የ2026 ዓለም ዋንጫ ሕልሙ ሳይጀመር የተቀጨው የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤርትራ ለ2026 ዓለም ዋንጫ ለመድረስ የነበራት ሩቅ ሕልም ሳይጀመር በአጭሩ ተቀጭቷል።
የምስራቅ አፍሪካዋ ሃገር ለመጨረሻ ጊዜ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ያደረገችው በአውሮፓውያኑ ጥር 2020 ነበር። አሁን ደግሞ ሜክሲኮ፣ አሜሪካ እና ካናዳ ከሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ውጭ መሆኗ ታውቋል።
ኤርትራ በ2022 የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ከነበረችው ሞሮኮ ጋር የነበራት የማጣሪያ ጨዋታ አንድ ሳምንት ሲቀረው ነው ራሷን ያገለለችው።
የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ የሃገሪቱ መንግሥት ስለዚህ ውሳኔ ምንም መረጃ አልሰጡም፤ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ግን በውሳኔው ቁጭታቸውን ገልጠዋል።
“እንዴት ይህ ሊሆን እንደቻለ፤ ውሳኔውን ማን እንዳስተላለፈ የማውቀው ነገር የለም። ከላይ የተቀመጡት ሰዎች እግር ኳስ በቁም ነገር እንዳልወሰዱት ግን ግልጥ ነው” ይላል ለስዊድናዊው ክለብ የሚጫወተው ኤርትራዊው አማካይ ሞሐመድ ሰዒድ።
“በጣም ተበሳጭቻለሁ። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በርካታ ትውልደ ኤርትራዊያን አውሮፓ ውስጥ ይጫወታሉ። ዕድሉ ቢሰጠን መወዳደር እንችል ነበር። ነገር ግን አሁን እየሆነ ያለውን ሲያዩ ወደፊት ሃገራቸውን መወከል ይፈልጋሉ ወይ?” ይላል ሞሐመድ።
“አንድ ቀን ለልጆቼ ለኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቻለሁ ብዬ እናገራለሁ። ለኤርትራ መጫወቴ ለኔ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ነግራቸዋለሁ። ነገር ግን በርካቶች ይህን ዕድል ተነፍገዋል።”
ከ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያም ራሷን ያገለለችው ኤርትራ ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውጭ መሆኗ ሃገሪቱ በእግር ኳስ ዓለም ያላት ሥፍራ አጠራጣሪ ሆኗል።
ምንም እንኳ ኤርትራ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን ማሕበር ብትሆንም ከዓለም የኳስ ሰንጠረዥ ውጭ ሆናለች።
“ኤርትራ ድንገት ከዓለም እግር ኳስ ውጭ መሆኗ ደጋፊዎችን እጅግ ያስከፋ ነው” ይላል ካናዳ የሚኖረው አክሊል ተኽለአብ።
“አግር ኳስ ከጨዋታም በላይ ነው። የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ነው። አንድነት ነው። ሃገራችን ይህንን የስፖርቱን መንፈስ ስታስወግደው ማየት ልብ ይሰብራል።”
ሃገር ጥሎ የመጥፋት ስጋት
ኤርትራ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ኢ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 10 ጨዋታዎች እንድታደርግ ከሞሮኮ፣ ዛምቢያ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ታንዛኒያ እና ኒጀር ጋር ተደልድላ ነበር።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ከማጣሪያው ራሷን ያገለለችው በሃገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ወደ ውጭ ለግጥሚያ በመወጡበት ይቀራሉ የሚል ፍራቻ ስላለ ነው የሚል መላ ምት ይሰጣል።
ኤርትራ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዋን ባለፈው ሳምንት ወደ ሞሮኮ አቅንታ ማከናወን ነበረባት።
ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 1993 ነፃነት ያገኘችው ኤርትራ በአንድ ፓርቲ የምትመራ መሆኗ፤ ሃገሪቱ እጅግ ወታደራዊ የሆነ መዋቅር ያላት ናት ትባለለች።
የተባበሩት መንግሥታት በያዝነው ዓመት ባወጣው ዘገባ በሃገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የግዴታ የውትድርና ሥልጠና እና አፈና “እጅግ አሳስቦኛል” ብሎ የሕግ የበላይነት “የለም ማለት ይቻላል” ሲል ገልጧል።
ከዚህ ቀደም የተለያዩ ኤርትራዊያን ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን እና ለክለብ ግጥሚያ ከሃገር ወጥተው ቀርተዋል።
