በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ምን ያህል ስደተኞች ይገባሉ? ከየትኞቹ አገራት የመጡ ናቸው?

በጀልባ የሚያቋርጡ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ዕቅዱ በትናንሽ ጀልባ አቋርጠው ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ይገታል የሚል እምነት ይዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ እንደ ቁልፍ ጉዳይ የያዙት የሩዋንዳ ረቂቅ ሕግ ከረጅም ወራት ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ ውዝግብ በኋላ በፓርላማው ጸድቋል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት የአትላንቲክ ውቅያኖስ አካል በሆነው እና ደቡባዊ እንግሊዝን ከሰሜን ፈረንሳይ በሚለየው ዘ እንግሊሽ (ዘ ቻናል) የባሕር ወሽመጥ በትናንሽ ጀልባ አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞችን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም አቅደዋል።

በትናንንሽ ጀልባዎች ወደ ዩኬ ምን ያህል ሰዎች ይገባሉ?

ከጥቂት ቀናት በፊት በተገኘ መረጃ መሠረት ከጥር ወር ጀምሮ ባለው ጊዜ ዘ ቻናል ወሽመጥን አቋርጠው ወደ ዩናይትድ ኪምግደም የገቡ ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ 265 ነው።

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በሩብ ገደማ ጨምሯል።

የአውሮፓውያኑ ያለፈ ዓመት አሃዝን በምናይበት ወቅት በአጠቃላይ በትናንሽ ጀልባዎች በባሕር ወሽመጡ በኩል ወደ አገሪቱ የገቡ ሰዎች 29 ሺህ 437 ነው።

መረጃ መሰብሰብ ከተጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው በ2022 አሃዙ 45 ሺህ 755 በደረሰበት ወቅት ነው።

ከ2018 ጀምሮ 120 ሺህ ሰዎች በኢንግሊሽ ቻናል በኩል ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብተዋል።

ስደተኞቹ ከየትኞቹ አገራት የመጡ ናቸው?

ያለፈውን የአውሮፓውያኑን ሩብ ዓመት ሲታይ 40 በመቶ የሚሆኑት የመጡት ከቬትናም እና ከአፍጋኒስታን ነው።

በዚህም ወቅት 1 ሺህ 266 ቬትናማውያን እና 1 ሺህ 216 አፍጋኒስታውያን የባሕር ወሽመጡን በጀልባዎች አቋርጠው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብተዋል።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት አፍጋኒስታውያን በአንደኛ ደረጃ የተቀመጡ ሲሆን፣ በትናንሽ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡትን አንድ አምስተኛውን ይሸፍናሉ።

በመቀጠል ኢራናውያን 13 በመቶ፣ ቱርካውያን 11 በመቶ እና ኤርትራውያን 9 በመቶውን ድርሻ በመያዝ ይከተላሉ። ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከአንድ እስከ አምስተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ አልተጠቀሱም።

በትናንሽ ጀልባዎች አቆራርጦ ወደ ዩኬ መግባት ቀላል አይደለም፤ በርካቶች በውሃ ተበልተዋል። እስከ አውሮፓውያኑ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 72 ስደተኞች ባሕሩ ውስጥ ሰምጠው እንደሞቱ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ፍልሰተኞች ድርጅት አስታውቋል።

ምን ያህል ሰዎች በዩኬ ጥገኝነት ጠይቀዋል?

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 84 ሺህ ሰዎች በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በቋሚነት ለመኖር ጥገኝነት ጠይቀዋል።

በአውሮፓውያኑ 2022 ጥገኝነት የጠየቁ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በታች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩኬ የገቡት 45 በመቶ ናቸው።

የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው በአውሮፓውያኑ 2002 ሲሆን፣ 103 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ናቸው። አብዛኞቹም በአፍጋኒስታን፣ በሶማሊያ እና በኢራቅ የተከሰቱ ጦርነቶችን በመሸሽ ወደ አገሪቱ ገብተዋል።

ከዚያም ቀጥሎ ባሉት ዓመታት የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ያሽቆለቆለ ሲሆን፣ በ20 ዓመታት ውስጥ ትንሹ የተባለው 22 ሺህ 600 የጥገኝነት ጠያቂዎች የተመዘገቡት በአውሮፓውያኑ 2010 ነው።

ሆኖም በዚያው አልቀጠለም፣ ከ2010 በኋላ ባሉት ጊዜያት እንደገና ያንሰራራ ሲሆን፣ ለዚህ መንስኤው በሶሪያ የተቀሰቀሰው ጦርነትን የሸሹ ስደተኞች መጉረፋቸውን ነው።

በአብዛኞቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች ከየት አገር ቸው?

በባለፈው ዓመት በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት የጠየቁ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት አፍጋኒስታውያን ሲሆኑ፣ ቁጥራቸውም 9 ሺህ 307 ነው።

በተከታይነት ደግሞ 7 ሺህ 400 የሚሆኑ ከኢራን፣ ከፓኪስታን፣ ከሕንድ እና ከባንግላዴሽ ናቸው።

ከሁለት ዓመት በፊት ከፍተኛውን ቁጥር ይዘው የነበሩት አልባኒያውያን ሲሆኑ፣ በዚያም ወቅት 17 ሺህ 300 አልባኒያውያን ስደተኞች ጥገኝነት ጠይቀዋል። ከእነዚህ ጥገኝነት ጠያቂዎች 73 በመቶዎቹ ወደ ዩኬ የደረሱት በትናንንሽ ጀልባዎች ነው።

የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ወደ ዩኬ የገቡ ዩክሬናውያን ስደተኞች በእነዚህ መረጃዎች አልተካተቱም። የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ባዘጋጀላቸው ሕጋዊ መንገዶች ተጠቅመው ለገቡ 255 ሺህ 900 ዩክሬናውን ስደተኞች ቪዛ ተሰጥቷል።

ለተወሰኑ የአፍጋኒስታን እና የሆንግ ኮንግ ስደተኞች መንግሥት የሚያመቻችላቸው ፕሮግራሞችም አሉ።

ምን ያህል ጥገኝነት ጠያቂዎች በሂደት ላይ ናቸው?

አንዳንድ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸው እስኪታይ እንዲሁም ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ ወራትን ወይም ዓመታትን ሊጠብቁ ይችላል።

በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጥያቄ ላይ በተፈጠረው መዘግየት ምክንያት 128 ሺህ ስደተኞች ጥያቄያቸው ምላሽ አላገኘም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የእነዚህን ጥያቄዎች ሂደት ለማፋጠን እና የዘገዩ ጥያቄዎች ምላሾችን በ2023 መጨረሻ ላይ ለመቋጨት ቃል ገብተው ነበር።

ነገር ግን በዚያኑ ወቅትም 4 ሺህ 500 “ውስብስብ የተባሉ ሂደቶች” ውሳኔያቸውን እስከ ታኅሣሥ ድረስ ለማግኘት እየተጠባበቁ ነበር። በቅርቡ ደግሞ በተገኘው መረጃ መሠረት ከእነዚህ ሂደቶች ውስጥ 2 ሺህ 377 የሚሆኑት የመጀመሪያ ውሳኔ እየተጠባበቁ እንደሆነ ተገልጿል።

ዩኬ ምን ያህሉን ወደ አገራቸው ትመልሳለች?

የስደተኞችን ጉዳይ የሚያየው የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት (ሆም ኦፊስ) በዩኬ የመቆየት ሕጋዊ መብት የሌላቸው ሰዎችን ከአገሩ ያስወጣል ወይም እንዲገቡ አይፈቅድም።

ባለፈው ዓመት የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ 6 ሺህ 14 ሰዎችን ወደመጡበት አገራት እንዲመለሱ ተደርገዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው 2 ሺህ 931 ተመላሾች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ የአልባኒያውያን ተመላሾች ቁጥር ከ988 ወደ 3 ሺህ 369 ከፍ በማለቱ ነው።

በዚሁ ዓመት 1 ሺህ 889 በትናንሽ ጀልባዎች የገቡ ስደተኞች እንዲመለሱ ተደርገዋል። ከአውሮፓውያውኑ 2018 እስከ 2023 ባለው ወቅት 2 ሺህ 580 በትናንሽ ጀልባዎች የገቡ ስደተኞች ወደየአገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በትናንሽ ጀልባዎች የገቡ 2 በመቶ የሚሆኑት ይሸፍናል።

ወደ ሌሎች አገራት በጀልባ የሚገቡ ስደተኞች

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 263 ሺህ 48 ስደተኞች ባሕር እና ውቅያኖስን አቆራርጠው ወደ አውሮፓ ገብተዋል።

ከእነዚህም መካከል 60 በመቶው [157 ሺህ 314] ጣልያን፣ 57 ሺህ 0711 ስፔን እንዲሁም 41 ሺህ 561 ስደተኞች ወደ ግሪክ ደርሰዋል።

ከጥር ወር ጀምሮ ባለው ጊዜ 40 ሺህ ስደተኞች በጀልባዎች እና በመርከቦች ወደ አውሮፓ ገብተዋል።

ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበው በ2015 (እአአ) ሲሆን፣ በዚህም አንድ ሚሊዮን ስደተኞች የአገራት ድንበሮችን አቋርጠው ገብተዋል። አብዛኞቹም የሶሪያ ግጭትን ፈርተው ወደ አውሮፓ የመጡ ናቸው።

በአውሮፓ ምን ያህሉ የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበዋል?

ባለፈው ዓመት በመላው አውሮፓ የጥገኝነት ጥያቄን በመቀበል ዩናይትድ ኪንግደም አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ከ329 ሺህ 35 የጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል ጀርመን አንድ ሦስተኛውን ተቀብላለች።

ስፔን 160 ሺህ 460 ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመቀበል ሁለተኛ፣ ፈረንሳይ 145 ሺህ 95 ጠያቂዎችን በመቀበል ሦስተኛ እንዲሁም ጣልያን 130 ሺህ 565 ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመቀበል አራተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።