰናልን በማሸነፍ በሜዳው የድል አድራጊነቱን ክብር ያስቀጥላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዚህ ሳምንት ዋነኛ ትኩረት ቪላ ፓርክ ነው።
አስተን ቪላ በሻምፒዮኖቹ ላይ ፍጹም የበላይነትን በመወሰድ ድል አድርገዋቸዋል። በሜዳቸውም የማይቀመሱ መሆናቸውን አሳይተዋል።
ግን ግን ቪላ ይህን በአርሰናል ላይ ይደግመዋል? ሲል የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን ይጠይቃል።
ሱቶን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታ ውጤቶችን እንደሚከትለው ገምቷል።
ቅዳሜ
ክርስታል ፓላስ ከ ሊቨርፑል
ፓላስ ካለፉት ስምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው። በዚህም የሮይ ሆድሰን በቡድኑ የመቆየት ጉዳይ አጠራጣሪ እየሆነ መጥቷል።
ምንም እንኳ ፓላስ ከሊጉ የመውረድ ስጋት አለበት ብዬ ባላስብም በአሁኑ አቋማቸው ጠንካራ ተፎካካሪዎችን መቋቋም የሚችሉ አይመስለኝም።
ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙት ሊቨርፑሎች ይህን ጨዋታ እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።
ግምት፡ ፓላስ 0 - 2 ሊቨርፑል

ብራይተን ከ በርንሌይ
ይህ በጎል የታጀበ አዝናኝ ጨዋታ እንደሚሆን እገምታለሁ። ሁለቱም አሠልጣኞች አጥቅተው መጫወትን ይመርጣሉ።
በተመሳሳይ ሁለቱም ክለቦች የተከላካይ መስመር ችግር አለባቸው። ብራይተን ባለፈው የውድድር ዘመን ያሳየውን ጥንካሬ መድገም አልቻለም። በዚህ የውድድር ዓመትም በርካታ ግቦች ተቆጥረውባቸዋል።
በርንሌይ ሼፊልንድን ማሸነፉ ትልቅ መነሳሳት ቢሆንም፣ ከሜዳው ውጪ ብራይተንን ያሸንፋሉ ብዬ አልገምትም።
ግምት፡ ብራይተን 3 - 1 በርንሌይ
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ቦርንመዝ
የዩናይትድ ውጤትን ስንመለከት ወጥነት ያለው አቋም ይመስላል። አጨዋወታቸውን ብቻ ለተመለከተ ደግሞ ግራ የሚገባ ቡድን ነው። በመልበሻ ክፍል ውስጥ የሁሉም ተጫዋቾች ድጋፍ የላቸውም እየተባለ የሚወራባቸው ኤሪክ ቴን ሃግ ባለፈው ጨዋታ ቼልሲን ማሸነፋቸው ትልቅ እረፍት ይሆናቸዋል።
ይሁን እንጂ ቴን ሃግ በሜዳቸው ቢጫወቱም ከቦርንመዝ ቀላል የማይባል ፈተና ይጠብቃቸዋል። ቼሪስ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸነፍው አንዱን አቻ ተለያይተዋል።
ግምቴ ቦርንመዝ ከዩናይትድ ጋር ነጥብ ይጋራል የሚል ነው።
ግምት፡ ዩናይትድ 1 - 1 ቦርንመዝ

ሼፊልድ ከ ብሬንትፎርድ
አዲሱ የሼፊልድ አሠልጣኝ ክሪስ ዋይልደር አንድ ዓላማ ነው ሊኖራቸው ይሚችለው። ይህም ቡድኑ ከሊጉ እንዳይወርድ ማስቻል። ይህ ግን ቀላል እንደማይሆን መገመት ይቻላል።
ለንቦቹ ብራይን እምቦሞ መጎዳት ትልቅ ኪሳራ ነው የሚሆነው። ብሬንትፎርድ ግብ አስቆጣሪያቸውን ባይዝም ይህን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ገምታለሁ።
ግምት፡ ሼፊል 0 - 1 ብሬንትፎር
ዎልቭስ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ይህ ጨዋታ ከማንም በላይ ለስቲቭ ኩፐር ወሳኝ ግጥሚያ ነው። ቡድናቸው ባለፉት 11 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው።
ባለፈው ጨዋታም በፉልሃም 5 ለ 0 መሸነፉ ቅስም የሚሰብር ነው።
ፎረስት ምንም እንኳ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ቢለውም ጥሩ ተደራጅቶ የሚገኘውን ዎልቭስ ያሸንፋል ብዬ መገመት ይከብደኛል።
ግምት፡ ዎልቭስ 2 - 0 ፎረስት

