እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሐማስ ከፍተኛ ኃላፊን ገደለች

በጥቃቱ የተገደለው ኢሃብ አል ጉሴን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ የተገደለው ኢሃብ አል ጉሴን

እስራኤል በጋዛ ከተማ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች መካከል የሐማስ ከፍተኛ ኃላፊ እንደሚገኝበት የፍልስጤም ምንጮች ገለጹ።

የአካባቢው ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢሃብ አል ጉሴን በጋዛ ከተማ እና በሰሜን ጋዛ የሚገኘውን የሐማስ አስተዳደር እንዲመራ የተሾመው ከሦስት ወራት በፊት ነው።

የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ በሚገኝ “አሸባሪዎች እያሴሩበት እና ተደብቀውበታል” ባለው አንድ የትምህርት ቤት ህንጻ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

ጦሩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እርምጃዎችን ወስጃለሁ ብሏል።

የዓይን እማኞች እንደገለጹት ከሆነ ጥቃቱ ያነጣጠረው ከጋዛ ከተማ በስተምዕራብ ካለው ሆሊ ፋሚሊ ቤተክርስቲያን አጠገብ በሚገኘው ሆሊ ፋሚሊ ትምህርት ቤት ነው። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በህንጻው ውስጥ ተጠልለው እንደነበር ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል።

የአየር ጥቃቱ ታችኛው ወለል ላይ በሚገኙ ሁለት የመማሪያ ክፍሎች ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።

ኢሃብ አል ጉሴን በሐማስ አስተዳደር ምክትል የሠራተኛ ሚኒስትር እና ከዚያ በፊት ደግሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነበር። የኢሃብ አል ጉሴን ሞት ለሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ጉዳት እንደማያስከትል ቢታሰብም ግን በሐማስ አመራር ውስጥ ክፍተት እንደሚፈጥር ተገልጿል።

በርካታ የሐማስ አስተዳደር አመራሮች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ተገድለዋል።

ባለፈው ህዳር እስራኤል በፈጸመችው አንድ የአየር ጥቃት ምክትል የባህል ሚኒስትሩ እና የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ከሌሎች የመንግስት ሠራተኞች፣ ባለስልጣናት እንዲሁም ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች ጋር ተገድለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የእስራኤል ጦር ነዋሪዎች ከጋዛ ከተማ ማዕከላዊ ክፍል እንዲለቁ ትዕዛዝ አውጥቷል።

ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ቤተሰቦች እየወጡ ነው ሲል በባኒ አመር አካባቢ ከሚስቱ፣ ከአምስት ልጆቹ፣ ከእናቱ እና ከእህቱ ጋር የሚኖረው የ47 ዓመቱ ኢብራሂም አል-ባርባሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ቤታችንን መልቀቅ እንዳለብን ከጎረቤቶቻችን ሰማን። ከሠራዊቱ ምንም ዓይነት ጥሪ ወይም ጽሑፍ ባይደርሰንም እንደገና ለመፈናቀል ንብረታችንን መሰብሰብ ጀምረናል” ብሏል።

"ለወራት ለረሃብ በተቃረበ ሁኔታ ውስጥ እየኖርን ነው።"

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የሚደረስ የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል ዓላማዋ እስክታስፈጽም ድረስ ጦርነቱን እንድትቀጥል መፍቀድ እንዳለበት አሳስበዋል።

ይህ ዓላማ የሐማስን ወታደራዊ እና የአስተዳደር አቅም ማፈራረስን እና ታጋቾችን መመለስ እንሚመለከተ ከዚህ ቀደም ገልጸዋል።

በቅርቡ ለቀረበው የተኩስ አቁም ሃሳብ የእስራኤልን ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸውን የሐማስ ባለስልጣናት ተናግረዋል።