በአፍጋኒስታን በተከሰተ ርዕደ መሬት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ

ፍርስራሽ ላይ የተቀመጡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ርዕደ መሬቱ በርካታ መንደሮችን አፈራርሷል።

አፍጋኒስታን ከኢራን ጋር በምትዋሰንበት ምዕራባዊ ክፍል በተከሰተ ርዕደ መሬት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ።

ከገጠር አካባቢዎች አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ በመሆኑ የሟቾቹ ቁጥር ይጨምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አንድ የታሊባን መንግሥት መሥሪያ ቤት ቁጥሩ ከ2 ሺህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በአደጋው ተጎድተዋል።በርካታ ሕንጻዎች ፈራርሰዋል።ሰዎችም በፍርስራሾቹ ውስጥ ተቀብረዋል።

ቅዳሜ ዕለት ከጠዋቱ 3፡30 አካባቢ በተከሰተው እና በ6.3 ሬክተር ስኬል በተለካው ርዕደ መሬት በሔራት ከተማ አቅራቢያ የሚገኙ ቢያንስ 12 መንደሮች ወድመዋል።

የመጀመሪያ ርዕደ መሬት ከተከሰተ በኋላም ከባድ የመሬት መንቀጥቀጦች አጋጥመዋል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች በፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው ያሉ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ጥረታቸውን ቀጥለዋል።

የሔራት ነዋሪ የሆነው ባሺር አሕመድ ስለተፈጠረው ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ሲናገር “ ቢሯችን ውስጥ ነበርን። ድንገት ሕንጻው መንቀጥቀጥ ጀመረ። የግድግዳው ምርጊት መርገፍ ጀመረ ። ከዚያም ግድግዳው ተሰነጠቀ ። የተወሰነ ግድግዳው እና የሕንጻው አካል ፈረሰ።” ብሏል።

ባሺር “ ቤተሰቦቼን ማግኘት አልቻልኩም። ኔትወርክ ጠፍቷል። በጣም ተጨንቄያለሁ፣ ሰግቻለሁም። በጣም የሚሰቀጥጥ ነበር።” ሲልም ያለበትን ሁኔታ ተናግሯል።

ደጅ ላይ የተሰበሰቡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ርዕደ መሬቱ ካጋጠመ በኋላ በርካታ ሰዎች በሔራት ከሚገኙ ሕንጻዎች ውስጥ ወጥተዋል።

የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ የተለያዩ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

የሔራት ሆስፒታል ዳይሬክተር ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስካሁን ቢያንስ 225 ሰዎች በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ወደ 500 የሚጠጉ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ሌሎች ደግሞ የአደጋው ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ቁጥር ከተጠቀሰው እንደሚበልጥ ገልጸዋል።

ቅዳሜ ዕለት ቀደም ብሎ የግዛቷ የአደጋ መከላከል ኃላፊ ሞሳ አሻሪ፣ “ እስካሁን ጉዳት የደረሰባቸው ከ1 ሺህ በላይ ሴቶችን፣ ሕጻናትን እና አረጋውያንን እንዲሁም 120 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ማለፉን መዝግበናል።” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።

ከሔራት ሴንትራል ሆስፒታል የወጡ ምስሎችም ከሆስፒታሉ ሕንጻ ውጭ ግሉኮስ የተተከለላቸው በርካታ ሰዎች ሕክምና ሲደረግላቸው አሳይተዋል።

ሌሎች ምስሎች ደግሞ በሔራት ኢንጂል ድስትሪክት መንገዶች በፍርስራሽ በመዘጋታቸው የነፍስ አድን ሥራውን እንