የአየር ብክለት የኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ አትሌቶችን እንዳይጎዳ የሳይንስ ጥረት

ኬንያዊያን ሯጮች በናይሮቢ ጎዳና

የአየር ብክለት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ወቅት አትሌቶች ራሳቸውን ከዚህ አደጋ ለመከላከል ሳይንስን ተገን ማድረግ ጀምረዋል።

አፍሪካ ውስጥ በስድስት አገራት የአየር ጥራትን የሚከታተሉ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙ ሲሆን፣ አሠልጣኞች እና የሩጫ ውድድር አዘጋጆች ከዚህ ቴክኖሎጂ የሚገኘውን መረጃ መጠቀም ጀምረዋል።

“የአየር ንብረቱ በተበከለ አካባቢ ከሮጥክ አቋም ሊቀንስ ይችላል” ሲል የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ማራቶን አሸናፊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ለቢቢሲ ይናገራል።

“የተበከለ ከተማ ስትሄድ ሳንባህን የሆነ ነገር የተጫነው ያህል ነው የሚሰማህ” ይላል ኪፕቾጌ።

የአየር ንብረት ብክለት በአፍሪካ ብቻ በየዓመቱ ለ1.2 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ምክንያት ነው ይላል የተባበሩት መንግሥታት እና ‘ክሊር ኤር ፈንድ’ የተሰኘው ድርጅት ያወጣት መረጃ። ይህ ማለት የአየር ብክለት በአፍሪካ ቁጥር ሁለት የሞት ምክንያት ነው።

በተለይ ይህ ጉዳይ የሚያሳስባቸው አዘውትረው የሩጫ ልምምድ የሚያደርጉ አትሌቶች ናቸው። ልምምድ የሚያደርጉ ሰዎች ከሌሎች ሲነፃፀር 20 እጥፍ የሚሆን አየር ይስባሉ። በሌላ ቋንቋ 20 እጥፍ የተበከለ አየር ሊስቡ ይችላሉ ማለት ነው።

በደቂቃ እና በሰከንድ ልዩነት ውጤት ለማምጣት ለሚጥሩ አትሌቶች የአየር ብክለት ጉዳይ አሳሳቢ የሚሆነው ለዚህ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የመድኃኒት ላይብረሪ ያደረገው አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው የአየር ብክለት በማራቶን ላይ የሚታይ አቋምን በ1.4 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል።

“ያን ያህል ርቀት አየሩ በተበከለ ከተማ ውስጥ የምትሮጥ ከሆነ አቋምህ ሊዋዥቅ ይችላል” የሚሉት የስቶክሆልም ኢንቫይሮንመንት ተቋሙ ዶ/ር ፊሊፕ ኦሳኖ ናቸው።

ተቋሙ ከተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ አካባቢ ፕሮግራም (ዩኤንኢፒ) ጋር በመተባበር የአየር ብክለት የሚለዩ መሣሪያዎች ተክሏል።

“[የአየር ብክለት] የአተነፋፈስ አቅምን እና የደም ኦክሲጅን መጠንን የሚጎዳ ነው” ይላል።

አደጋ ላይ ያሉ የልምምድ ሥፍራዎች

የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያ
የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት የአፍሪካ ሀገራት የተተከለው የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያ

የአየር ብክለት የሚለዩት መሣሪያዎች በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በካሜሩን፣ በሴኔጋል፣ በታንዛኒያ እና በዛምቢያ በሚገኙ ስታድየሞች እና የመለማመጃ ሥፍራዎች ነው የተተከሉት።

ኢቴን የተሰኘችው የኬንያዋ የአትሌቲክ መንደር ይህ ቴክኖሎጂ ከተተከለባቸው ሥፍራዎች መካከል ናት። በሥፍራው ያሉ አጥኚዎች በዐይን የማይታዩ ነገሮችን ይመረምራሉ።

ኢቴን ባለፉት 20 ዓመታት “በጣም ተቀይራለች” የሚለው ኪፕቾጌ በተለይ ብዙ ነዳጅ የሚጠቀሙና ጭስ የሚለቁ ያረጁ መኪኞች መበርከታቸውን አስተውሏል።

የ39 ዓመቱ አትሌት የራሱ ጫካ ያለው ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ግንዛቤ በማስፋፋት ላይ ይገኛል።

“እኔ ልምምድ የማደርገው ንፁህ ኦክሲጅን ባለበት ጫካ አካባቢ ነው። ጫካውን ጠብቄ ለማቆየት እየጣርኩ ነው። በርካታ ዛፎች እተክላለሁ።”

የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አባል የሆኑት ማክስዌል ንያሙ በኢቴን ያለውን የተፈጥሮ መመናመን “ለስፖርቱ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ አደጋ ነው” ሲሉ ይገልጡታል።

“ጫካው ይሸፍነው የነበረው ቦታ ቀንሷል፤ የብክለት መጠኑ ደግሞ ጨምሯል። ጫካው ከተሽከርካሪዎች የሚወጣውን ካርበን በመያዝ ያግዘን ነበር” ይላሉ።

አሊዩድ ኪፕቾጌ
የምስሉ መግለጫ, ሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ማራቶን ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው አሊዩድ ኪፕቾጌ

ለውጥ ማምጣት

ሯጮች እና አሠልጣኞች ከአዲሱ ቴክኖሎጂ የሚያገኙትን ውጤት ተጠቅመው የልምምድ ጊዜያቸውን እያስተካከሉ ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአየር ብክለት የሚጨምረው ንጋት እና አመሻሽ ላይ ነው።

ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ብክለትን መሸሽ የሚቻል አይደለም።

ባለፈው ጥር ኢቴን አቅራቢያ በምትገኘው ሎቦ ሊደረግ የነበረ ልምምድ ለስምንት ተከታታይ ቀናት የነበረው “ጤናማ አይደለም” በመባሉ ሊሰረዝ ግድ ሆኗል።

“አሁን መፍትሔ ካላበጀንለት በርካታ አትሌቶቻችን የሚለማመዱባቸው ሥፍራዎች አደጋ ላይ ይወድቃሉ” ይላል የኬንያ አትሌቲክስ ኃላፊ ጃክ ቱዌይ።

አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የአየር ብክለት መጠን ሲኖር መረጃውን ለቴክኒካል ቡድን ያቀብላል፤ ቡድኑ ደግሞ ለአሠልጣኞች ይሰጣል።

“ከአንድም ሁለት ጊዜ በላይ በአየር ብክለት ምክንያት የልምምድ ሥፍራ እና ሰዓት ለመቀየት ተገደን እናውቃለን” ይላሉ የአትሌቲክስ አሠልጣኝ እና የአካባቢ ጥበቃ ምሑር የሆኑት በርናርድ ኡማ።

“ጠዋት 2 ሰዓት መጀመር ሲገባን 4፡00 ሰዓት ጀምረን እናውቃለን። ኒያዮ ስታድየም መለማመድ ሲገባን ወደ ካረን [ናይሮቢ የሚገኝ የልምምድ ሥፍራ] ሄደን ልምምድ ሠርተን እናውቃለን።

“ምንም እንኳ አድራሻ መቀያየሩ ለሎጂስቲክስ የማይመች ቢሆንም ለአትሌቶቹ ጤና ስንል እናደርገዋለን።”

የአየር ጥራትን ማሻሻል

ከቴክኖሎጂው የሚገኘው መረጃ የሩጭ ውድድርን ለማዘጋጅትም ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

ባለፈው ዓመት ናይሮቢ የተዘጋጀ የማራቶን ውድድር የአየር ብክለት መጠኑ ከፍ በማለቱ ሊሰረዝ እንደነበር አዘጋጆቹ ይናገራሉ። በሥፍራው የነበሩ መኪኖችን በማራቅ የአየር ጥራቱን ለማሻሻል መሞከራቸውንም ያስረዳሉ።

‘አይኪው ኤር’ የተባለ ድርጅት ያወጣው ዘገባ ‘ቤኖኒ’ የተባለችውን ጆሀንስበርግ የምትገኝ የደቡብ አፍሪካ ከተማ አፍሪካ ውስጥ እጅግ የተበከለ አየር ያለባት የአፍሪካ ከተማ ብሏታል።

ኦጋዱጉ፣ አቡጃ፣ ካይሮ እና ኪንሻሳም በተከማ መስፋፋት እና በኢንዱስትሪ ምክንያት የአየር ብክለት ያለባቸው የአፍሪካ ከተማዎች መሆናቸውን ጥናቱ ይገልጣል።

ዩኤንኢፒ በሌሎች ሥፍራዎችም ቴክኖሎጂውን በመግጠም የተሻለ መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በጥቂት ቀናት ውስጥ በሚጀመረው የፓሪስ ኦሊምፒክ አገራቸውን ወክለው ለመሳተፍ ለሚጥሩ ኬንያዊያን አትሌቶች ይህ መረጃ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው።

የፓሪስ ኦሊምፒክ አዘጋጆች የዘንድሮውን ውድድር “አረንጓዴ እና አስተማማኝ” ለማድረግ የካርቦን ልቀት መጠን ከዚህ ቀደሙ በግማሽ ለመቀነስ ቃል ገብተዋል።