ሪሺ ሱናክ ዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የምትልከው “እንደገና ከተመረጥኩ ነው” አሉ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ የሚላኩት “እንደገና ከተመረጥኩ ነው” አሉ።

በዚህም አወዛጋቢ የሚባለው ወደ አገሪቱ በህገወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸው ሂደት በሩዋንዳ እንዲታይ ለማድረግ የመላክ ሂደቱም ይዘገያል ተብሏል።

ጥገኝነት ጠያቂዎች በአስገዳጅ በረራ ወደ ሩዋንዳ ከምርጫው በፊት እንደማይላኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞች ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ከምርጫው በፊት ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን እንደሚልኩ ተጠብቆ ነበር።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዩናይትድ ኪንግደም ሰኔ 27/ 2016 ዓ.ም በምታደርገው ምርጫ “እንደገና ከተመረጥኩ ስደተኞቹ ይሄዳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

የሌበር ፓርቲ በበኩሉ በምርጫው ካሸነፈ ይህንን የመንግሥት እቅድ ለማጠፍ ቃል ገብቷል።

240 ሚሊዮን ፓውንድ እንደወጣ የተገለጸው ይህ እቅድ በስድስቱ ሳምንት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በሁለቱ ዋና ተፎካካሪ ፓርቲዎች (ወግ አጥባቂው እና ሌበር ፓርቲ) መካከል ዋነኛ የሚለያዩበት ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሱናክ ከምርጫው በኋላ ህገወጥ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ እልካለሁ ማለታቸውን አስመልክቶ የሌበር ፓርቲ ይህ እቅድ “ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ማጭበርበር የታየበት ነው” በማለት ተችቶታል።

ከመንግሥት ትይዩው ሆም ሴክሬታሪ ኢቩት ኩፐር “[ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ] ይህ እቅድ ይሰራል ብሎ አያምንም ለዚያም ነው ምርጫውን አሁን ያነሳው፤ ይሸፋፍነዋል በሚል ተስፋ በማድረግ ነው” ብለዋል።

በህጋዊ አወዛጋቢነቱ የዘገየው ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ መርሃ ግብር ይፋ የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ቦሪስ ጆንሰን ነው።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩኬ የሚገቡ ስደተኞችን ያስቆማቸዋል በሚል የአገዛዛቸው ዋነኛ ዕቅድ አድርገውታል።

እናም ይህንን እቅዳቸውን ለማሳካት መራጮች እሳቸውን መምረጥ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

“በጀልባዎች የሚገቡ ስደተኞችን ማቆም አስፈላጊ ነው ብለው ካሰቡ ይህንን ለማድረግ እነሱም የሚጠበቅባቸውን ማድረግ አለባቸው። እኔ ብቻ ነኝ ይህንን የማሳካው” ሲሉ ከቢቢሲ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ሊበራል ዲሞክራት ፓርቲ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተያየት “ፍጹም ውርደት እና ሽንፈትን የተላበሰ” ሲል ጠርቶታል።

“የሩዋንዳ እቅድ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሞራል አልባ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስወጣ ቀዉስ ነው” ሲሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ ቃል አቀባይ አልስታይር ካርሚኬል ገልጸዋል።