ለ2018 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ቦትስዋና ያቀኑ 10 ተጫዋቾች ኅዳር 2015 ጥገኝነት ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል። ታኅሣሥ 2019 ደግሞ ቀጣናዊ ውድድር ለማድረግ ወደ ኡጋንዳ ካቀኑ ተጫዋቾች መካከል ሰባቱ መጥፋታቸው ይታወሳል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የኤርትራ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ እንደሚናገሩት “ተጫዋቾች ጥለው የሚጠፉት ሃገሪቱ ውስጥ ካለው ፖለቲካዊ ውጥረት አንፃር ነው።”
መንግሥት እንደሚለው ሁሉም ሰው ወታደራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት። ሁሉም ሰው፤ ዶክተርም ሆነ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ብስክሌተኛ አሊያም ኢንጂነር፤ ብሔራዊ አገልግሎት መስጠት አለበት። ነገር ግን ይህ ከ18 ወራት በኋላ የሚያበቃ አይደለም። ወደፊት ተስፋ የሚያደርጉበት ነገር የላቸውም፤ አስመራ ውስጥ ደግሞ ጥሩ የሚባል ሕይወት አይደለም የሚኖሩት። ለዚህ ነው አማራጭ ሲያገኙ የሚጠፉት።”
ከኤርትራ እግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል አንዱ ተጫዋቾች ሃገር ጥለው ለመጥፋት መወሰናቸውን እንደሚረዳው ተናግሮ “የሃገሪቱን እግር ኳስ ለማሳደግ ምንም ነገር አልተሠራም” ይላል።
“ብሔራዊው ቡድን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከተሳተፈ ቆይቷል። ለዚህ ነው ተጫዋቾች ከሃገር የመውጣት ዕድሉን ሲያገኙ መመለስ የማይፈልጉት” የሚለው ደግሞ ኬንያ የሚኖረው ከሚሊዮን አብርሓ ነው።
ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ የሃገሪቱን አግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ የኤርትራን መንግሥት አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም።
ትውልደ ኤርትራዊያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የመንግሥት ባለሥልጣን እንደሚሉት ብሔራዊው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ተጫዋቾች ሃገር ጥለው የመጥፋታቸውን ዕድል ለመቀነስ ትውልደ ኤርትራዊያንን ያቀፈ ብሔራዊ ቡድን ለመሥራት ዕቅድ ይዟል።
ለስዊድኑ ትሬሌቦርግ የሚጫወተው ሞሐመድ ሰዒድ በ2019 ለመጀመሪያ ጊዜ ለኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት በእግር ኳስ ሕይወት አንድ አስደሳች ምዕራፍ የተከፈተ መስሎት ነበር።
ነገር ግን ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ከናሚቢያ ጋር በነበረው ግጥሚያ ብቻ ነው። ኤርትራ ራሷን ከማጣሪያው ማግለሏን የሰማው ደግሞ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ነው።
የ32 ዓመቱ ሞሐመድ “እኔ የምንጫወት መስሎኝ ነበር። ሁሉም ተጫዋቾች እንደዛ ነበር የመሰለን” ይላል።
“ባለፈው ወር እርስ በርሳችን ስናወራ ድጋሚ የምንገናኝ መስሎን ነበር። እንደውም በዓለም አቀፉ እረፍት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግና እርስ በርሳቸውን የበለጠ ለመተዋወቅ ነበር ዕቅዳችን። ኤርትራን ወክየ እንደምጫወት ለቤተሰቦቼ ስነግራቸው ነበር። ነገር ግን ጨዋታ እንደሌለ ሰማሁ።”
ሞሐመድ ከአራት ዓመት በፊት ወደ ናሚቢያ አቅንቶ ሃገሩን ወክሎ ሲጫወት ነው የሃገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ችግሮች የተረዳው።
“በጣም ያልተደራጀ ነበር። አሠልጣኙ እኔ ማን እንደሆንኩ እንኳ አያውቁም ነበር። እኔው ራሴን አስተዋውቄ ከአውሮፓ ከመጡት ጥቂት ተጫዋቾች መካከል መሆኔን ማስረዳት ነበረብኝ።”
“አሠልጣኙ ተጫዋቾቹ እነማን እንደሆኑ የማወቅ ኃላፊነት የለበትም?” ሲል ይጠይቃል።
ምንም እንኳ ጉዞው ዝግጅት የጎደለው እንደሆነና ሌሎች ውጣ ውረዶች የነበሩበት እንደነበር የሚያስታውሰው ሞሐመድ ሃገሩን ወክሎ መጫወቱ ግን እጅግ የሚኮራበት ነው።
“በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የኔን ቋንቋ ከሚናገሩ፤ እኔን ከሚመስሉ ሰዎች ጋር ነበርኩ። ይህ ከኔ ልዩ ነው። ደጋፊው ምንም ዓይነት ውጤት ብናመጣ ከጎናችን ነው።”
ሞሐመድ ምንም እንኳ አሁን የኤርትራ እግር ኳስ ወደኃላ ቢቀርም ለውጥ መምጣቱ አይቀርም ብሎ ያስባል።
“ልምድ ያለው ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ነገሮችን መቀየር የሚችል አሠልጣኘ መጥቶ ተጫዋቾችን መቀየር አለበት” ይላል።
“ሁሌም የዓለም አቀፍ እረፍት በመጣ ቁጥር እኛ ዜና መከታተል ሆኗል ሥራችን። በጣም ብዙ ዕድሎች መጥተው ሄደዋል። ጊዜ ማባከን ሰልችቶናል። ተጫዋቾቹ ሁሌም ኤርትራን መወከል ይፈልጋሉ።”












