የመብት ተሟጋቾች “አሳሳቢ” ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እና የፍትህ መዶሻ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሙስ ዕለት በሕዝብ ተካዮች ምክር ቤት የተገኙት የመንግሥታቸውን ዓመታዊ ሪፖርት ለማቅረብ እና ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ለመስጠት ነበር።

ለሦስት ሰዓት ያህል በዘለቀው የምክር ቤት ውሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የመንግሥታቸው አቋም ምን እንደሆነ ፍንጭ ሊሰጡ የሚችሉ ጉዳዮችን አንስተዋል።

ከእነዚህ መካከልም መንግሥታቸው ደጋግሞ ይጥሰዋል ስለሚባለው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዮ አቶ አበባው ደሳለው ጥያቄ ከቀረበላቸው በኋላ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን የተመለከተው ይገኝበታል።

አቶ አበባው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥያቄ፤ “መንግስት.... እንዲሁም ጅምላ ግድያ እና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማቆም ምን የወሰነው ጉዳይ አለ?” የሚል ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሻቸውን የጀመሩት የሰብዓዊ መብትን “እንደ ቋንቋ” በማሞካሸት ነው። የሰብዓዊ መብትን ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ ፍቺ ከግንዛቤ አስገብተው ለመተንተን ብዙም አልደከሙም።

“ሰብዓዊ መብት ደስ ሚል ቋንቋ ነው” ያሉት ዐቢይ፤ “ግን ይሄ ቋንቋ ከዋናው የትርጉም ግንዱ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ብቻ አላበቁም፤ “የሰብዓዊ መብት የሚባል አዋጅ ተቋም አሠራርን መፈተሽ ያስፈልጋል” በማለት፤ “እኛ ደሞዝ የማንከፍለው ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናነተ መተው ነው” ብለዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን ያስደነገጠ ነበር።

በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚመሩ ግለሰቦች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር “አሳሳቢ” እና “አስደንጋጭ” መሆኑን ለቢቢሲ ተናገረዋል።

ሆኖም ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሐሙስ ዕለት ንግግር ድንገት ተከሰተ አለመሆኑን ያነሳሉ።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በድኅረ 2010 በአዲሱ የሲቪል ማኅበራት ሕግ የተገኘው የመደራጀት ነጻነት “የመጨረሻ ግብዓተ መሬት ነው” ይላሉ።

ነገር ግን ይህ የዐቢይ ንግግር አጠቃላይ የአገሪቱ “ሰብዓዊ መብት ሁኔታ ላይ ለውጥ አያመጣም” ሲሉ ያክላሉ። የሰብዓዊ መብት ምህሩ የሰብዓዊ መብት ደርጅቶቹ በመኖራቸው መንግሥት “ከሕግ ውጪ የሚገደሉ እና የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር አለመቀነሱ ወይም በአጠቃላይ የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ሁኔታን” ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ በተጨማሪም የሕግ ማሻሻያዎቹ ከአዲስ አበባ እና ከአንዳንድ ዋና ዋና የከተማ ማዕከላት ውጪ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ የጎላ ተጽዕኖ አላመጣም” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ተጽዕኖ ቢኖረውም “መዋቅራዊ ወይም ጥልቅ አይሆንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ኃይለማሪያም “በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ላይ እየደረሰ ካለው ጥቃት እና ጫና አንጻር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ብዙም አላስገረመኝም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱን “መንግሥታዊ መማረርን” እንዳልጠበቁ የገለጹት አቶ ያሬድ፤ “በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን [define] ያደረጉበት የፈረጁበት መንገድ ግን እጅግ እጅግ አሳሳቢ ነው” ይላሉ።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በፈቃዱ ኃይሉም ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው።

አቶ በፍቃዱ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሉ ሁኔታዎች በሙሉ የሚያመላክቱት መንግሥት በጥርጣሬ እና በጥላቻ እየተመለከተን እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችሉ ናቸው” ይላሉ።

እንደ አቶ ያሬድ ሁሉ እሳቸውም፤ “በግልጽ እንደዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቀርብ ሪፖርት ላይ ከምንም ተነስተው እንደዚህ ዓይነት ንግግር ያደርጋሉ የሚል እምነት አልነበረኝም” ሲሉ ያክላሉ።

