በአውሮፓ ዋንጫ መድረክ ደምቀው የታዩት ትውልደ አፍሪካውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያን 1990ዎቹ እና 2 ሺዎቹ የነበረው ስደት የዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ከምንጊዜውም በላይ የደመቀ እና የባሕል ስብጥር የበዛበት እንዲሆን አድርጓል።
የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ሩብ ፍፃሜ ላይ ደርሷል። ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀሉትም ይሁኑ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚሸጋገሩ ብሔራዊ ቡድኖች ውጤታማ ከሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ ትውልደ አፍሪካዊ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል።
ኬቪን ዳንሶ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
የ25 ዓመቱ ተከላካይ ለትውልድ አገሩ ኦስትሪያ መከታ ነበር። ኦስትሪያ ወደ ዙር 16 ብትደርስም በቱርክ ተሸንፋ ከውድድር ውጪ ሆናለች።
ዳንሶ ምንም እንኳ ኦስትሪያ ይወለድ እንጂ ከ6 ዓመቱ ጀምሮ ከጋናውያን ቤተሰቦቹ ጋር የኖረው እንግሊዝ ውስጥ ነው። የእግር ኳስ ክህሎቱን ያካበተውም በሬዲንግ እና ኤምኬ ዶንስ አካዳሚዎች ነው።
ለፈረንሳይ ሊግ 1 ክለብ ላንስ የሚጫወተው ዳንሶ የሦስት አገራት አደራ ቢኖርበትም ሁሌም የቤተሰቦቹን አገር ግን አይረሳም።
በአውሮፓውያኑ 2021 ጋናን የጎበኘው ዳንሶ “ኦስትሪያን ቤቴ፤ ጋናን ደግሞ የአያቶቼ መገኛ ብዬ መጥራት በመቻሌ እጅግ ዕድለኛ ነኝ” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
“ባሕሉ፣ ምግቡ፣ ሕዝቡ፣ ብቻ ሁሉም የጋና የሆነ ሁሉ ለእኔ መሠረቴ ነው። ብሔራዊ ቡድኑን እመለከታለሁ፤ ድጋፌን እገልጣለሁ።”
ሌላኛው የኦስትሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነው ዴቪድ አላባ ቤተሰቦች የናይጄሪያ ሰዎች ናቸው። ከዳንሶ ጋር የማያስማማቸው አንድ ነገር የጋና ወይስ የናይጄሪያ ምግብ ነው ጣፋጭ የሚለው ነው።
“እሱ [አላባ] ጋናን ያውቃታል። ምርጥ ‘ጆሎፍ’ እንዳለንም ያውቃል። ነገር ግን ሁሌም እንበሻሸቃለን።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስፔን ዕንቁዎች
ስፔን በ2000ዎቹ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ መድረክ የበላይነቷን ያሳየችው ረጋ ብሎ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ነበር።
ነገር ግን አሁን ይህ ተቀይሯል። የስፔንን መብረቃዊ እግር ኳስ በክንፍ በኩል እየመሩ ያሉት ደግሞ ወጣቶቹ ኒኮ ዊሊያምስ እና ላሚን ያማል ላ ሮሀ ናቸው።
ኒኮ ዊሊያምስ ጋናዊ ደም ያለው ሲሆን፣ ላሚን ያማል ደግሞ ከሞሮኮ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ የሚመዘዝ የዘር ግንድ አለው።
የቦአቴንግ ወንድማማቾችን እናስታውሳቸዋለን። ዤሮም ቦአቴንግ ለጋና ኬቪን ፕሪንስ ቦአቴንግ ደግሞ ለጋና ነበር የሚጫወቱት። የኒኮ ታላቅ ወንድም ኢናኪ ዊሊያምስ ለጋና ብሔራዊ ቡድን ነው የሚጫወተው።
ጋናዊያኑ ጥንዶች የተሻለ ኑሮን ፍለጋ የሰሃራ በረሀን አቋርጠው ስፔን መኖር ከጀመሩ በኋላ ነው ኒኮ እና ኢናኪን የወለዱት። ኢናኮ ከኒኮ በተለየ የአራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ለሆነችው ጋና መጫወትን መርጧል።
ኢናኪ ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር እያደረገ ያለው ጉዞ ይህን ያህል ስኬታማ ባይሆንም፣ ኒኮ ግን ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር የተሳካ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል።
በዙር 16 አገሩ ስፔን ጆርጂያን 4-1 ስትረታ የመጀመሪያ የአውሮፓ ዋንጫ ጎሉን ያስቆጠረው ኒኮ ከዚህ ጨዋታ በፊት ያሳየው ብቃት የወደፊት የቡድኑ ተስፋ መሆኑን ያስመሰከረ ነው። በተለይ ስፔን ጣሊያንን 1-0 ስታሸንፍ ጎልቶ መውጣት ችሏል።
