በአፍጋኒስታን በተከሰተ ርዕደ መሬት ከ800 በላይ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በአፍጋኒስታን በተከሰተ ርዕደ መሬት ከ800 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በምሥራቃዊ አፍጋኒስታን እሁድ ከዕኩለ ሌሊት በፊት የተከሰተው ይህ ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 6.0 ተለክቷል።
የርዕደ መሬቱ ማዕከል በአፍጋኒስታን አምስተኛ ትልቋ ከተማ ጃላላባድ በ27 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ክልል ናት።
በክልሏ በመሬት መንቀጥቀጡ የተጠቁት ኩናል እና ናንጋርሃር የተሰኙት ግዛቶች ከመዲናዋ ካቡል በ140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛሉ።
አፍጋኒስታን ከፓኪስታን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ወድመው ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዳንድ መንደሮች ሙሉ በሙሉ የፈራረሱ ሲሆን፣ በርካታ ቤቶችም በፍርስራሾች ስር ተቀብረዋል።
ርዕደ መሬቱ በስምንት ኪሎ ሜትር ብዙም በማይባል ሁኔታ ጥልቀት ያለው በመሆኑ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።
ከመዲናዋ ካቡል እስከ ፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ያሉ ሕንጻዎች ተንቀጥቅጠዋል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች እርዳታ እንዲያደርሱ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ርዕደ መሬቱ የተከሰተበት አካባቢዎች በተራሮች የተከቡ ከመሆናቸው አንጻር ኮሙዩኒኬሽን ውስን ሆኗል። ባለሥልጣናት እስካሁን ባለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ቢሉም ጉዳቱ ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችልም እየተናገሩ ይገኛሉ።
ርዕደ መሬቱ ሌሊት ነዋሪዎች ተኝተው በነበረበት ወቅት በመከሰቱ በርካቶች ሳይነቁ በፍርስራሾች ስር ተቀብረው እንደሚገኙ ተፈርቷል።
በግዛቲቷ ባለው የመንገዶች ጥበት፣ አንዳንዶቹም በመሬት መንሸራተቱ በመዘጋታቸው ሕይወት የመታደግ ሥራን የተወሳሰበ አድርገውታል።
መንግሥት በርዕደ መሬቱ በተጎዱ አካባቢ ያሉ ማኅበረሰቦችን ለመድረስ ሄሊኮፕተሮች እየተጠቀመ መሆኑ ተነግሯል።
በሄሊኮፕተር የሰዎችን ሕይወት መታደግ እንደተቻለም ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
በተራራ በተከበቡት በእነዚህ መንደሮች ውስጥ ያለው የቤቶች ግንባታ በሸክላ፣ በጭቃ እና በድንጋይ ሲሆን የመሬት መንቀጥቀጥን የሚቋቋሙ አይደሉም።
በርካታ የመሬት መንቀጥቀጦችን በምታስተናግደው አፍጋኒስታን ከሁለት ዓመት በፊት በተከሰተ ተከታታይ ርዕደ መሬት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
በዚያ ወቅት ርዕደ መሬቱ ሄራት በተሰኘች ግዛት ነበር የተከሰተው።
ከሦስት ዓመታት በፊት ደግሞ ፓክቲካ በተሰኘች ግዛት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እንዲሁ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ተቀጥፏል።