አቶ በፍቃዱ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፤ “ድንገት የወጣ ንግግር እንዳልሆነ ያስታውቃል” በማለት፤ ለዚህ ደግሞ በማሳያነት የሚጠቅሱት የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚደርሱ ጫናዎችን ነው።

እነዚህ ጫናዎች ከሁለት ሳምንታት በፊት 12 የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ አገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ ላይ ተስተጋብቷል።

ተቋማቱ በመግለጫቸው “ጠንካራ የውትወታ ሥራን” በመሠራታቸው “ከመንግሥት በኩል ተደጋጋሚ ጥቃት እና ከፍተኛ ጫና” እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ጠቁመው ነበር።

እነዚህ ጫናዎች “በሚወጡ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና አሠራሮች ላይ ጭምር” ጎልተው እንደሚታዩ በዚሁ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ በሥራ ኃላፊዎች እና በሠራተኞቻቸው ላይ ከፍተኛ የሆኑ “ማስፈራሪያዎች፣ ዛቻዎች እና ጫናዎች” መፈጸማቸውንም በዚሁ መግለጫው ገልጸዋል።

አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር “በዘፈቀደ ይፈጸሙ የነበሩ ከሕግ አግብ ውጪ መንግሥት የሚፈጽማቸውን ጥፋቶች እና ስህተቶች ሕጋዊ ቅርጽ የማስያዝ ዓይነት ምልክት ነው የሚታየው” ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, @PMEthiopia

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተወካዮች ምክር ቤት ስለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በተናገሩበት ስብሰባ ላይ

የሴታዊት ንቅናቄ መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ስህን ተፈራ “እስካሁን ያለው ማዋከብም፣ ፍተሻም በሕግ የታቀፈ አይደለም” ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ካሻሻሏቸው እና ከፍተኛ ውዳሴ ካገኙባቸው ሕጎች መካከል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ አንደኛው ነው።

ከአምስት ዓመት በፊት የተሻሻለው ሕግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከ10 በመቶ በላይ ገቢያቸውን ከውጭ ምንጮች እንዲቀበሉ አይፈቀድላቸውም።

ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይህን ሕግ “አፋኝ” ሲሉ ይገልጹታል። በዚህ ሕግ ሳቢያም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴያቸው በእጅጉ ተገድቦ ነበር።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ “አላስፈላጊ ገደብ ነው ተብሎ” ሕጉ መሻሻሉን የሚያስታውሱት አቶ በፍቃዱ “አስተዳደራቸው ውዳሴ እና ሙገሳ የተቀበለበትን ነገር ነው አሁን እየተቹ ያሉት” ይላሉ።

አቶ ያሬድ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው “መልሰን እንደገና ከዚህ በፊት ወደነበሩት አፋኝ ሕጎች ልንመለስ የምንችለበት አደጋ ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋት የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ውስጥ እንዲገባ ነው ያደረጉት” ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም. ለአገሪቱ ሕግ አውጪዎች ባደረጉት ንግግራቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የገቢ ምንጭ የተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል።

ዐቢይ “እኛ ደመወዝ የማንከፍለው፣ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናነት መተው ነው” ብለዋል።

ይህ ንግግራቸው “መሠርታዊ የሆነ የሃሳብ መዛነፍ ያለበት ነው” የሚሉት አቶ ያሬድ “በየትኛውም ዓለም ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ለትርፍ ያልተቋቋሙ ስለሆኑ የራሳቸው ገንዘብ ማመንጨት አይችሉም” ይላሉ።

አቶ ያሬድ አክለውም “እኛ የማንከፍላቸው የሚለው ሃሳብ በራሱ ስህተት አለው እነሱ ሊከፍሉ አይችሉም ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ምክንያቱም የአቅም ጉዳይ ሳይሆን ከነጻነት ጋር ስለሚያያዝ” ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ላይ አለ ያሉትን “ስህተት” ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሚያስደነግጥ ይዘት ያለው ንግግር ነው ያደረጉት” የሚሉት ዶ/ር ስህን “በተለይ እኛ የማንከፍላቸው ተቋማት ያሉት እሱ ያሳስባል። የትኛውም አገር ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች መንግሥት አይከፍላቸውም ገለልተኛ መሆን ስላለባቸው” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

