በስደተኞች ላይ ጠንካራ አቋም ያላቸው የዩኬው ፖለቲከኛ ናይጀል ፋራጅ ማን ናቸው?

ናይጀል ፋራጅ

ናይጀል ፋራጅ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ የሚታወቁት የአውሮፓን ኅብረት እና ጥምረት በመተቸት ነው።

የዩኬ የነጻነት ፓርቲ መሪ በነበሩበት ወቅትም ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ኅብረት አባልነት እንድትወጣ ዘመቻ አካሂደዋል። ከዚያም የብሬግዚት ፓርቲ መሪ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የሪፎርም ዩኬ ፓርቲ መሪ ናቸው።

በሥራ ሕይወታቸውም በፖለቲካው፣ በሚዲያው እና በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራርነት ሲንቀሳቀሱ ነው የቆዩት።

ፋራጅ የተወለዱት በደቡባዊ ምሥራቅ ዩኬ በምትገኘው ኬንት ግዛት ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በደቡብ ለንደን በሚገኘው ዱልዊች ኮሌጅ ተከታትለዋል።

አብረዋቸው የተማሩ አቻዎቻቸው ፋራጅ በሚናገሩት አወዛጋቢ ንግግሮች ተማሪዎች እና መምህራንን በማስቆጣት የሚታወቁ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

ፋራጅ ዕድሜያቸው 18 ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲ ላለመግባት ወስነው እአአ በ1982 በለንደን የብረታ ብረት ኢንደስትሪ ውስጥ ነጋዴ ሆኑ።

የፋራጅ የፖለቲካ ጉዞ

ፋራጅ የወግ አጥባቂን ፓርቲ የተቀላቀሉት እአአ 1978 ነበር።

ሆኖም ዩናይትድ ኪንግደም በ1992 የአውሮፓ አገራትን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክረውን የማስትሪች ውልን ከፈረመች በኋላ ከፓርቲው ለቀቁ።

በኔዘርላንድስ ማስትሪክች ከተማ የተፈረመው ውል የአውሮፓ አገራትን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በሕግ የሚያስተሳስር እንዲሁም አንድ የመገበያያ ገንዘብ እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው።

ፋራጅ ፓርቲውን ከለቀቁ በኋላ ያኔ ትንሽ አባላት የነበሩት የዩኬ የነጻነት ፓርቲ (ዩኬአይፒ) መሥራች አባል የነበሩ ሲሆን፣ በ1994 በደቡባዊ ኢንግላንድ ኢስተሊን በተደረገው የማሟያ ምርጫ የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ቢወዳደሩም ሳይሳካላቸው ቀረ።

ከዚያም በ1999 ለአውሮፓ ምክር ቤት የደቡብ ኢንግላንድ ተወካይ ሆነው ተመረጡ። እስከ 2020 ድረስም እዚያው ቆዩ።

ፋራጅ ይበልጥ የታወቁት በ2006 ለመጀመሪያ ጊዜ የዩኬ የነጻነት ፓርቲ መሪ ከሆኑ በኋላ ነበር።

በ2009 በተደረገው እና ፓርቲያቸው ከሌበር እና ሊብ ዴምስ በላይ ድምጽ ባገኘበት የአውሮፓ ምርጫ የፓርላማ መቀመጫ አገኙ።

በ2016 በተካሄደው ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት እንድትወጣ ባደረገው የብሬግዚት ሕዝበ ውሳኔ ላይ የመሪነት ሚና ነበራቸው። ሆኖም ዩኬ ከአውሮፓ ሕብረት አባልነት እንድትወጣ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ከዩኬ የነጻነት ፓርቲ (ዩኬአይፒ) ለቀቁ።

ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ድምጽ ከሰጠች በኋላ፤ ነገር ግን መውጣቷ በይፋ ከመታወጁ ፊት በሚያዝያ 2019 ፋራጅ ብሬግዚት ፓርቲን መሠረቱ።

ከዚያም ዩኬ በይፋ ከአውሮፓ ኅብረት አባልነቷ ከወጣች በኋላ የፓርቲያቸውን ስም ወደ ‘ሪፎርም ዩኬ’ ለወጡት። በ2021 ከፖለቲካ መሪነታቸው ገለል ብለው በወቅቱ በተቋቋመው 'ጂቢ ኒውስ' የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ሆኑ።

የዩኬ ጠቅላላ ምርጫ ዘመቻ እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስም ለታችኛው ምክር ቤት አባልነት ለመመረጥ እንደማይወዳደሩ ተናግረው ነበር።

ሆኖም እአአ ሰኔ 3 ላይ በባሕር ዳርቻዋ ክላክተን ከተማ ሪፎረም ዩኬን ወክለው እንደሚወዳደሩ በማሳወቅ በድጋሚ የፓርቲ መሪነታቸውን እንደሚረከቡ ገልጸዋል።

ፋራጅ ለማሳካት ቃል የገቡት ምንድን ነው?

