ጎዳና ተዳዳሪዎችን በገንዘብ እና በእስር የሚቀጣው አዲሱ የአሜሪካ ከተሞች ፖሊሲ

የፎቶው ባለመብት, EPA
“ከዚህች ስፍራ እስኪያስነሱኝ ድረስ 20 ደቂቃ አለችኝ” ይላል በሎስ አንጀለስ ሆሊውድ የእግረኛ መንገድ ላይ አረንጓዴ ድንኳኑን ዘርግቶ የሚኖረው አንቶኒ።
የሎስ አንጀለስ ባለሥልጣናት ጓዙን ጠቅልሎ ከዚህ ቦታ ካልሄደ ሊታሰር እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል ለጎዳና ተዳዳሪው አንቶኒ።
ከተሞች ማንኛውንም ጎዳና (ውጭ) ላይ የሚያድር ሰው መቅጣት እንደሚችሉ የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ባለሥልጣናቱ ነግረውታል።
ይህም የአሜሪካ የመኖሪያ ቤት እጦት ቀውስ ከጀመረበት ከ1980ዎቹ በኋላ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ጉልህ ውሳኔ ነው ተብሏል።
በጎዳና ላይ ኑሮውን ያደረገው አንቶኒ ይህ ውሳኔ በጭንቀቱ ላይ ሌላ ጭንቅ እንደጨመረበትም ለመጠለያነት በዘረጋት ድንኳን ውስጥ ሆኖ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በዚያች መጠለያ ውስጥ ቆሻሻ በሚጣልበት ጥቁር ትልቅ ፕላስቲክ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ሲጓጓዝ ይዞት የሚሄደው እቃው ተቋጥሯል።
“አንዳንድ ምሽቶች እንቅልፍ አይወስደኝም” የሚለው አንቶኒ “ዛሬ ድክም ብሎኝ ነው የዋልኩት። ሰውነቴን የማሳርፍበት እና መተኛት ብቻ ነው የምፈልገው። ማንንም አላስቸገርኩም” ሲል ለቢቢሲ ያስረዳል።
ከአፍታ ቆይታ በኋላ አንቶኒ መጠለያውን ጠቅልሎ አዲስ ማረፊያ ስፍራ ፍለጋ ወጣ።
የሰሞኑን የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን ተከትሎ ቀድሞውንም ጎዳና ተዳዳሪዎች ውጭ እንዳያድሩ እየከለከሉ የነበሩ ከተሞች ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ጎዳና የሚያድሩ አሜሪካውያን የዘረጓቸውን መጠለያዎችንም መጥረግ ጀምረዋል።
በርካታ የአሜሪካ ከተሞች በአገሪቷ እያንሰራራ የመጣውን የቤት አልባነት ቀውስ እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል ሲታገሉ ቆይተዋል።
በቅርብ ጊዜ በነበረው የዌስት ኮስት ግዛቶች ምርጫ ቤት አልባነት ዋነኛ ጉዳይ የነበረ ሲሆን፣ ባለሥልጣናቱም ለቤት አልባዎች መጠለያ ለመቋቋም እና አቅምን ከግምት ውስጥ ያስገቡ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በማፍሰስ ላይ ናቸው።
በርካታ የከተማ አስተዳደሮችም ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጁ ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው ይገኛል።
“ቀላል አይደለም። ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማምጣት ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። አሁን እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ቲያትር ነው” ሲሉም የአሜሪካ የሲቪል ነጻነቶች ኅብረት (ኤሲኤልዩ) የተሰኘው ድርጅት የሕግ ባለሙያ የሆኑት ስካውት ካትቪች ያስረዳሉ።
“ፖለቲከኞች አንድ ነገር እያደረግን ነው የሚለውን ማሳያ ይፈልጋሉ” ይላሉ።
የሕግ ባለሙያዋ ካትቪችም ሆነ ሌሎች ተሟጋቾች የሚሉት ጎዳና ተዳዳሪዎችን ማሰር ወይም መቅጣት ችግሩን ከማባባስ ውጪ ምንም መፍትሄ አያመጣም ነው።
“ይህ እርምጃ ጊዜያዊ ነው። እርግጥ ነው በጎዳናዎቹ ላይ ያሉትን መጠለያዎች ማስወገድ ይቻላል። ነገ ግን የታሰሩት ሰዎች ወደ እነዚሁ ጎዳናዎች ተመልሰው መምጣታቸው የማይቀር ነው” ይላሉ።
በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበው የአሜሪካውያን ቤት አልባነት
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ያሳለፈው ብያኔ ከተሞች እና የአካባቢው አስተዳደሮች ቤት አልባዎችን በምን መንገድ መያዝ እንዳለባቸው ያስቀመጠው ነገር የለም። ነገር ግን ማኅበረሰቦች ሕጋዊ ምላሽን ሳይፈሩ ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ፈቅዷል።
ለዚህ ብያኔ መነሻ የሆነው 40 ሺህ ገደማ ሕዝብ የሚኖርባት የኦሪጎኗ ግዛት ግራንትስ ፓስ የተሰኘችው አነስተኛ ከተማ ናት።
በባለፉት 20 ዓመታት የከተማዋ ሕዝብ በእጥፍ ቢጨምርም ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ቤቶች እና የመንግሥት መኖሪያ ቤቶች አቅርቦት በትይዩ መልኩ አልሄዱም። በዚህም ምክንያት የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበ ሲሆንመ፣ የቤት አልባዎችም ቁጥር እንዲሁ ጨምሯል።
የከተማዋ አስተዳዳሪዎችም በሕዝባዊ ስፍራዎች እና ጎዳናዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚያድሩ ሰዎች 295 ዶላር ቅጣት ወይም በ20 ቀን እስራት እንዲቀጡ የሚፈቅደውን ሕግ አውጥተዋል።
የከተማዋ ሦስት ጎዳና ተዳዳሪዎችም ከተማዋ ያስቀመጠችውን ቅጣት መክፈል ባለመቻላቸው በአውሮፓውያኑ 2018 አስተዳደሩን ከሰዋል።
የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንደነዚህ ያሉ ሕጎች ጭካኔ የተሞላባቸው ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጠ።
ነገር ግን የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተሞች ጎዳና ተዳዳሪዎች በሕዝብ ስፍራዎች እንዳያድሩ መከልከል ይችላሉ ሲል ውሳኔ አሳለፈ።
ግራንትስ ፓስ ከተማን ወክለው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረቡት ቲያን ኢቫንጀሊስ የከተማዋ ባላሥልጣናት ማንንም አስገድደው መጠለያ ውስጥ ማስገባት ባለመቻላቸው እጃቸው ተጠምዝዞ እንደነበር ነው ያስረዱት።
ከተማዋ እየሰጠችው ያለውን የመጠለያ አገልግሎት ለመጠቀም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በጎዳናዎች ላይ መጠለያ ዘርግተው እያደሩ ነው ሲሉ ተከራክረው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔንም አድንቀዋል።
የግራንትስ ፓስ ከተማ አስተዳዳሪዎች ጎዳና የሚያድሩ ሰዎች የሚዘረጓቸውን መጠለያዎችን ከማገዳቸው በፊት ውሳኔያቸውን እንደሚመረምሩ አስታውቀዋል።
ይህ ብያኔ የተላለፈው የቤት አልባ አሜሪካውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለበት ወቅት ነው።
ባለፈው ዓመት 653 ሺህ ሰዎች ቤት እንደሌላቸው የአሜሪካ መንግሥት አሃዝ የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህም የአሜሪካ የቤቶች እና የከተማ ልማት ቆጠራ ከጀመረበት ከ2007 ጀምሮ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ11 በመቶ ያህል ጭማሪ አሳይቷል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ የሲቪል ነጻነቶች ኅብረት (ኤሲኤልዩ) የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን ተከትሎ የተለያዩ ከተሞች እየወሰዷቸው ያሉ እርምጃዎችን እየተከታተለ ይገኛል።
የኒው ሃምፕሻየር ከተማ ከንቲባ “ጎዳናዎችን ደኅንነታቸው የተጠበቀ፣ ጽዱ እና መተላለፊያ” እንዲኖራቸው ለማድረግ የጎዳና ላይ መጠለያዎችን እንደሚያጸዱ መናገራቸውን ተከትሎ አስተዳደሩ ውሳኔውን እንዲቀለብስ ኅብረቱ ደብዳቤ ጽፏል።
