ቦይንግ ከኢትዮጵያ እና ከኢንዶኔዢያ አደጋዎች በኋላ በማጭበርበር ወንጀል ክስ ጥፋተኛ መሆኑን ለማመን ተስማማ

በአደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአደጋዎቹ የሞቱ ሰዎች ዘመዶች የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ቦይንግን እንዲከስ ግፊት እያደረጉ ነው

ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ አውሮፕላኖች ከደረሱ አደጋዎች በኋላ የሚጠበቅበትን ባለማድረግ በቀረበበት ለማጭበርበር የማሴር ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን ለማመን ከስምምነት ደረሰ።

ኩባንያው የ346 ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈ አሰቃቂ አደጋ በኋላ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን እንዲያሻሽል የተደረሰውን ስምምነት በመጣስ የማጭበርበር ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።

የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት አውሮፕላን አምራቹ ጥፋተኝነቱን ከማመኑ በተጨማሪ 243.6 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ለመክፈል ተስማምቷል ብሏል።

ይሁን እንጂ ከአምስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ ሁለት አውሮፕላኖች ተከስክሰው ሕይወታቸውን ያጡ የ346 ሰዎች ቤተሰቦች በውሳኔው ደስተኛ አይደሉም።

በአደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች ስምምነቱ ለቦይንግ ያደላ እና ለጠፋው ሕይወት ኃላፊነት እንዳይወስድ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን አስምተዋል።

ቦይንግ ለቀረበበት የማጭበርበር የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ነኝ ሲል ማመኑ ወደ ወንጀል የክስ ሂደት ከመግባት ይታደጋዋል።

ኩባንያው እአአ 2018 እና 2019 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖቹ በኢንዶኔዢያ እና ኢትዮጵያ ከተከሰከሱ በኋላ ከአውሮፕላኖች ደኅንነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትችት ሲደርስበት ቆይቷል።

እነዚህን አደጋዎች ተከትሎ በመላው ዓለም ከ18 ወራት በላይ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደው መቆየታቸው ይታወሳል።

እአአ 2021 ላይ ቦይንግ ለሁለቱ አውሮፕላኖች መከስከስ ምክንያት ነው የተባለ ኤምካስ የተባለ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን በተመለከተ የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደርን አጭበርብሯል መባሉን ተከትሎ በማጭበርበረ ወንጀል ተከሶ ነበር።

ኩባንያው ከ737 ማክስ 8 አውሮፕላኖቹ በተጨማሪ 787 ድሪምላይነር እና 777 ሞዴል አውሮፕላኖች ከፍተኛ የሆነ የምርት ጥራት ችግር አለባቸው በሚል ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል።

ይህን ተከትሎ ኩባንያው የምርት ሂደቱን በማሻሻል ለአውሮፕላኖቹ ደኅንነት ማረጋገጫ እንዲሰጥ በአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ትዕዛዝ ተላልፎበት ነበረ።

ኩባንያው መቀጮ ለመክፈል ከተስማማ እና ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የምርት ቁጥጥር ሂደት እና ሪፖርት የሚያጠናቅቅ ከሆነ ክስ እንደማይመሰረትበት ከስምምነት ተደርሶ ነበር።

ይህ የሦስት ዓመቱ የቁጥጥር ሂደት ሊያበቃ ጥቂት ጊዜያት ሲቀሩት ንብረትነቱ የአላስካ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ መገንጠሉ አውሮፕላን አምራቹ የአውሮፕላኖቹን ደኅንነት የሚያረጋግጥ አይደለም የሚል ክስ ቀርቦበታል።

አሁን ላይ ኩባንያው በወንጀል ክስ ጥፋተኛ ነኝ ብሎ ማመኑ በንግድ ሥራው ላይ ያለው ተጽእኖ በትክክል ይህ ነው ማለት ባይቻልም በስሙ ላይ ጥቁር ነጥብ ሆኖ ይገለጻል።

በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ በደረሱት አደጋዎች ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች ጠበቃ የሆኑት ፖል ካሴል፤ “በቦይንግ የተገደሉት 346 ሰዎች ከዚህ በላይ ፍትሕን ይጠይቃሉ” ብለዋል።

ጠበቃው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት አውሮፕላን አምራቹ 24 ቢሊዮን ዶላር እንዲቀጣ ጠይቀው ነበር።