የቱርክ ያልተጠበቀ ድል፡ የቱርኩ ግብ ጠባቂ ያዳናት ኳስ በዩሮ ታሪክ አስደናቂዋ ተባለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቱርክ ከ ኦስትሪያ ባደረጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የቱርኩ ግብ ጠባቂ የቡድኑን አሸናፊነት ያረጋገጠችውን አደገኛ ኳስ ያዳነበት ሁኔታ በዩሮ ታሪክ አስደናቂው እየተባለ ነው።
ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 25/2016 ዓ.ም. በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ቱርክ እና ኦስትሪያ ባደረጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ቱርክ ሳትጠበቅ ኦስትሪያን 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ከቱርክ አስደናቂ ድል በላይ መነጋገሪያ የሆነው የቱርኩ ግብ ጠባቂ መርት ጉኖክ በባከነ ሰዓት ያዳናት ኳስ ነች።
ቱርክ 2ለ1 እየመራች በተጨማሪ ደቂቃዎች ኦስትሪያ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥራ እየተጫወተች ነበር።
በ94ኛው ደቂቃ ላይ የተሻማውን ኳስ የኦስትሪያው አጥቂ ኳሷን በጭንቅላት ከመሬት አጋጭቶ ከግብ ጠባቂው በስተቀኝ በኩል አርቆ ወደ ግብ ላካላት።
በዚያ ቅጽበት በስታዲየሙ የነበሩ ደጋፊዎች ኳስ ከመረበ ይገናኛል ብለው ሲጠበቁ፤የቱርኩ ግብ ጠባቂ በአስደናቂ ሁኔታ ወደ ቀኝ ተወርውሮ በጣቶቹ ወደ መረብ ልትሄድ የነበረችውን ኳስ ወደ ውጪ አውጥቷል።
በቢቢሲ ራዲዮ ግጥሚያውን እያሰራጨ የነበረው የእግር ኳስ ተንታኙ ክሪስ ሱተን ግብ ጠባቂው ኳሷን ያዳነበትን ሁኔታ የሚገልጽበት ቃላት አጥረውት “ያዳነበት ሁኔታ ጨርሶ ሊታመን የማይችል ነው” ብሏል።
የቀድሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ የነበረው ማቲው አፕሰን ደግሞ “የማይታመን ነው፤ግብ ጠባቂው ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ የተወረወረበት ሁኔታ የማይታመን ነው” ብሏል።
ጉኖክ ያዳናት ኳስ በዓለም ዋንጫ ታሪክ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረው ጎርደን ባንክስ ካዳናት ኳስ ጋር እየተነጻጸረች ነው።
ባንክስ በ1970 የዓለም ዋንጫ የብራዚሉ ፔሌ በጭንቅላቱ ከመሬት አላግቶ ወደ ግብ የላካትን ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ ተስፈንጥሮ ውጪ አውጥቷታል። ግብ ጠባቂው ኳሷን ያዳነበት ሁኔታ በዓለም ዋንጫ ታሪክ አስደናቂዋ ተብላ ተመዝግባለች።
ከትናንት ምሽቱ ጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የኦስትሪያው አሠልጣኝ ራልፍ ራግኒክ የቱርኩ ግብ ጠባቂ ተግባርን ከባንክስ ጋር አነጻጽረዋል።
“የአቻነት ግብ ማስቆጠር የምንችልበት ዕድል ነበር፤ ይሁን እንጂ ግብ ጠባቂያቸው ጎርደን ባንክስ መሆኑ አክብዶብናል” ብለዋል።
አሠልጣኝ ራግኒክ ቡድናቸው የአቻነት ግብ ማስቆጠር ቢችል ኖሮ በተጨማሪ ሰዓት ኦስትሪያ የማሸነፍ ዕድል ይኖራት ነበር ብለዋል።
በትናንት ምሽቱ ጨዋታ ለቱርክ ብሔራዊ ቡድን ሁለቱንም የማሸነፊያ ጎሎች ያስቆጠረው ተከላካዩ ሜሪህ ዴሚራለ ግብ ጠባቂያቸው ኳሷን ያዳነበትን ሁኔታ ሲገልጽ፤ “የተመለከትኩትን ማመን ተስኖኝ ነበር። ምናልባት እስካሁን ካየኋቸው ምርጥ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን የማዳን ብቃቶች ይህ አንዱ ሊሆን ይችላል” ብሏል።
ቱርክ እና ኦስትሪያ ያደረጉት የመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ነበር። በሩብ ፍጻሜው የፊታችን አርብ ሰኔ 28/2016 ዓ.ም. ስፔን ከ ጀርመን እንዲሁም ፖርቹጋል ከ ፈረንሳይ ይገናኛሉ።
ቅዳሜ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም. ደግሞ እንግሊዝ ከስዊትዘርላንድ እንዲሁም ኔዘርላንድስ ከ ቱርክ ይገናኛሉ።












