አንቶኒ ብሊንከን በመጪው ረቡዕ በአዲስ አበባ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሚቀጥለው ሳምንት ለጉብኝት ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዙ መሥሪያ ቤታቸው አስታወቀ።
ብሊንከን ከሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ መጋቢት 05 እስከ አርብ መጋቢት 08/2015 ዓ.ም. ወደ አፍሪካ ለጉብኝት እንደሚያቀኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው በዚህ ጉዟቸው ወደ ኢትዮጵያ እና ኒጀር ያቀናሉ ተብሏል።
አንቶኒ ብሊንከን መጋቢት 06/2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚያደርጉት ጉብኝት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን ለማስቆም የተደረሰው ስምምነት አተገባበርን እና በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
በተጨማሪም ከሰብአዊ እርዳታ አጋሮች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ጋር በመገናኘት በእርዳታ አቅርቦት፣ በምግብ ዋስትና እና በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ እንደሚወያዩ መሥሪያ ቤታቸው አመልክቷል።
ብሊንከን በአዲስ አበባው ቆይታቸው ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ጋር በዓለም አቀፋዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች፣ ከወራት በፊት በተካሄደው የአፍሪካ-አሜሪካ ጉባኤ ላይ ስለተነሱ ጉዳዮች ቀጣይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም አንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ ጉብኝት እንደሚያደርጉ እና ከከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ሐሙስ የካቲት 30/2015 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ መንግሥታት ግንኙነት ሻክሮ መቆየቱ ይታወሳል።
በጦርነቱ ወቅት በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያትም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫናዎችን የሚያሳድሩ እርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን፣ ከዚህም መካከል ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ለማስገባት ከሚያስችለው የአጎዋ መረሃ ግብር እንድትወጣ ተደርጓል።
ጦርነቱን ያስቆመው ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻልን እያሳየ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄደው የብሊንከን ጉብኝት ከጦርነቱ መቆም በኋላ በከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን የተደረገ የመጀመሪያው ጉብኝት ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ባለሥልጣናት መካከል በተደረሰው ስምምነት ውስጥ አሜሪካ ጉልህ ሚና እንደነበራት ይነገራል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ባለፈው ዓመት እና በዚህ ዓመት ለሁለት ጊዜ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት በማቅናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የአሁኑ በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ በአህጉሪቱ የሚያደርጉት ጉብኝት ነው።
ከፍተኛው የአሜሪካ መንግሥት የዲፕሎማሲ ባለሥልጣን በዚህ ጉዟቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ምዕራብ አፍሪካዋ ኒጀር በማቅናት ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።