ቪላ ከ አርሰናል
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ይህ ነው።
ቪላ ሲቲን አሸነፎ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ከሁሉ በላይ አስደናቂው ነገር የኡናይ ኤምሪ ቡድን በሜዳው ያለው ሬኮርድ ነው። በሜዳው በተከታታይ 14 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል።
አንድ መረሳት የሌለበት እውነታም አለ። ለመጨረሻ ጊዜ ቪላ በሜዳው የተሸነፈው በአርሰናል ነው።
ይህ ጨዋታ ጥንቃቄ እና መከላከል የበዛበት ይሆናል።
መድፈኞቹ ይሸነፋሉ ብዬ አልጠብቅም።
ግምት፡ ቪላ 1 - 1 አርሰናል
እሁድ
ኤቨርተን ከ ቼልሲ
ሾይን ዳይሽ በኤቨርተን አስደናቂ ሥራን እያከናወኑ ነው። ሰማያዊዎቹ 10 ነጥቦችን ተቅጥተው እንኳ ኒውካስልን አሸንፈው ከወራጅ ቀጠና መውጣት ችለዋል።
ከቼልሲው ሞሪሲዮ ፖቼቲኖ ቡድን ምን መጠብቅ እንዳለብኝ አላውቅም። በውድድር ዓመቱ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች እስካሁን ስላልተሸነፉ ይህ ጨዋታ አቻ ይጠናቀቃል ብዬ እገምታለሁ።
ግምት፡ ኤቨርተን 1 - 1 ቼልሲ

ፉልሃም ከ ዌስት ሃም
ፉልሃም በተጋጣሚዎቹ ላይ ግቦችን እያዘነበ ነው። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች 11 ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል። ልብ በሉ ከዚያ በፊት በነበሩት 12 ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው ግብ 10 ብቻ ነው።
እውነት ነው ዌስት ሃም ከሜዳው ውጪ ቶተነሃምን ማሸነፉ አስደናቂ ነው። ግን ይህን ጨዋታ ባለሜዳው ፉልሃም እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።
ግምት፡ ፉልሃም 2 - 1 ዌስት ሃም
ሉተን ከ ማንቸስተር ሲቲ
ማን ሲቲ ይህን ጨዋታ የማያሸንፍበት ምንም ምክንያት የለም። ግዴታ ማሸነፍ አለበት።
ሮድሪ ወደ ሜዳ ተመልሷል። ስለዚህ የተከላካይ አማካዩ ክፍል ይጠናከራል። ቪላ ፓርክ ላይ ሁለት ጊዜ ብቻ ሙከራ ማድረጉ በሲቲ ደረጃ ካለ ቡድን የሚጠበቅ አይደለም። ይህን መቀየር ይኖርበታል።
ሉተን በሜዳቸው ሊቨርፑል እና አርሰናልን ፈትኗል። ባለቁ ሰዓታት በተቆጠሩባቸው ግቦች ነው ከሊቨርፑል ጋር አቻ የተለያዩት፤ በአርሰናል ደግሞ የተሸነፉት።
ሉተን ሲቲ ላይም እንደሚበረታ አልጠራጠርም፤ ነገር ግን የጋርዲዮላው ቡድን ይህን ጨዋታ ያሸንፋል።
ግምት፡ ሉተን 1 - 3 ሲቲ
ቶተነሃም ከ ኒውካስል
የቶተነሃም አሠልጣኝ ጥሩ አጀማመር አሳይተው ብዙ ሽንፈቶችን በተከታታይ አስተናግደዋል። ከዚህ ጨዋታ አዎንታዊ ውጤት ማግኘት እንደሚኖርባቸው ባስብም ከኒውካስል ሦስት ነጥብ መውሰድ ቀላል አይሆንም።
ኒውካስል እንዲሁ ከሜዳው ውጪ ይህ ነው የሚባል አርኪ ውጤት ሲያስመዘግብ አይታይም። በኤቨርተንም ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናግዷል።
ሁለቱም ቡድኖች በጉዳት ምክንያት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ቢያጡም በዚህ ጨዋታ ብዙ ግብ እንደምንመለከት እገምታለሁ።
ግምት፡ ቶተነሃም 3 - 3 ኒውካስል