የሴታዊት ንቅናቄ መሥራቿ ዶ/ር ስህን “[እኛ የማንከፍላቸው ያሉት] እንደ እኛ ዓይነት ድርጅቶችን ቆንጠጥ ለማድረግ ከሆነም ግልጽ አይደለም። መንግሥት ከከፈለንማ ችግር አለ፤ ገለልተኛ መሆን አንችልም” ሲሉ አክለዋል።

አቶ በፍቃዱ በበኩላቸው፤ “ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከተለያዩ ድርጅቶች ገቢ ማሰባሰብ ይችላሉ ይበል እንጂ ዞሮ ዞሮ ክትትል የሚያደርገው ተቋም የመንግሥት ነው” ሲሉ ሥራቸው የመንግሥት ዕይታ የተሰወረ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም “በምሥጢር የምናድረገው ነገር የለም፤ ለነገሩ ሥራችንንም በአደባባይ ነው የምንሠራው ግን ሪፖርት የሚያደርጉት ለሌላ ኃይሎች ነው፤ ገንዘብ የሚያገኙትም ከውጭ ኃይሎች አሉ። ከተገኘው ምንጭ ሁሉ ገቢ የማሰባሰብ መብቱ ነው የተሰጠን፤ ያ ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ የመደራጀት ነጻነት ጋር የሚገናኝ ነው። ችሮታ አይደለም” ብልዋል።

“በፊትም በኢህአዲግ ጊዜ እንደዚያ ነበር የሚባለው፤ ‘የውጭ ድርጅቶች ተላላኪ’ ብዙ ብዙ ስያሜ ነበር” የሚሉት ዶ/ር ስህን፤ “ወደ አፋኝ አካሄድን ከሄድን ለሁላችንም አደጋ አለው፤ ለእኛ ለሥራችን ሳይሆን ዋናው ነገር ከዚያ በኋላ ማን ነው ይሄንን ሪፖርት የሚያደርገው?” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ዶ/ር ስህን አክለውም “ራሳችን ገንዘብ ከለጋሽ ድርጅቶችም ከሌላ ውጭ አገር ካሉ ለጋሽ ድርጅቶችም አፈላልገን ሥራውን መሥራታችን አይቀርም። የትም አገር ቢሆን ለሰብዓዊ መብት ሥራ ሌላ መንገድ የለውም” ይላሉ።

ሦስቱም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የመንግሥታቸውን ቀጣይ እርምጃ ጠቋሚ መሆኑን ያነሳሉ።

ዶ/ር ስህን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር፤ “ለምን መንግሥትን የሚወቅስ ነገር ትናገራችሁ ብሎ በፊት እንደነበረው ዓይነት በጣም አፋኝ ወደ ሆነ ሕግ ተመልሰን ልንሄድ ነው የሚል ዓይነት ፍንጭ መሰለኝ” ይላሉ።

በአቶ በፍቃዱ ኃይሉ በበኩላቸው “የሰብዓዊ መብት የሚባል አዋጅ ተቋም አሠራር ነው ያሉት ስለዚህ በሁሉም ዘርፍ ነው መምጣት ፈለጉት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“አንዳንዱ ነገር በሕግ የሚወሰን ነው። ስለዚህ የሕግ ክለሳ ሊኖር እንደሚችል [እጠረጥራለሁ]” የሚሉት አቶ ፍቃዱ፤ “ይሄ በተዘዋዋሪ ስናያቸው የነበሩ ጫናዎች በሙሉ በሕጋዊ እና በአሠራር ደረጃ መንግሥታዊ እውቅና ኖሮት ሊመጣ እና ሊጠናከር የሚችል ነው ብለን ጠርጥረናል፤ የሚያስደነግጥ ነው ምንም ጥያቄ የለውም” በሚል ስጋታቸውን አጋርተዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት የሕግ ምሁር ደግሞ በቅርብ ጊዜ የተዋወቁ ሕጎችን በመጥቀስ ከዚህ በፊት የነበሩት “የሕግ ለውጦች እና ማሻሻያዎች አሁን ሞተዋል” በማለት ነገሮች ወደ ኋላ እየተመለሱ ነው የሚል ምልከታ አላቸው።

ለዚህም የኢሚግሬሽን እና የንብረት ማስመለስ አዋጅን በማንሳት “የ2010ሩን ለውጥ ተከትሎ የተገኙት የሕግ ማሻሻያዎች መቅበሪያ ሣጥን ላይ የመጨረሻው ሚስማር እየተመታ ያለ ይመስላል” በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።