የአትሌቲክስ ፌደሬሽን አመራሮችን ያላግባባው የአትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ጉዳይ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም. ድረስ በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አገራት የሚወክሏቸውን አትሌቶቻች በመምረጥ ይፋ እያደረጉ ይገኛሉ።
በተለይ በኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድር ዝነኛ የሆነችው ኢትዮጵያም ፈረንሳይ በምታስተናግደው የዘንድሮ ኦሊምፒክ ላይ የሚወክሏትን አትሌቶች በቅርቡ ይፋ አድርጋለች።
በውድድሩ ኢትዮጵያን እንዲወክሉ በተካሄደው ከአትሌቶች መረጣ ጋር በተያያዘ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ቅሬታ አቅርባለች።
በዓለም አቀፍ መድረኮች አገሯን በመወከል እና በግሏ በመወዳደር ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ የቻለችው አትሌቷ፤ ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ ወክለው ከሚሳተፉ ስፖርተኞች ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቷ ቅሬታዋን አቅርባለች።
“በ1500 እና በ5 ሺህ ሜትሮች ላይ ትኩረት አድርጌ ነው ስሠራ የቆየሁት። በዚህ ዓመት በ1500 ያሳየሁት አቋም ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም በቤት ውስጥ ውድድር ወርቅ አሸንፌያለሁ። የተሻለ ሰዓትም አስመስግቤያለሁ” የምትለው አትሌት ፍሬወይኒ፣ ከእሷ ያነሰ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች ለኦሊምፒክ እንደተመረጡ ለቢቢሲ ገልጻለች።
በ5 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ በተጠባባቂነት የተያዘችው አትሌቷ “በተለይ በ1500 ሜትር ከአምስት ጊዜ በላይ ያሸነፍኳት አትሌት ለኦሊምፒክ ተመርጣለች። በዚህ ዓመት የተሻለ ሰዓት አለኝ፤ ነገር ግን እሷ ባለፈው ዓመት ያስመዘገበችው ሰዓት ታይቶ ነው የተመረጠችው” ትላለች።
በተመሳሳይ ዘንድሮ በ5 ሺህ ሜትር የተሻለ ሰዓት የእርሷ ሆና ሳለ ባለፈው ዓመት ባስመዘገቡት ‘ሚኒማ’ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንደተመረጡ አክላ ትናገራለች።
“ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን ለመምረጥ ያወጣው መስፈርት ግልጽ አይደለም። በወንዶች ላይ ‘ዘንድሮ ጥሩ የሮጡ’ ተብለው ተመርጠዋል። በሴቶች ላይ ግን የተሻለ ሰዓት እና የተሻለ ብቃት እያለኝ አላዩትም።”
ለዚህ ቅሬታዋ መልስ እና ማብራሪያ ለማግኘት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ ብትጽፍም ከፌደሬሹን አመራሮች በኩል “ተገቢ እና ቀጥተኛ” የምትለውን ምላሽ እንዳላገኘች ትገልጻለች።
“በዚህም ምክንያት ሕዝቡ እንዲያውቀው የቪዲዮ መልዕክት ለማስተላለፍ ተገድጃለሁ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ፍረወይኒ ዓመቱን ሙሉ ባሳየችው አቋም መሠረት “በ1500 ሜትር ተሳታፊ እንዲሁም በ5 ሺህ ሜትር ተጠባባቂ” ሆና እንደምትመረጥ እምነት እንደነበራት ትገልጻለች።
አትሌቷ በዘንድሮው ዓመት በ5ሺህ ሜትር 14 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ የሆነ ሰዓት ማስመዝገቧን አስታውሳ፤ በእርሷ ቦታ ተመርጣለች ያለቻት አትሌት ግን ያላት ሰዓት 14 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ እንደሆነ ትገልጻለች።
“የሚመለከታቸውን ለማናገር ሞከርኩ ግን ላገኛቸው አልቻልኩም። እንዲህ ያለ ያልተጠበቀ ውሳኔ ሲኖር የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነው። ሆኖም ማስተካከያ አድርገው እንደሚያስገቡኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ለቀጣይ ውድድሮች እራሴን በሞራል ማዘጋጀቴን ግን አላቆምም” ብላለች።
የፌዴሬሽኑ ምላሽ
በኦሊምፒክም ሆነ በሌሎች አገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን የመምረጥ ኃላፊነት የተሰጠው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው።
ዘንድሮም አትሌቶቹ የተመረጡበት መንገድም ይህንን ኃላፊነት መሠረት አድርጎ እንደሆነ የሚናገሩት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ገዛኽኝ አበራ “ይሁን እንጂ የተላለፈው ውሳኔ በማናውቀው ምክንያት ተለውጧል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ለፓሪስ ኦሊምፒክ አትሌቶችን ለመምረጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አቋማቸውን ስንከታተል ቆይተናል። በዚህም መሠረት ባለፈው ረቡዕ የመጨረሻ ተመራጮችን ዝርዝር አዘጋጅተናል። በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃም ተወያይተንበታል” ሲሉ መጨረሻ ላይ ደርሰውበት የነበረውን መግባባት አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት በሦስት ውድድሮች ማለትም በ10 ሺህ፣ 5 ሺህ እና 1500 ሜትሮች ለመሳተፍ ጠይቃ የነበረችው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በሁለቱ ብቻ እንድትሳተፍ እና ፍሬወይኒ ደግሞ አንደኛው ላይ አገሯን እንድትወክል መወሰኑን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጽዋል።
