የሶማሊያው ፕሬዝዳንት “ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቱን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ አይደለችም” አሉ

የፎቶው ባለመብት, @TheVillaSomalia
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የገቡበትን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በንግግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ዝግጁ አይደለችም ሲሉ ተናገሩ።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ቅዳሜ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም. በአገሪቱ ምክር ቤት የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ መንግሥታቸው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቱን ለማርገብ ፍላጎት ቢኖረውም፤ በአዲስ አበባ ያለው መንግሥት ግን ለውይይት ዝግጁ አይደለም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ ከጥቂት ቀናት በፊት “የሶማሊያ መንግሥት እኛን ከማናገር፣ በየሰፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ መርጧል” ብለው ከተናገሩ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ላይ ሰለሶማሊያ ጉዳይ ሲናገሩ፤ “እኛን ለመክሰስ አገር ለአገር መሄድ አያስፈልግም፤ አዲስ አበባ መምጣት ይቻላል። ለመነጋገር ዝግጁ ነን. . . ” ብለው ነበር።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ሁለቱ አገራት የገቡበትን ቀውስ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት ጨርሶ ሊያነጋግረን አልሞከረም ብለዋል።
“ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት አገር ወቅታዊ ጉዳዮችን በትብብር ለመፍታት አናግራን አታውቅም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በአንጻሩ “እየተዘዋወሩ ሽምግልና ይጠይቃሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።
የተካረረው የሞቃዲሾ እና አዲስ አበባ ዲፕሎማሲ
ከስድስት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ መፈረሟ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል።
የመግባቢያው ሠነድ ኢትዮጵያ ነጻ አገር መሆኗን ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅናን የሚሰጥ ሲሆን፤ ሶማሊላንድ በምላሹ ለኢትዮጵያ የባሕር በር እና የባሕር ኃይል ሰፈር የሚውል የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚፈቅድ ስለመሆኑ መዘገቡ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ፣ ሞቃዲሾ የአዲስ አበባ እና የሃርጌሳ ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ ድርጊት ነው ትላለች።
በዚህ ያልተገደበችው ሶማሊያ በሞቃዲሾ የሚገኘቱን የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገር አስወጥታ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን መጥራቷ ይታወሳል።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ከግዛቷ እንደምታስወጣም ጭምር ገልጻለች።
የአንካራው ውይይት
ለወራተ በዘለቀ ውጥረት ውስጥ የቆዩት የሁለቱ አገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰኔ 24/2016 ዓ.ም. ወደ ቱርክ መዲና አንካራ ተጉዘው የተናጠል ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከውይይቱ በኋላ ቱርክ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በጋራ ባወጡት መግለጫ በሁለቱ አገራት መካከል ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ለሁለተኛ ዙር ውይይት ነሐሴ 27/ 2016 ዓ.ም. እንደሚገናኙ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ግን ይህ የአንካራ ውይይት “ገና ሳይጀምር የተጠናቀቀ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ አንካራ የተጓዙት የኢትዮጵያን ጥያቄ ተከትሎ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በአቋሟ በመጽናቷ “ድርድሩ ገና ሳይጀምር እንዲጠናቀቅ” ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
“እኛ ድርድሩን እንዳልሰረዝነው መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ጠይቃለች” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ፕሬዝዳንቱ ሁለቱን አገራት ከዚህ ቀደም በናይሮቢ ኬንያ ለማደራደር የተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀርቷል በማለት ጨምረው ተናግረዋል።
ነገር ግን “ይህ የኢትዮጵያ ለውይይት ዝግጁ አለመሆን እና ቅንነት ማጣት” ቱርክ ለማደራደር እያደረገች ባለችው ጥረት ላይ እንቅፋት አይሆንም የሚል እምነት አለን ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ቅዳሜ ዕለት ለአገራቸው የፓርላማ አባላት ሲናገሩ “የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት የመልካም ጉርብትና እና ዓለም አቀፍ ሕግ መርህን ጣሰ። ዛሬ ደግሞ ሕገ-ወጥ በሆነ አቋሙ ጸንቷል” ብለዋል።
“ሶማሊያን ይህ ውዝግብ አልፈጠረችም እንዲሁም ስምምነት እንዳይደርስ እክል አልሆነችም” ሲሉ ተናግረዋል።
“አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ የምፈልገው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጠላትነት ስሜት የለንም፤ አሁን ካሉበት ፈተና እንዲወጡ እንዲሁም ስኬት፣ ሰላም እና መረጋጋትን ከልብ እንመኝላቸዋለን” ብለዋል።












