ዴሞክራቶች ባይደንን ዕጩ አድርጎ ማቅረብን በተመለከተ ውይይት አደረጉ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተጽእኖ ፈጣሪ ዴሞክራት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቀጣዩ ምርጫ ጆ ባይደንን ዕጩ አድርጎ ማቅረብን በተመለከተ ተወያዩ።

ለሁለተኛ ዙር ለመመረጥ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ባይደን፤ ከተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያደረጉት ክርክር አገሪቱን መምራት የሚያስችል አካላዊ እና አእምሯዊ ጤና አላቸው ወይ የሚል ከፍተኛ ጥያቄን አስነስቶባቸዋል።

ባይደን ከአንድ ሳምንት በፊት በነበረው ክርክር፤ ንግግራቸው ሲወለካከፍ እና ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው ታይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ባይደን በክርክሩ ወቅት ድምጻቸው እንደመታፈንም ብሎ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ብዙ ጥያቄን ካስነሳባቸው ክርክር በኋላ በተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳዎች እንዲሁም ለቃለ መጠይቆች ቢቀርቡም አሁንም በፓርቲ አባላቶቻቸው ጭምር አቅሙ እንዳላቸው ማረጋገጫ መስጠት አልቻሉም።

ይህን ተከትሎ ትናንት እሁድ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም. አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተጽእኖ ፈጣሪ ዴሞክራት የሆኑ የምክር ቤት አባላት ስብሰባ በተቀመጡበት ወቅት ባይደንን ዕጩ አድርጎ በማቅረብ አግባብነት ላይ ተነጋግረዋል።

የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው በስብሰባው ከነበሩ ዴሞክራቶች መካከል ቢያንስ አራቱ ባይደን ኅዳር 2017 በሚደረገው ምርጫ ከዕጩነት እራሳቸውን አግልለው ዴሞክራቶች በሌላ ዕጩ መወከል አለባቸው ብለዋል። ሦስቱ ደግሞ ባይደን ምርጫውን ላያሸንፉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ቁልፍ የዴሞክራት አባላት ጭምር ባይደን ከትራምፕ ጋር እንዲወዳደሩ የሚደረግ ከሆነ ዴሞክራቶች ስልጣናቸውን እንደሚያጡ ይገምታሉ። በዚህም ባይደን በሌላ ዕጩ እንዲተኩ ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ ፕሬዝዳንቱን በሌላ መተካት በመራጮች ዘንድ ብዙ የማይታወቁ ሰዎችን ወደፊት ማምጣት ይሆናል ይላሉ።

የካሊፎርኒያ ግዛት ተወካይ የሆኑት አደም ሺፍ፤ ፕሬዝዳንቱ ያደረጉት ክርክር ዶናልድ ትራምፕን ማሸነፍ የሚያስችል አቅም አላቸው ወይ የሚል ጥያቄን ማስነሳቱን ተናግረዋል።

ምንም እንኳ እኚህ ተጽእኖ ፈጣሪ ዴሞክራት ፕሬዝዳንቱ በሌላ ዕጩ መለወጥ አለባቸው ባይሉም ቢያንስ አምስት ዴሞክራት የምክር ቤት አባላት ባይደን በሌላ ዕጩ መተካት አለባቸው ሲሉ ሃሳባቸውን በይፋ ገልጸዋል።

ከሁለት ቀናት በፊት ዎል ስትሪት ጆርናል ይፋ ያደረገው ከፓርቲ አባላት የተሰበሰበ አስተያየት ባይደን በዴሞክራቶች ዘንድ ያላቸው ድጋፍ መቀነሱን አሳይቷል።

ከአምስት ወራት በፊት 93 በመቶ የሚሆኑት ዴሞክራቶች ፕሬዝዳንቱን እንደግፋለን ያሉ ሲሆን አሁን ላይ የተሰበሰበው አስያየት የድጋፍ ቁጥሩ ወደ 86 በመቶ መውረዱን አሳይቷል።

ባይደን በማን ሊተኩ ይችላሉ?

በብዙዎች ጋር እየተመላለሳ ያለው ጥያቄ ፕሬዝዳንቱ በምርጫው የማይሳተፉ ከሆነ ማን እና እንዴት ሊተኩ ይችላሉ የሚለው ነው።

ዴሞክራቶች ባይደንን የሚቀይሩ ከሆነ ፓርቲው ውስጡ እየታመሰ ነው የሚል መልዕክት ስለሚያስተላልፍ ለሪፓብሊካን እና ለትራምፕ ስኬት ይሆናል የሚሉ ተንታኞች አሉ።

በዚህም አንዳንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ዴሞክራቶች ትኩረት መደረግ ያለበት ዕጩዎቹ ላይ ሳይሆን ፖሊሲዎች ላይ ነው ይላሉ።

የቬርሞንት ሴናተር የሆኑት በርኒ ሳንድረስ ትናንት ለሲቢኤስ ሲናገሩ፤ “ባይደን አርጅተዋል። እንደከዚህ ቀደሙ ንግግራቸው ያማረ አይደለም። የኤር ፎርስ ዋን ደረጃን ሲወጣጡ ማየት እፈልጋለሁ። ግን አይችሉም። ትኩረታችን ፖሊሲዎች ላይ ማድረግ አለብን። አገሪቱን የሚጠቅም እና ብዙዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ ያለው ማን ነው የሚለው መሆን አለበት” ብለዋል።