ከእድሳት በኋላ በመጀመሪያው ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት የአዲስ አበባ ስታዲየም

ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Football Federation

ለዓመታት በዕድሳት ላይ የቆየው የአዲስ አበባ ስታዲየም ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ በሩን ከፍቶ የእግር ኳስ ተመልካቾችን አስተናግዷል። ነገር ግን ከጨዋታው ይልቅ በተሰባበሩት ወንበሮቹ ምክንያት ስታዲየሙ መነጋገሪያ ሆኗል።

የስፖርታዊ ውድድሮችን፣ ሃይማኖታዊ ዝግጅቶችን፣ የሙዚቃ ድግሶችን ጨምሮ በርካታ መሰናዶዎችን ለበርካታ አስርት ዓመታት ያስተናገደው የአዲስ አበባ ስታዲየም ላለፉት ዓመታት ለዕድሳት ተዘግቶ ቀይቷል።

የኮቪድ ወረረሽኝ በስፖርት ላይ ካደረሰው ተጽዕኖ በተጨማሪ ስታዲየሙ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ብቁ አይደለም ተብሎ መከናወን ያለባቸው የማሻሻያ ሥራዎችም በአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፈደሬሽን (ካፍ) በዝርዝር ተቀምጠውለታል።

ስታዲየሙ በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደር የአገሪቱ ዋነኛው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ሆኖ ቆይቷል።

ለዓመታት በስታዲየሙ ላይ ሲካሄድ የነበረውን የዕድሳት ሥራ በበላይነት የሚመራው እና የሚቆጣጠረውም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ነው።

የኢትዮጵያ ዋንጫ

የኢትዮጵያ ዋንጫ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ እና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ ዋንጫ በሚል ውድድር ሲካሄድ ቆይቷል።

ውድድሩ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሥር የሚከናወን ነው።

ውድድሩ በ1937 እስከ 1970ዎቹ የኢትዮጵያ ዋንጫ በሚል ስያሜ ይካሄድ ስለነበር በቀደመ ስያሜው እንዲቀጥል መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሙኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አብርሃም ገብረማሪያም በተለይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድሩ በ2011 ዓ.ም. በኮቪድ ወረርሽን ምክንያት ለዓመታት ሳይካሄድ ቆይቶ ነበር።

“ዘንድሮ ከአራት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ዋንጫ በሚል 46 ቡድኖችን ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እና ከአንደኛ ሊግ ክለቦች በስድስት ዙሮች ተሳትፈውበታል” ብለዋል።

ውድድሩ የመጨረሻዎቹ ዙር ጨዋታዎች አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአበበ ቢቂላ ስታዲም ተከናውነዋል።

የፍጻሜው ጨዋታውም በዚሁ ስታድየም እንዲከናወን መርሃ ግብር ቢወጣለትም “[ስታዲየሙ] አሁን ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ እና አቅሙን ለመፈተሽ በሚል ፌደሬሽኑ ለሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል” ብለዋል አቶ አብርሃም።

ስታዲየሙ አሁንም ያልተጠናቀቁ ውስጣዊ ሥራዎች ይቀሩታል። የመሮጫ መም ማንጠፍ እና በክብር እንግዶች መቀመጫ አካባቢ የሚኖረው የሊፍት እና ሌሎች ሥራዎች ገና አልተጠናቀቁም።

“ሆኖም መጫወቻ ሜዳው እና የተመልካች መቀመጫዎች ዝግጁ በመሆናቸው ፈቃድ ተገኝቶ ነው ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲም የተከናወነው” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ዋንጫ ለፍጻሜ ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ዲቻ ቀርበው፤ ኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 በማሸነፍ የ2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል።

ኢትዮጵያ ቡና የዋንጫው አሸናፊ በመሆኑ በአህጉራዊው በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር የመሳተፍ ዕድልን አሳክቷል።

ነገር ግን ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ በስታዲየሙ የተከሰተው ሁኔታ በዕድሳት ላይ ባለው ስታዲየም ላይ ጉዳት ያደረሰ ነበር።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩ የነበሩ ምሥሎች እንዳሳዩት ከረዥም ዓመታት በኋላ ደጋፊዎችን ያስተገናገደው ስታዲም መቀመጫዎች በተቆጡ ደጋፊዎች ተሰባብረዋል።

ስታድየሙ ላይ የደረሰውን አደጋ የሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Facebook

ሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም

ከረዥም ጊዜ በኋላ ጨዋታ ማስተናገዱን ተከትሎ ስታዲየሙ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ነበር የሚሉት የፌዴሬሽን የኮሙኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አብርሃም፣ በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች መግባት ሳይችሉ ለመመለስ ተገደዋል ብለዋል።

