የሜክሲኮ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን አሜሪካዊያንን ገድለዋል ያላቸውን አባላት ለፖሊስ አስረከበ

ሜክሲኮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ስኮርፒኖስ የተባለው ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን አራት አሜሪካዊያንን አፍኖ ሁለቱን በመግደሉ ይቅርታ ጠይቆ ገዳይ ናቸው ያላቸውን አባላት አሳልፎ ሰጥቷል።

በርካታ የሜክሲኮ ጋዜጦች አምስት ሰዎች የፊጥኝ ተጠፍረው፤ በለበሱት ካናቴራ ፊታቸው ተሸፍኖ መሬት ላይ ተዘርግተው ያለበት ምስል አትመዋል።

ፖሊስ ሥፍራው ሲደርስ አምስቱን ሰዎች ከዕፅ አዘዋዋሪው ቡድን የተፃፈ ደብዳቤ አግኝቷል።

ደብዳቤ ለማታሞሮስ ነዋሪዎች፣ ለተገደሉት አሜሪካዊያንና ቤተሰቦቻቸው፤ አልፎም አሜሪካዊያን ሲገደሉ በተባራሪ ጥይት ለተገደለች ሜክሲካዊት የተላከ ይቅርታ ነው።

ታማውሊፓስ በተሰኘው ግዛት ያሉ ሕግ አስካበሪዎች የደብዳቤውን ግልባጭ ሰጥተውኛል ሲል አሶሲዬትድ ፕረስ ዘግቧል።

“ለተፈጠረው ክስተት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ናቸው ያልናቸውን ሰዎች አሳልፈን ሰጥተናል” ይላል ደብዳቤው።

ደብዳቤው አክሎ እንደሚጠቁመው አምስቱ ሰዎች “እንደፈቀዳቸው ዲሲፒሊን የጎደለው ውሳኔ አሳልፈዋል” ሲል ይነበባል።

አምስቱ የቡድኑ አባላት “የንፁሃንን ሕይወት መጠበቅ” የተሰኘውን የዕፅ አዘዋዋሪው ቡድን መመሪያ ጥሰዋል ሲልም ይገልጣል።

የቡድን አባላት የቆሰሉትን አሜሪካዊያን ለማሳከም የወሰዱበት ክሊኒክ በፖሊስ ተከቦ ይገኛል።

ከአራቱ አሜሪካዊያን መካከል ሁለቱ፤ ሻይድ ውዳርድ እና ዚንዴል ብራውን ክፉኛ ቆስለው ብዙም ሳይቆይ ሕይወታቸው አልፏል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደፃፈው የሜክሲኮ ባለሥልጣናት የሁለቱን አሜሪካዊያን አስክሬን ሐሙስ ከሰዓት ለአሜሪካዊያን አስከረክበዋል።

አራቱ አሜሪካዊያን ወደ ማታሞሮስ ያቀኑት አንዷ ጓደኛቸው የኮስመቲክስ ቀዶ ሕክምና ማድረግ በመሻቷ መሆኑ ተሰምቷል።

የላታቪያ ማክጂ ሶስት ጓደኞች ወደ ሜክሲኮ ያቀኑት እሷን ለማጀብ እንጂ ሌላ ጉዳይ እንዳልነበራቸው ተዘግቧል።

ነገር ግን ሮይተርስ እንደሚለው ሶስቱ አሜሪካዊያን ከዚህ ቀደም ቀላል የሚባል ከዕፅ የተገናኘ ወንጀል ፈፅመው ያውቃሉ።

የሜክሲኮ ባለሥልጣናት አሜሪካዊያኑ የታፈኑት ስኮርፒኖስ፤ የተቀናቃኜ ቡድን አባላት ናቸው ብሎ በማሰቡ ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚያምኑ ሮይተርስ ዘግቧል።

የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት የአሜሪካ ጦር ኃይል የሜክሲኮ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል የሚል ሐሳብ አላቸው።

ሪፓብሊካኑ ሊንድዚ ግራሃም፤ ዕፅ አዘዋዋሪዎች “የውጭ አሻባሪ ኃይሎች” ተብለው እንዲሰይሙ ይሻሉ።

ይህን አስተያየት ተከትሎ የሜክሲኮው ፕሬዝደንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ኦብራዶር “ሜክሲኮ የአሜሪክ ቅኝ ግዛት” አይደለችም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርሴሎ ኤባርድም የአሜሪካዊው ፖለቲከኛ አስተያየት “ተቀባይነት የሌለው” ነው ብለዋል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል ሁኔታዎች ቢከሩም የአሜሪካው የሃገር ውስጥ ደኅንነት አማካሪ ሊዝ ሼርውድ ከፕሬዝደንት ሎፔዝ ኦብራዶር ጋር ለመምከር ሜክሲኮ ይገኛሉ።