የዘንድሮውን የአውሮፓ ዋንጫ ማን ያነሳል? የእግር ኳስ ተንታኞች ምን ይላሉ?

ቤሊንግሃም፣ ምባፔ፣ ቫን ዳይክ እና ያማል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውሮፓ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ደርሷል። ማክሰኞ ስፔን ከፈረንሳይ፤ ረቡዕ ደግሞ እንግሊዝ ከኔዘርላንድስ ይገናኛሉ። ለዋንጫ ለማለፍ ይፎካከራሉ።

በአውሮፓውያኑ 2012 ዋንጫውን ያነሳችው ስፔን ለአራተኛ ጊዜ የአውሮፓ ባለድል ለመሆን ቆርጣ ተነስታለች።

ፈረንሳይ ለመጨረሻ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ ያነሳችው ከ24 ዓመታት በፊት ነው። ኔዘርላንድስ ደግሞ በ1988 ነው ባለድል የሆነችው። እንግሊዝ በበኩሏ በወንዶቹ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫን ለማሸነፍ እየጣረች ነው።

ከአራቱ ቡድኖች መካከል ጠንካራ አቋም ላይ ያለው ማነው? ዋንጫውን ማን ሊያነሳ ይችላል?

ስፔን

ስፔናውያን የጀርመን ቡድንን ካሸነፉ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስፔናውያን የጀርመን ቡድንን ካሸነፉ በኋላ

ስፔን ከጀርመን ጋር ስትጫወት ሦስት ዓይነት መንገዶችን አሳይታናለች ይላል ስፔናዊው የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ጉሌም ባላግ።

በክንፍ መስመር ተጫዋቾች፤ ያለክንፍ መስመር ተጨዋቾች፤ ያለ አጥቂ እንዲሁም በ4-4-2 አሰላለፍ አይተናቸዋል ይላል። ይህ ማለት ስፔን ከጀርመን የገጠማትን ፈተና ተወጥታለች ማለት ነው።

ባላግ እንደሚለው እርግጥ ነው ስፔን ልትሸነፍ ትችል ነበር፤ ነገር ግን ማሸነፍ እንደሚቻልም አሳይታለች።

ስፔን፤ ጀርመንን ከመግጠሟ በፊት የነበሩትን አራት ጨዋታዎችን በበላይነት አጠናቃለች። የጀርመን ፈተና ግን ከብዷት ነበር። ቢሆንም ፈተናውን መወጣት ችላለች።

ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ አካላዊ ሙግትም የታየበት ነበር። ከአውሮፓውያን 2016 በኋላ በጣም በርካታ ጥፋቶች የተፈፀሙበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

የስፔን ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያውን ጎል ካስቆጠረ በኋላ ተከላክሎ ለመጫወት ቢሞክርም ጀመርን ጫና ፈጥራ አቻ ሆናለች። ባላግ እንደሚለው ስፔን ወደኋላ አፈግፍጋ መጫወት ሳይሆን እያጠቃች መጫወት ነው ያለባት።

ስፔናዊው ጋዜጠኛ ስፔን የራሷ ሳጥን ውስጥ ተሸሽጋ መጫወት ለአደጋ ያጋልጣታል ብሎ ነው የሚያስበው።

አክሎም ከፈረንሳይ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ስፔን ልክ በምድብ ጨዋታ ወቅት ያሳየችውን ኳስን ተቆጣጥሮ የማጥቃት ሂደት እንደምታሳይ ያምናል። አልፎም በመልሶ ማጥቃት የሚመጣውን የፈረንሳይ ኃይል ለመመከትም መላ እንደሚዘጋጅም ያስባል።

ባላግ እንደሚለው ፈረንሳይ ከስፔን ጋር ያለባትን ጨዋታ ለማሸነፍ ማጥቃት ላይ የተመሠረተ ስልት መከተል አይጠበቀባትም። ፈረንሳይ በመልሶ ማጥቃት ስፔንን ጉድ ልትሠራት እንደምትችል ይጠረጥራል።

ሁለት ቢጫ ያዩ ተጫዋቾች ባይሰለፉም፤ እንዲሁም ፔድሪ በጀርመኑ ጨዋታ ተጎድቶ ቢወጣም፣ ይህ ስፔንን ሊያሳስባት አይገባም የሚለው ባላግ ቡድኑ አንድ ሆኖ መጫወት መቻሉ ክፍተት ይሞላል የሚል እምነት አለው።