ከጨዋታው ጋር ተያይዞም በስታዲየሙ ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን “አንዳንድ ቦታዎች ላይ የተመልካች ወንበሮች ላይ ጉዳት ደርሷል። . . . የተለያዩ ባለሙያዎች ቆጠራ እያካሄዱ እና የደረሰውን ጉዳት እየፈተሹ ይገኛሉ” በማለት ገልጸዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወሩ በነበሩ ምሥሎች የተሰባበሩ የተመልካቾች ወንበሮች እና የተቀያሪ ተጫዋቾች መቀመጫዎች ያለቦታቸው ተገልብጠው ታይተዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው የተመልካች መቀመጫዎች ናቸው ያሉት አቶ አብርሃም “የተቀያሪ ተጫዋቾች መቀመጫዎች በቦታቸው አልነበሩም። የደረሰ ጉዳትን በተመለከተ በቀጣይ በሚቀርበው ሪፖርት ላይ የሚታይ ይሆናል። . . . በተመልካች መቀመጫዎች ላይ ጉዳት ደርሷል” ብለዋል።

አጠቃላይ የሪፖርቱ ውጤት ከታወቀ በኋላ የደረሰውን ጉዳት ይፋ ከማድረግ ባለፈ “ጥፋተኛ የሆኑ አካላት ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን የእግር ኳስ ቤተሰቡ እንዲያውቃቸው ይደረጋል” ሲሉ አክለዋል።

ከእሁዱ ጨዋታ በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያጋጠመውን ክስተት በተመለከተ ሪፖርቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግም ጨምረው አስታውቀዋል።

ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ እያጠላ የሚገኘው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ጉዳይን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ “እግር ኳስ ሜዳ ላይ የሚገኙ ውጤቶችን በፀጋ መቀበል እና ጨዋታዎችን በስፖርታዊ ጨዋነት የመከታተል ክፍተቶች አሁንም እያጋጠሙ ነው” ብለዋል።

“ስታዲየሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ውደድር አድርጎ በርካታ ወንበሮች ተነቅለው ጉዳት ደርሷል። ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው መሠረተ ልማቶች ጉዳት የሚደርስባቸው ከሆነ ለወደፊቱ ጨዋታዎችን በተመልካች የማድረጉ ነገር አዳጋች ያደርገዋል።”

ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫ ሲያነሳ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Football Federation

ይህንን ለመቅረፍ ሕብረተሰቡ እንደዚሁም ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን “የማስተማር እና ግንዛቤ የማስጨበት ሥራ በሰፊው መሥራት ይኖርባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

በደጋፊዎች ዘንድ ያገጠመው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብረሃም “ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ችግር እንደ አገር እያለብን የሚሠሩትንም በዚያው ልክ የማውደም ነገሮች ካሉ እግር ኳሱን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ይሆናል።”

ይህ በስታዲየሞች የሚያጋጥመው ሁኔታ በተለያዩ ስሜቶች በሚሆኑ ተመልካቾች የሚከሰቱ ናቸው በማለትም “በደስታ ወቅት ብዙ ጊዜ ወንበሮች ሲነቃቀሉ እናስተውላለን፤ ንዴትንም ለመግለጽ ሲነቃቀሉ እናያለን። ስለዚህ ሁሉንም ነገር ሥርዓት ባለው መልኩ ማከናወን ከደጋፊዎች የሚጠበቅ ተግባር ነው” ብለዋል።

ከእሁዱ ክስተት ጋር በተያያዘ በስታዲየም ውስጥ ሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

“በጨዋታው መጀመሪያ አካባቢ ወደ ስታዲም ለመግባት በነበረው ከፍተኛ ሰልፍ ከስታዲየም ውጪ መጠነኛ ግርግሮች ነበሩ። ነገር ግን በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የደረሰን ሪፖርት የሉም” ብለዋል።

የአዲስ አበባ ስታዲየምን በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መመዘኛ መሠረት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እየተከናወነ ያለው የዕድሳት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ገና አልተጠናቀቀም።

ዓለም አቀፍ ውድድር ከማዘጋጀት አንጻር ዕድሳቱ ከመጀመሩ በፊት ካፍ የሰጠው የግምገማ ሪፖርት መሠረት ተደርጎ ሥራው እየተከናወነ ሲሆን፣ ዕድሳቱ ከተጀመረ በኋላም የካፍ ተወካይ ስታዲየሙ ላይ የተደረጉ ሥራዎችን ገምግሞ አስተያየት መስጠቱን ቢቢሲ ተረድቷል።

እድሳቱ ሲጠናቀቅም አህጉራዊው የእግር ኳስ የበላይ አካል ባስቀመጠው ደረጃ መሠረት ሥራዎች መከናወናቸውን ገምግሞ ውሳኔ የሚሰጥ ይሆናል።

በዕድሳት ላይ ባለው ስታዲየም ንብረት ላይ እሁድ ዕለት የደረሰው ጉዳትን በሚመለከት ገና የተሰጠ አሃዛዊ መረጃ ባይኖርም፤ በዕድሳቱ ሂደት ላይ ተጨማሪ ወጪን የሚጠይቅ እንደሚሆን ይታመናል።