እንደ ላንካስተር፣ ስፖካኔ፣ ካሊፎርኒያ ያሉ የከተማ አስተዳደሮች ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ እና በጎዳና ላይ ያሉ መጠለያዎችን እንደሚጠራርጉ እየተናገሩ ነው።
ነገር ግን አቅም የሌላቸውን በገንዘብ መቅጣት አሳሳቢ እንደሆነ ተሟጋቾች ይናገራሉ። እንዲሁም በእስራት መቅጣት ሥራ ወይም መኖሪያ ቤት ለማግኘት የበለጠ ፈታኝ እንደሚያደርገውም ነው እነዚህ ተሟጋቾች የሚያስረዱት።
“ቅጣት ያልከፈሉ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው በጣም በርካታ ናቸው። መታሰራቸው ደግሞ ሥራ እንዳይቀጠሩ እንዲሁም መኖሪያ ቤት እንዳያገኙ የበለጠ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይከታቸዋል” በማለት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሶሺዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስ ሄሪንግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፍርድ ቤት ውሳኔውን ሁሉም ከተሞች በደስታ አልተቀበሉትም።
የሎስ አንጀለስ ከተማ ከንቲባ ውሳኔውን “አሳዛኝ” ብለው የጠሩት ሲሆን፣ በተመጣጣኝ ዋጋ መኖሪያ ቤቶች ለማቅረብ ኢንቨስት የማድረግ ዕቅድን ከቤት የማስወጣትን ጥበቃ እንደሚያጠናክሩ ቃል ገብተዋል።
ይህንን ከተናገሩ ከቀናት በኋላም ከተማዋ በስድስት ዓመታት ውስጥ አይታው የማታውቀውን ዝቅተኛ ቤት አልባዎች ቁጥር መዝግባለች።
ተሟጋቾችም ሌሎች ከተሞች ይህችን ከተማ ተምሳሌት ሊያደርጓት እንደሚገባ እየተናገሩ ነው። “እውነተኛ ለውጥ ጊዜ ይወስዳል” በማለት የሚናገሩት በሎስ አንጀለስ አካባቢ ለቤት አልባዎች አገልግሎት የሚሰጠው ፓዝ የተሰኘው ድርጅት ዳይሬክተር ሳቫ ሞሮዞቭ ናቸው።
የሳቫ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በሎስ አንጀለስ አካባቢ ለሚገኙ ጎዳና ተዳዳሪዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን ለማሳወቅ እየሠሩ ነው።
ቤት የሌላቸውን ማሰር? “ቢያንስ አልጋ ይኖረኛል”
አንቶኒ ድንኳን ከዘረጋበት አካባቢ የሚኖረው የ28 ዓመቱ ቶፈር ዊሊያምስ መጠለያውን ከዛፍ ቅርንጫፎች እና ከመኪና ማቆሚያ ምሰሶ ጋር አስሯል።
ወታደር እንደነበር የሚናገረው ቶፈር በጎዳና ላይ ኑሮውን ካደረገ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። ከፍተኛ እና ተደራራቢ የህክምና ወጪዎች እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ ያመጣው ውጣ ውረድ ሥራውን እና መኖሪያውን አሳጥተውታል።
ልክ እንደ አንቶኒ ቶፈርም የከተማው ባለሥልጣናት እና ሕግ አስከባሪዎች ርህራሄ ማጣታቸው ያሳዝነዋል እንዲሁም ያበሳጨዋል።
“ሰዎች እኛን የሚመለከቱበት መንገድ አስገራሚ ነው። ከእንሳሳት ባነሰ መልኩ ነው የሚያዩን፤ ምንም አያስቡበትም” ሲልም እንባው ያቀረረ ቶፈን ያስረዳል።
“ወታደር ሆኜ ለስምንት ዓመታት አገልግያለሁ። ሁለት ጊዜ ዘምቻለሁ። ለዚህች አገር የመጨረሻውን መስዋዕትነት ከፍያለሁ፤ ነገር ግን እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቆጠሬ የሚገርም ነው” ይላል።
በጎዳና ላይ በመኖሩ መታሰር ያስፈራው ይሆን ብሎ ቢቢሲ በጠየቀው ጊዜም ክስተቱ የሕይወት አካል ነው የሚለው ቶፈር “እስኪደርስ ድረስ አያስጨንቀኝም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ልክ እንደ ቶፈር፣ አንቶኒም መታሰር የከፋ ሊሆን አይችልም ይላል። “ቢያንስ አልጋ ይኖረኛል፤ ምናልባትም በሥርዓቱ ውስጥ ተካትቼ ትክክለኛውን ድጋፍ አገኛለሁ” ሲል ተናግሯል።












