ኬንያ መንግሥታትን ለሸሹ ስደተኞች መሸሸጊያ መሆኗ እያበቃ ይሆን?

በኬንያ በአሁኑ ሰዓት ከ 3ሺህ በላይ ስደተኞች በተለያየ ምክንያት ከለላ እንደሚፈልጉ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በኬንያ በአሁኑ ሰዓት ከ 3ሺህ በላይ ስደተኞች በተለያየ ምክንያት ከለላ እንደሚፈልጉ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይናገራሉ።

ኬንያ የአገራቸውን መንግሥታትን በትር፣ እስር እና ማሰቃየት ሸሽተው ለሚመጡ የጎረቤት አገራት ስደተኞች አስተማማኝ መጠለያ ሆና ቆይታለች።

አሁን ግን ከፖለቲካ እስር እና ከጦርነት ሸሽተው ለሚመጡ የምትዘረጋው እጅ ሳይሆን እስር እና ጠርዞ ማሰናበት በመሆኑ ስጋት እየሆነች መምጣቷን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።

ለዚህ ስጋት መነሻ የሆነው ደግሞ ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ እና መሳሪያ የደቀኑ ግለሰቦች፣ የቱርክ ስደተኞችን ከዋና መዲናዋ ናይሮቢ አፍነው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማደረጋቸው ነው።

እነዚህ አራት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስደተኛ መሆናቸው የተመዘገበ ቱርካውያን፣ የቱርክ መንግሥት በአገር መክዳት ወንጀል እንደሚፈልጋቸው በመግለጹ ተላልፈው አንደተሰጡ ተናግሯል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ እና የኬንያን መንግሥት ድርጊት የኮነኑ አካላት የአገሪቱ መንግሥት እስር እና እንግልትን ሸሽተው የሚሰደዱ ግለሰቦችን በግዴታ ወደ መጡበት አገር ያለመመለስ የኖረውን የተባበሩት መንግሥታትን መርኅ ወደ ጎን ብሏል ሲሉ ይተቻሉ።

ኬንያ የወሰደችው እርምጃ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የነበራትን መልካም ስም የሚያጠለሽ ተግባር ነው።

ይህንንም ተከትሎ ኃያላን አገራት ስጋት እንደገባቸው በአገሪቱ የሚታተመው ዴይሊ ኔሽን ጠቅሶ፣ የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ድርጅት ኃላፊዎች ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መነጋገራቸውን ዘግቧል።

የኬንያ የስደተኞች ኮሚሽንን የሚመሩት ጆን ቡሩጉ ጉዳዩን በሚመለከት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ኮሪር ሲንጎኤይ ግን፣ አገሪቱ የቆመችበትን መንታ መንገድ ሲያስረዱ “ትልቁ ጉዳይ ያለውን ፍላጎት ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል” ብለዋል።

አክለውም “ወዳጅ አገርን የሚጎዱ ተግባራትን ፈጽመዋል ተብለው የተከሰሱት አካላትን በሚመለከት ኬንያን በዲፕሎማሲ እና በሰብዓዊነት አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል” ብለዋል።

በስተመጨረሻም ኬንያ ከቱርክ ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት አደጋ ላይ ላለመጣል በሚል፣ ሁለቱ አገራት በሐምሌ ወር ወታደራዊ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ያታወሳል፣ ፖለቲካ ድል የቀናው መስሎ ታይቷል።

ኬንያን ከጎረቤቶቿ ጋር አነጻጽሮ የሚመለከታት ማንኛውም ሰው ለዓመታት ሰላም እና መረጋጋት ሰፍኖባት መቆየቷን በቀላሉ ያስተውላል።

ይህም ከኢትዮጵያ፣ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከኤርትራ፣ ከሩዋንዳ እና ከደቡብ ሱዳን ለሚመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ዋነኛ መዳረሻ አድርጓታል።

በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ኬንያ ከ800 ሺህ በላይ ስደተኞች ማረፊያ መሆኗን የስደተኞች ኮሚሽነሩ ጆን ቡሩጉ ተናግረዋል።

የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራቸው የሚደርስባቸውን እስር ሸሽተው ለሚሰደዱ ሰዎች ኬንያ ፊቷን እያዞረች መምጣቷን ጠቅሰው፣ ለደኅንነታቸው ስጋት እንደገባቸው ይናገራሉ።

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2022 የፓኪስታን ቴሌቪአዝን ዜና አንባቢ የነበረው አርሻድ ሻሪፍ በኬንያ ተተኩሶበት ተገድሏል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2022 የፓኪስታን ቴሌቪአዝን ዜና አንባቢ የነበረው አርሻድ ሻሪፍ በኬንያ ተተኩሶበት ተገድሏል

የኬንያ ፖሊስም በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ የደኅንነት ተቋማት ጋር በመመሳጠር በአገራቱ ስጋት ተብለው የተፈረጁ ሰዎችን በመያዝ ተከስሷል።

በቅርብ ጊዜ እንኳ የኡጋንዳው ኦብዘርቨር ጋዜጣ እንደዘገበው በሐምሌ ወር 36 የኡጋንዳ ተቃዋሚ ደጋፊዎች ላይ በተፈጸመው “ድንበር ተሻጋሪ አፈና” ውስጥ ተባባሪ ነው ተብሎ መከሰሱ ይታወሳል።

ቡድኑ በኬንያዋ ኪሱሙ ከተማ ለሥልጠና ተጉዞ እንደነበር ጠበቆቻቸው ገልጸዋል።

ነገር ግን ከአገር የመባረር ትዕዛዝ ወይም ተላልፎ የመሰጠት ጥያቄዎችን ያዘለ የሕግ መስመርን ሳይከተል ወደ ኡጋንዳ ተባረዋል።

የኡጋንዳ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ “በድብቅ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸው የኬንያ የፀጥታ ኃይሎችን ትኩረት ስቧል” ሲል ወንጅሏቸዋል።

ነገር ግን የቡድኑ አባላት በጠበቃቸው በኩል ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈፀሙ አስተባብለዋል።

"የኡጋንዳ የደኅንነት አባላት ወደ ኬንያ እንዲሻገሩ እንዲሁም ግለሰቦችን አፍነው እንዲወስዱ በማድረግ፣ ኬንያ በግዛቷ የሚገኙ ግለሰቦች ዜግነታቸው እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምንም ቢሆን ነፃነታቸው እና ደኅንነታቸውን የማስጠበቅ ግዴታዋን አልተወጣችም” ሲል ኦብዘርቨር በርዕሰ አንቀጹ ላይ አስነብቧል።

ባለፈው ግንቦት ወር ሩዋንዳዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ዩሱፍ አህመድ ጋሳና፣ ናይሮቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታፍኖ ተወስዶ እስካሁን ድረስ ያለበት አልታወቀም።

ምንጮች ለጋሳና ቤተሰቦች ግለሰቡ ከሌሎች እስካሁን ድረስ ክስ ካልተመሠረተባቸው ግለሰቦች ጋር በሩዋንዳ ምሥጢራዊ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሌሎች በኬንያ የተፈጸሙ አፈና እና እስሮች

  • ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መንግሥትን በመተቸት የሚታወቀው ደቡብ ሱዳናዊ ማቢዮር አዊክጆክ ባክ ናይሮቢ ውስጥ የኬንያ የፖሊስ የደንብ ልብስን በለበሱ ሰዎች ታፍኖ ተወስዷል። በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ሱዳን ታስሮ ይገኛል።
  • ፓኪስታናዊው ጋዜጠኛ አርሻድ ሻሪፍ ለደኅንነቱ በመስጋት ከፓኪስታን ወደ ኬንያ ከመጣ ከሁለት ወራት በኋላ በጥቅምት 2022 ከናይሮቢ ከተማ ወጣ ባለ ሥፍራ በፖሊስ በጥይት ተመትቶ ተገድሏል። ፖሊስ ስለ ጉዳዩ ሲያስረዳ ከሌላ ግለሰብ ጋር ማንነቱ በመመሳሰሉ መገደሉን ገልጿል።
  • ከናይጄሪያ ነጻነታቸውን ለማግኘት የሚታገሉት ናምዲ ካኑ እ.ኤ.አ. በ2021 በኬንያ አየር ማረፊያ ተይዘው ለናይጄሪያ የስለላ አገልግሎት ተላልፈው ተሰጥተዋል። አሁን በሽብር እና ሽብርን በማነሳሳት ክስ ተመሥርቶባቸዋል። ሁለቱም መንግሥታት በግለሰቡ መያዝ እጃቸው እንደሌለበት አስተባብለዋል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁን በኬንያ ጥገኝነት ለሚፈልጉ ሰዎች ሁኔታው አስፈሪ ነው።