ባላግ፤ ስፔን ፈረንሳይን አሸንፋ በፍፃሜው ከእንግሊዝ እንደምትገናኝ ይገምታል። ዋንጫውን ከማንሳት ወደኋላ አትልም ይላል።

እንግሊዝ

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቢቢሲው የእግር ኳስ ፀሐፊ ፊል ማክነልቲ እንግሊዝ በሩብ ፍፃሜው ያሳየችውን ፅናት እንዲሁም የጁድ ቤሊንግሃም እና የቡካዮ ሳካ የግል ብቃት ከምንጊዜውም በላይ የሚያስፈልግበት ሰዓት አሁን ነው ይላል።

የጋሬዝ ሳውዝጌት ቡድን በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ተከላክለው ከሚጫወቱ ቡድኖች ትልቅ ፈተና ገጥሞት ታይቷል። ነገር ግን ኔዘርላንድስ ወደኋላ ተሸሽጎ የሚጫወት ቡድን አይደለም። ምናልባት ሁለቱ ቡድኖች ወደፊት እየገፉ በመሄድ አዝናኝ ጨዋታ ያሳዩን ይሆናል።

እንግሊዝ በግማሽ ፍፃሜው ጨዋታ ተከላካይ መስመሯ ጠንካራ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚገባ ፊል ያምናል። ምክንያቱም ኔዘርላንድስ አደገኛ የሚባሉ ጨራሽ ተጫዋቾች አሏት። የሊቨርፑሉ ኮዲ ጋክፖ በአውሮፓ ዋንጫ መልካም አቋም እያሳየ ይገኛል። ሜምፊስ ዴፓይም ቢሆን አደገኛ የሚባል አጥቂ ነው።

ነገር ግን እንግሊዝ አጥቅታ የምትጫወት ከሆነ ጫና ሲበዛበት መቋቋም የሚከብዳትን ኔዘርላንድስ ልትፈትን ትችላለች ይላል ፊል። የእንግሊዙ አምበል ሃሪ ኬን እና የኔዘርላንድሱ አቻው ቨርጂል ቫን ዳይክ ይፋጠጣሉ።

ኬን ከስዊትዘርላንድ ጋር በነበረው የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ኳስን ከመረብ ለማገናኘት ሲዘገይ ታይቷል። እንደዚያም ሆኖ አጋጣሚውን ካገኘ የመጨረስ አቅሙ የሚታማ ተጫዋች አይደለም።

ምንም እንኳ እንግሊዝ በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ባሳየችው ብቃት ደጋፊዎቿ ተስፋ ቆርጠው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ዋንጫውን ሊያነሱ ይችላሉ ከሚባሉ ቡድኖች ተመድባለች። ከጨዋታ ጨዋታ የበለጠ ጥንካሬ እና በራስ መተማመን እያዳበረች ያለችው እንግሊዝ ታሪክ ልትሠራ ትችላለች።

ፊል አገሩ እንግሊዝ ከ1966 የዓለም ዋንጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ብታነሳ ደስታውን አይችለውም። ነገር ግን ስድስተኛው የስሜት ህዋሴ ስፔን ልታነሳው እንደምትችል ይነግረኛል ይላል።

በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ስፔን የተሻለ ብቃት ይዛ እንደመጣች ፊል ይናገራል። ነገር ግን ከዲዲዬ ዴሾ ቡድን ፈተና ሊገጥማት እንደሚችል ያምናል።

ፊል ማክነቲ የዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ ስፔን ትሆናለች ሲል ይገምታል።

ፈረንሳይ

ኪሊያን ምባፔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪሊያን ምባፔ

ፈረንሳዊው የእግር ኳስ ተንታኝ ጁሊየን ሎረንስ ፈረንሳይ በዘንድሮው ውድድር ጠንካራ ተከላካይ መስመር እንዳላት አሳይታናለች ባይ ነው። ይህ ደግሞ የዋንጫ ውድድርን ለማሸነፍ በጣም አስፈላጊ ነው ብሎ ያስባል።

