አሌሃንድሮ ጋርናቾ፡ “በእግር ኳስ ሕይወቱ ከዚህ የተሻለ ጎል አያስቆጥርም”

የአሌሃንድሮ ጋርናቾ ጎል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሌሃንድሮ ጋርናቾ ጎል

“እንዲህ ያለ መቀስ ምት ስታድየም ተገኝቼ አይቼ አላውቅም። ዋይኒ ሩኒ ያን ድንቅ ጎል ማንቸስተር ሲቲ ላይ ሲያስቆጥር ተመልክቻለሁ፤ ግን ይህ ይለያል።”

ጋሪ ኔቪል የአሌሃንድሮ ጋርናቾን ጎል ለመግለጥ ቃላት ያጠሩት ይመስላል።

ዩናይትድ ኤቨርተንን 3-0 ሲረታ ጋርናቾ በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ ድንቅ ከሚባሉ ጎሎች አንዱን አስቆጥሯል።

የ19 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የክንፍ መስመር ተጫዋች በሶስተኛው ደቂቃ ከዲዮጎ ዳሎ የተሻገረለትን ኳስ በአስደናቂ መቀስ ምት ወደ ጎል በመቀየር የጉዲሰን ፓርክ ተመልካቾችን አፍ አስከፍቷል።

“እውነት ለመናገር ማመን ተስኖኛል” ብሏል ጋርናቾ ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያት።“ደጋፊውን ሲጮህ ሰማሁና ለራሴ «ፈጣሪ ሆይ» አልኩ” ይላል።

የቀድመው የኤቨርተን አማካይ ሊዮን ኦስማን ቢቢሲ ራድዮ 5 ላይ ተገኝቶ “አፍ የሚያስከፍት አስደናቂ ክስተት ነው። ሁሉም ሰው ያን የመሰለ ጎል በመመልከቱ ተደንቋል።”

“አጨራረሱ ብቻ አይደለም የሚያስደንቀው። ኳሷ መጀመሪያው ከዩናይትድ ሜዳ ስትሻገር ጀምሮ ዳሎ ደርቦ የሮጠው፤ ከዚያ ሲያሻግረው፤ ቀጥሎ ደግሞ ጎሉ።”

የቀድሞው የዩናይትድ አምበል ጋሪ ኔቪል ለስካይ ስፖርትስ በሰጠው አስተያየት “አስማታዊ ክስተት። አስማታዊ ጎል። ይህ የመሰለ ጎል በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ አናይም። ይህ ከአስደናቂ ጎሎች አንዱ ነው” ብሏል።

“እኔ እስካሁን አላመንኩም። በእግር ኳስ ሕይወት ከዚህ የተሻለ ጎል ያስቆጥራል ብዬ አላስብም። እጅግ አስገራሚ ጎል።”

“ከጎል ሜትሮች ርቆ፤ እግሩን እንደ መቀስ አቆላልፎ ሰውነቱን አንሳፎ ያገባው ጎል ነው። እንዲህ ዓይነት ጎል አይቼ አላውቅም” ሲል መደነቁን ይገልጣል።

ባለፈው ቅዳሜ የክሪስታል ፓላሱ ማይክል ኦሊሴ ሉተን ታውን ላይ ድንቅ ጎል አስቆጥሯል።

ማች ኦፍ ዘ ደይ የተሰኘውን ፕሮግራም የሚያዘጋጁት ጋሪ ሊኒከር እና አለን ሺረር “የኦሊሴ ጎል የዓመቱ ምርጥ ጎል ተብሎ ሊታጭ ይገባዋል” ብለው ነበር።

ነገር ግን 24 ሰዓት እንኳ ሳይሞላው ሐሳባቸውን የሚያስቀይር አዲስ ክስተት ታየ። እንዳለመታደል ሆኖ ኦሊሴ ያስቆጠረው ጎል የወሩ ምርጥ እንኳ ለመባል ይሳነዋል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ለቢቢሲ ስፖርት ሲናገሩ “አጨራረሱ ድንቅ ነው። ገና የውድድር ዘመኑ ልጅ ቢሆንም የዓመቱን ምርጥ ጎል አይተናል” ብለዋል።

ነገር ግን አሰልጣኙ ጋርናቾ ከሌሎች ታላላቅ ተጫዋቾች ተርታ ለመሰለፍ ገና ብዙ ይቀረዋል ብለው ያምናሉ።

“ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ጭላንጭል አይተናል። ቢሆንም እንደ ዋይን ሩኒ አሊያም እንደ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለመሆን በፕሪሚዬር ሊጉ የውድድር ዘመን ከ20-25 ጎል ማስቆጠር አለብህ።”

የቀያይ ሰይጣኖቹ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ “የምገልጥበት ቃል የለኝም። ልዩ ጎል ከልዩ ልጅ። እጅግ አስደናቂ” ብሎታል።

ከዚህ ቀደም ካየናቸው ድንቅ የመቀስ ምት ጎሎች መካከል ጥቂቱን እንጥቀስ፡

  • በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 12/2011 ዋይኒ ሩኒ በፕሪሚዬር ሊጉ ማንቸስተር ሲቲ ላይ ያስቆጠራት ጎል
  • ጋሬዝ ቤል በ2018 ግንቦት 26 በአውሮፓው ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ሊቨርፑል ላይ አስቆጥሮ ያሳየን ጎል
  • ትሬቨር ሲንክሌር በ1997 ጥር 25 በኤፍ ኤ ዋንጫ ባርንስሊ ላይ ከ20 ጫማ ርቀት ያስቆጠራት ጎል
  • ዝላታን ኢቭራሂሞቪች ኅዳር 3/2012 ስዊድን ከእንግሊዝ የወዳጅነት ስትጫወት ከርቀት ተቀልብሶ ያስቆጠራት ጎል
  • ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ2018 ሚያዝያ 3 በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጁቬንቱስ ላይ ያስቆጠራት ጎል