ከ10 ዓመታት በላይ በኬንያ የኖረው እና የሩዋንዳን መንግሥት በመተቸት የሚታወቀው ሩዋንዳዊ ስደተኛ “ከተለያዩ ወገኖች በሚደርስብኝ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ምክንያት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለኝን ተሳትፎ አቁሜያለሁ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የ40 ዓመቱ ስደተኛ በኬንያ ያሉ ባለሥልጣናት እርሱን በሚመለከት መረጃ በማቀበል የሩዋንዳ ባለሥልጣናትን እየረዱ እንደሆነ ያምናል።

“ወደ አገሬ መመለስ ለእኔ እና ለቤተሰቤ አማራጭ አይደለም፤ ነገር ግን እዚህም በማያቋርጥ ፍርሃት ውስጥ ነው የምንኖረው” ይላል።

“ሸሽተናቸው በመጣናቸው ሰዎች የመያዝ ዕድላችን የሰፋ በመሆኑ እፈራለሁ።”

በኬንያ ያለባቸው ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ከ3,000 በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መንግሥታዊ ባልሆነው የኬንያ የስደተኞች ጥምረት ጥበቃ ስር ይገኛሉ።

የድርጅቱ ተመራማሪ የሆኑት ሻድራክ ኩዮህ እነዚህ ግለሰቦች በኬንያ ሲኖሩ መታሰርን፣ መከሰስን ወይም ተላልፎ መስጠትን በመፍራታቸው የተነሳ ለእርዳታ ወደ ጥምረቱ መምጣታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተመራማሪው፣ ስደተኞቹን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ የኬንያ የስደተኞች ሕግን የሚጥስ ነው ይላሉ።፡

“ጉዳት ሊደርስባቸው ወደሚችልባቸው አገራት እንዳይመለሱ” የሚለውን የስደተኞች ሕግ የተላለፈ ነው ሲሉም ያክላሉ።

የቱርክ ዜጎች ከኬንያ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።

አራቱ ግለሰቦች በኬንያ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ትምህርት ቤቶችን ያስተዳድር በነበረው በቱርካዊው የእስልምና መሪ ፌቱላህ ጉለን ስም የተሰየመው፣ የጉለን እንቅስቃሴ አካል እንደሆኑ ይታምኗል።

ቱርክ አሁን በሕይወት የሌሉት እና በ2016 የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥትን አቀነበባብረዋል በሚል ክስ የመሠረተችባቸው ጉለን ከሞቱ በኋላ ደጋፊዎቻቸውን እያሳደደች ማሰሯ ይታወሳል።

የኬንያ የሃይማኖቶች ምክር ቤት ሊቀ መንበር ጳጳስ ዊሊባርድ ኪቶጎ ላጎ አራቱን ቱርካውያን “ሰላም ወዳዶች” በማለት በሰብዓዊ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው እንደነበሩ ተናግረዋል።

“የእነሱ አፈና በኬንያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የደኅንነት ስጋታቸው እየጨመረ መምጣቱን አጉልቶ ያሳያል” ብለዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንታኝ ኤድጋር ጊቱዋ መንግሥት ራሱን ከትችት ለመከላከል ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም አሳልፎ መስጠት ነበረበት ይላሉ።

“ኬንያ ዓለም አቀፋዊ ገፅታዋን አበላሽታለች። ይህ ለዘመናት ሲጠቀስ ይኖራል። የሠራነውን መቀልበስ አንችልም” ይላሉ።