“ምንም እንኳ የተለያዩ አገራትን ወክለን ብንጫወትም ሁሌም እንደ አርአያ የምመለከተው እሱን [ኢናኪ] ነው” ሲል ኒኮ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ይናገራል።
“በ2022 የዓለም ዋንጫ ሁለታችንም የቤተሰባችንን ታሪክ የሚወክሉ አገራትን ወክለንም መጫወታችን በጣም አስደናቂ ነበር። ለእኛም ሆነ ለወላጆቻችን አኩሪ ወቅት ነበር።”
ያማል ኳስን ሲያናግር ማየት ያስደስታል። ገና በዚህ ዕድሜው አስደናቂ ተጫዋች መሆኑ ብዙዎችን እያስገረመ ነው። በተለይ የውሳኔ ብቃቱን ብዙዎች ያወድሱለታል።
የባርሴሎናው ታዳጊ በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ እያሳየ ያለውን ድንቅ ብቃት በ16 ዓመታቸው ማሳካት የቻሉ በጣም ጥቂት ናቸው።
ሞሮኮ ልክ እንደ አሽራፍ ሐኪሚ እና ብራሒም ዲያዝ ሁሉ ያማልን ከስፔን ነጥቃ የራሷ ለማድረግ ያደረገችው ጥረት አልተሳካላትም። ይህ ደግሞ ለስፔን መልካም ዜና ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጀርመኑ ‘ባምቢ’
የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ አዘጋጅ አገር ጀመርን ከስፔን ቀጥሎ ጠንካራ ቡድን የያዘች እየተባለች ነው። ከዴንማርክ የገጠማትን ፈተና አልፋ ወደ ሩብ ፍፃሜው የተሸጋገረችው ጀርመን ለዋንጫው ግምት ከተሰጣቸው መካከል ናት።
ምንም እንኳ ካይ ሀቨርትዝን አጥቂ አድርጎ መጠቀም እንዲሁም ፍሎሪያን ቪርትዝን ክንፍ ላይ ማሰለፍ አዋጭ አይደለም የሚሉ ትችቶች ቢሰሙም ወጣቱ ጃማል ሙሲያላ የጀመርን ተስፋ መሆኑን አስመስክሯል።
የ21 ዓመቱ ጃማል ሙሲያላ ገና ታዳጊ ሳለ ነው በጀመርን እና በእንግሊዝ መካከል ጠብ እንዲጫር መንስኤ የሆነው። ሙሲያላ ጥምር ዜግነት ባላቸው አባቱ ምክንያት ከእንግሊዝ እና ከጀመርን አልፎ ለናይጄሪያም መሰለፍ ይችል ነበር።
ሙሲያላ በቅርቡ ባደረገው ቃለ ምልልስ ለናይጄሪያ ባሕል ያለውን አመለካከት አጋርቷል። “እንግሊዝ ሳለሁ ገና በልጅነቴ አባቴ ሁሌም ፉፉ እየሠራ ያበላኝ ነበር” ሲል ተናግሯል።
የትኛውን ብሔራዊ ቡድን ወክዬ ልጫወት የሚለው ውሳኔ ቀላል እንዳልነበረ ሙሲያላ ይናገራል።
“ከናይጄሪያም ሆነ ከጀመርን ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ንግግር አድርጊያለሁ። ያው ውሳኔው የእኔ እንደሆነ እና የትኛው ይመቸኛል የሚለው ሐሳብ መሠረት ያደረገ እንደሆነ አውቃለሁ። ለዚህ ነው ጀመርንን የመረጥኩት” ይላል።
ልጅ ሳለ “ባምቢ” በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ሙሲያላ ኳስን ይዞ ክፍተት እየፈጠረ መጫወት የመቻል ብቃቱ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን የተመቸ ሆኗል። የጁሊያን ናግልስማን ቡድን ዋንጫውን ማንሳት ከቻለ የሙሲያላ ሚና ጎልቶ እንደሚወጣ እሙን ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስዊትዘርላንዱ ንዶዬ
ዳን ንዶዬ ከ12 ወራት በፊት በወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ለነበረችው ሴኔጋል ሊጫወት እንደሚችል ነበር የሚያስበው።
“ለእኔ ሴኔጋል ማለት ሁሌም የአፍሪካ ምርጧ ብሔራዊ ቡድን ናት” የሚለው ንዶዬ የወላጆቹ አገር ሴኔጋል በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ባሳየችው ብቃት ይኮራል።
በጣሊያን ሴሪ አ ከቦሎኛ ጋር ድንቅ የውድድር ዘመን ያሳለፈው ንዶዬ በባሕል ስብጥር ለምትኮራው ስዊትዘርላንድ መመኪያ ሆኗል።
ተጠባባቂ በረኛው ያን ምቮጎ፣ ተከላካዩ ማኑዌል አካንጂ፣ አማካዩ ዴኒስ ዛካራይ እና አጥቂዎቹ ብሪል ኢምቦሎ፣ ክዋድዎ ዱዋህ እና ዘኪ አምዱኒ አፍሪካዊ የዘር ግንድ አላቸው።
ዛሬ ቅዳሜ በሩብ ፍፃሜው እንግሊዝን የምትገጥመው ስዊትዘርላንድ የጀመርኑ የአውሮፓ ዋንጫ ያልተጠበቀች ነገር ግን አስደናቂ ግስጋሴ እያሳየች ያለች ሆናለች።
በምድብ ጨዋታው አዘጋጇ ጀርመንን አስጨንቃ አቻ ስትለያይ፤ በዙር 16 ደግሞ ጣልያንን 2 ለምንም በመርታታ ከውድድር ውጪ አድርጋታለች።
ሦስቱ አናብስት ከስዊትዘርላንድ ከባድ ፈተና እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል።