ነገር ግን እንደሌላው ጊዜ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት ላይ እንደደከመ አይክድም። ይህ ደግሞ የጎል ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ እንዳደረጋቸው ያምናል። ለወትሮው በተቃራኒ ቡድን ሳጥን ሁከት በመፍጠር የሚታወቁት ፈረንሳዮች ዘንድሮ ይህ ክህሎታቸውን የተጠነቁ ይመስላሉ።

ልክ እንደ ክርስትያኖ ሮናልዶ ሁሉ ኪሊያን ምባፔም ብዙ አመርቂ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ አይደለም።

ከኦስትሪያ ጋር በነበረው ጨዋታ አፍንጫውን የተሰበረው ምባፔ መከላከያ የፊት ጭምብል አድርጎ ለመጫወት ተገዷል። በዚህ ጨዋታ ምባፔ ጎልቶ ለመውጣት ሞክሮ ነበር።

የቀድሞው የፒኤስጂ ተጫዋች ወደ አውሮፓ ዋንጫ ከመምጣቱ በፊት ጉዳት አጋጥሞት ነበር። ለዚህ ነው ሙሉ አቋሙ ላይ አልነበረም የምለው ይላል ሎረንስ።

ሎረንስ የስፔኑ ፔድሪ መጎዳቱ የመሐል ሥፍራውን ያሳሳዋል ብሎ ያስባል። ስፔን እና ፈረንሳይ የሚያደርጉት ጨዋታ የአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ፉክክር የሚታይበት እንደሆነ ተናግሮ ይህን ያሸነፈ ጨዋታውን ሊረታ እንደሚችል ይገምታል።

የስፔን ብሔራዊ ቡድንን ሊፈትኑ ከሚችሉ ቡድኖች መካከል አንደኛው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ነው ይላል።

ለበርካታ ዓመታት በስፔን ክለቦች የተጫወተው አንትዋን ግሪዝማን እና ወደ ስፔኑ ሪያል ማድሪድ ያቀናው ኪሊያን ምባፔ ለዚህ ፍልሚያ እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ይናገራል።

ሎረንስ በፍፃሜው ፈረንሳይ ከእንግሊዝ እንደሚገናኙ ይገምታል። በፍፃሜው ጨዋታ ኪሊያን ምባፔ ከዚህ ቀደም የሚታወቅበትን ብቃት አሳይቶ ዋንጫውን ወደ አገሩ እንደሚወስድ ያምናል።

ኔዘርላንድስ

ዋውት ዌግሆርስት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዋውት ዌግሆርስት

ደቹ የእግር ኳስ ፀሐፊ ጃስፐር ሎንግብሮክ አገሩ ኔዘርላንድስ ከቱርክ ጋር በነበራት ጨዋታ አንደኛው ዕቅዷ ቢከሽፍ ሁለተኛ ዕቅድ ማዘጋጀት እንደምትችል ያሳየችበት ነው ይላል።

ኔዘርላንድስ ከቱርክ ባደረግችው የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያ ዋውት ዌግሆርስትን እንደ አጥቂ፤ ሜምፊስ ዴፓይን ደግሞ እንደ 10 ቁጥር አጥቂ አድርጋ በመጫወት ድል ተቀዳጅታለች።

እንግሊዝ በበኩሏ ከኔዘርላድስ ጋር በነበራት ፍልሚያ በአምስት ተከላካዮች ነው ወደ ሜዳ የገባችው። ጃስፐር፤ ኔዘርላንድስ ውጤት ማምጣት ካለባት እንደዚህ ተከላክላ ልትጫወት ይገባል የሚል ምክር ያስቀምጣል።

ጋዜጠኛው እንደሚለው ኔዘርላንድስ አጥቅታ ለመጫወት የማንቂያ ደወል ያስፈልጋታል። ከኦስትሪያ እና ከሮማኒያ ጋር በነበረው ጨዋታ የተስተዋለው ይህ ነው።

በሩብ ፍፃሜውም ቢሆን በቱርክ ጎል ከተቆጠረባት በኋላ ነው የመልስ ምት የሰጠችው። እንግሊዝም ሆነ ኔዘርላንድስ አቅም ያላቸው ተጨዋቾች ቢኖሯቸውም እስካሁን የሚገባውን አላሳዩንም ይላል ጃስፐር።

ጃስፐር አገሩ ኔዘርላንድስ ዋንጫውን ብታነሳ ደስ እንደሚል ቢናገርም የዘንድሮው ባለድል ስፔን እንደምትሆን ያምናል።