የመንግሥታቱ ድርጅት ቀይ ባሕር ላይ የተደቀነ አደጋን ለማስወገድ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ገዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የመን ባሕር ዳርቻ አካባቢ በአንዲት አሮጌ መርከብ ምክንያት በተፈጥሮ ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመቀልበስ በሚል ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ገዛ።
አደጋውን ታስከትላለች የተባለችው መርከብ እየበሰበሰ ባለ መጫኛዋ ከአንድ ሚሊዮን በርሜላ በላይ ድፍድፍ ነዳጅ ጭና ቀይ ባሕር ላይ ለዓመታት ቆይታለች።
ይህች አሮጌ ነዳጅ ጫኝ ግዙፍ መርከብ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ልትሰባበር አሊያም ልትፈነዳ ትችላለች የሚል ስጋት የፈጠረች ሲሆን፣ ይህም በቅርቡ ከተከሰቱት የባሕር ላይ ነዳጅ መፍሰስ አደጋዎች ሁሉ የካፋ ሊሆን ይችላlእ ተብሏል።
ሐሙስ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በመግዛት በቆመችው አሮጌ መርከብ ውስጥ ያለውን ድፍድፍ ነዳጅ ወደ አዲሱ እንደሚዘዋውር አስታውቋል።
“ይህንን ግዙፍ መርከብ የገዛነው ሊፈስ የተቃረውብ ነዳጅ በጥንቃቄ ቀድተን ሰብዓዊ እና አካባቢያዊ አደጋን ለመከላከል ነው” የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ባለሥልጣን አኺም ስታይነር ተናግረው “ይህ ትልቅ እርምጃ ነው” ብለዋል።
የመንግሥኣቱ ድርጅት አካል የሆነው ዩኤንዲፒ፤ መርከቧን በጣም ታዋቂ ከሆነ ዩሮናቭ ከተባለ ድርጅት እንደገዛም አስታውቋል።
“ነዳጁ ቢፈስ በቀይ ባሕር ዳርቻ የመን ውስጥ ላሉ ዓሳ አጥማጆች አደጋ ነው። 200 ሺህ ሰዎች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። በርካታ ሰዎች ሕይወትን ለሚያሰጋ አደጋ ሊጋለጡ ይችሉ ነበር። የተበከለ ውሃ ደግሞ ሚሊዮኖች ጋር ሊደርስ ይችላል” ይላሉ።
“አንድ ነገር ግልፅ ላድርግላችሁ። ይሄ አደጋ ያለበት ሥራ ነው። የሆነ ስህተት ልንሠራ እንችላለን” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ባልደረባ ተናግረዋል።
ዩኤንዲፒ አክሎ ነዳጁ ቢፈስ ለማፅዳት የሚወስደው ወጭ 20 ቢሊዮን ዶላር ሊጠጋ ይችላል ሲልም አመልክቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመርከቧ ምክንያት በቀይ ባሕር ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማስወገድ ለዓመታት መፍትሄ ሲያፈላልግ እና ለዚህም የሚያስፈልገውን ገንዘብ ልገሳ ሲጠይቅ ቆይቷል።
መርከቧ የምታስከትለውን አደጋ ለማስቀረት ለሚከናወነው ሥራ በድርጅቱ ለተያዘው ዕቅድ ማስፈጸሚያ 129 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም 75 ሚሊዮን ዶላር ሲገኝ 20 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ቃል ተግብቷል።
ኤፍኤስኦ ሴፈር የተባለችው ለዓመታ ባሕር ላይ የቆመችው አሮጌ መርከብ በየመን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሆዴያ ወደብ ተረስታ ትገኛለች።
መርከቧ ከፈረንጆቹ ከ2015 ዓመት ጀምሮ ጥገና ተደርጎላት አያውቅም።
በ1976 የተመረተችው መርከብ ለነዳጅ ማከማቻነት ስታገልግል ቆይታለች። በየመኑ የሁቲ አማፂያን የሚመራው ራስ ኢሳ የነዳጅ ማከመቻ አካባቢ ቆማ ትገኛለች።
376 ሜትር የምትርዝመው መርከብ በትንሹ 1.14 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ እንደያዘች ይገመታል።
መርከቧ በ2015 በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፈው የየመን አስተዳደር እና የሁቲ አማፂያን ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ እንክብካቤ የሚያደርግላት አጥታ እየዛገች መጥታለች።
የየመን የእርስ በርስ ጦርነት ቢያንስ 150 ሺህ ሰዎችን ቀጥፏል። ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ እርዳታ ፈላጊ ናቸው።