ሪፎርም ዩኬ (ዩናይትድ ኪንግደም) በምርጫው ዕድል ከቀናው አሳካቸዋለሁ ካላቸው ፖሊሲዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • ኢሚግሬሽን ፡ አላስፈላጊ ስደትን ማስቆም ወይም 'ዜሮ ኢምግሬሽን' ማድረግ፣ የውጭ አገር ወንጀለኞችን ወዲያውኑ ወደ አገራቸው መመለስ እና በሕገ ወጥ መንገድ በትንንሽ ጀልባዎች ወደ አገሪቷ የሚደረግ ስደትን ማስቆም፣
  • የውጭ ጉዳይ፡ ከብሬግዚት በኋላ የታሸጉ ምግቦችን፣ የአበባ ምርቶችን እና የእንስሳት ምግቦችን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ከታላቋ ብሪታኒያ ወደ ሰሜን አየርላንድ እንዲገቡ የሚያስችለውን እና በዩኬ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል የተደረሰውን ሕጋዊ ስምምነት [Windsor Framework] መሻር፣ ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት መውጣት እንዲሁም እርዳታን 50 በመቶ መቀነስ፣
  • ታክስ እና ምጣኔ ሀብት፡ የንግድ ግብርን ወደ 100 ሺህ ፓውንድ፣ የገቢ ግብርን ደግሞ ወደ 20 ሺህ ፓውንድ ከፍ ማድረግ፣ ከ2 ሚሊየን ፓውንድ በታች ዋጋ ባላቸው ላይ የውርስ ንብረት ታክስን ማንሳት፣ አላስፈላጊ ሕጎችን ማስወገድ እና የታክስ ሥርዓቱን ማቅለል፣
  • ወንጀል እና ፍትሕ ፡ የፖሊሶችን ቁጥር መጨመር፣ ዘረኛ የፖሊስ ሥርዓትን ማስቆም፣ 10 ሺህ አዳዲስ እስር ቤቶችን መገንባት፣

ምንም እንኳ የሕዝብ አስተያየቶች ሁልጊዜ 'ትክክል ባይሆኑም' በዩኬ ባለፉት 12 ወራት በተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት ፋራጅ የሚመሩት 'ሪፎርም ዩኬ' ፓርቲ 16 በመቶ የሕዝብ አስተያየት በማግኘት በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሌበር ፓርቲ ደግሞ ከ40 በመቶ በላይ ድምጽ ያገኘ ሲሆን፣ ወግ አጥባቂው ፓርቲ ማግኘት የቻለው 19 በመቶ ብቻ ነው።

ሪፎርም ዩኬ ያለው ድጋፍ በአገሪቷ ቢስፋፋም፣ ድጋፉን ወደ ፓርላማ ወንበር ለመቀየር ከባድ ሊሆንበት እንደሚችል ይታሰባል።

በዩኬ አጠቃላይ ምርጫ ሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም. ይካሄዳል።

በአገሪቱ የፖለቲካ የሥልጣን ዘመን በአምስት ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ወግ አጥባቂው ፓርቲ የመጨረሻውን ምርጫ ያሸነፈው በ2019 ታኅሣሥ ወር ላይ በመሆኑ በሕጉ መሠረት ቀጣዩ ምርጫ መካሄድ የነበረበት ጥር 2025 ነበር።

ሆኖም ይጠበቅ ከነበረው ጊዜ በወራት ቀድሞ ከቀናት በኋላ ጠቅላላ ምርጫው ይካሄዳል።

የዩኬ ፓርላማ 650 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን መራጮች በታችኛው ምክር ቤት ይወክለናል የሚሉትን አንድ የፓርላማ አባል ይመርጣሉ።

አብዛኞቹ ተመራጮች የፖለቲካ ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩ ሲሆን፣ የተወሰኑ ደግሞ በግላቸው የሚወዳደሩ ናቸው።