ነገር ግን ረቡዕ ሰኔ 26/2016 ዓ.ም. ላይ ይህንን ውሳኔ ይፋ ለማድረግ በሚዘጋጁበት ወቅት በፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ አማካይነት ለሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም. በድንገት ስብሰባ እንደተጠራ ይናገራሉ።
“የአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ በፌዴሬሽኑ አባላት የውስጥ የማኅበራዊ መገናኛ በኩል የደረሰን። ‘የመጨረሻውን የአትሌቶች ስም ዝርዝር ነገ ስለምናሳውቅ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና የኦሊምፒክ ኮሚቴ አባላት እንዲገኙ እናሳውቃለን’ የሚል ጥሪ ነው” ይላሉ አትሌት ገዛኽኝ።

የፎቶው ባለመብት, Eth Embassy Kenya
ሆኖም አትሌቶችን መርጦ የሚልከው አካል ፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚገኘው የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ እና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንጂ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ስላልሆነ እርሳቸውን ጨምሮ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አብዛኞቹ የሥራ አስፈፃሚ አባላት በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እንዳልተገኙ ያስረዳሉ።
“አትሌቶቹን መርጠን ጨርሰን እያለ ነው ሌላ ስብሰባ እና ውሳኔ የተባለው። ስለዚህ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት አልተገኙም። ፕሬዝዳንቷ [ደራርቱ] እና የኦሊምፒክ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የተደረገው ስብሰባ ደግሞ ፍረወይኒን በ5 ሺህ ሜትር ተጠባባዊ አድርጎ ውሳኔ አሳለፈ” ይላሉ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት።
“እኛ አስቀድመን ያሳለፍነው ውሳኔ ፍረወይኒ በ5 ሺህ ሜትር እንድትወዳደር እና ጉዳፍ ደግሞ በሁለቱ እንድትሳተፍ የሚል ነበር። በግለሰቦች የሚፈጸሙ ሥራዎች ናቸው እየተሠሩ ያሉት።”
“አትሌቶችን ከመምረጥ ጀምሮ እስከ ቅደመ መሰናዶ ያለው ሥራ እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚሠራው ፌዴሬሽኑ እንጂ የኦሊምፒክ ኮሚቴን የሚመለከተው አይደለም። ኮሚቴው ከሎጂስቲክስ፣ ከሆቴል ማረፊያ ቦታ እና ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ውጪ ሥልጣን እንደሌለው ሕጋችን ውስጥ አለ” ሲሉም አክለዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ወደ ፈረንሳይ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ የሚያቀኑ አትሌቶች ስም ዝርዝር በፌዴሬሽኑ በኩል ለዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተላከ ሲሆን፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ በ5 ሺህ ሜትር ብቻ ተጠባባቂ ሆና ተካታለች።
“የአትሌቶች ዝርዝር የሚላኩባቸው ቀናት ተጠናቀዋል። ኢትዮጵያን በተለያዩ ውድድሮች የሚወክሉ አትሌቶች ስም ዝርዝርም ለዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተልኳል። አሁን ለአገሪቱ ውጤት የሚታሰብ ከሆነ ቀደም ብለን እንደወሰንነው አትሌት ጉዳፍ በሁለቱም መሮጥ አለባት። ፍሬወይኒ ደግሞ በ5ሺህ መወዳደር ይገባታል” ሲሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ሥራ ወስዷል ብለው የሚናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ የዚህ ጣልቃ ገብነት ውጤት የአትሌቶች አመራረጥ ሂደት ግልጽነት እና ሙያዊነት የጎደለው እንዲሆን አድርጓል ይላሉ።
“የኦሊምፒክ ኮሚቴ በአትሌቶች ምርጫ ላይ መሳተፍ የለበትም። ነገር ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲሠራ የነበረው እንደዚህ ነው። ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ እኛ ኃላፊነታችንን አሳልፈን ስለተሰጠን ብቻ ነው” ሲሉም አክለዋል።
በዚህ ገዳይ ዙሪያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉን እና በተቀየረው የአትሌቶች ምርጫ ውሳኔ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ሌሎች የፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎችን እና የኦሊምፒክ ኮሚቴ አባላትን ቢቢሲ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።












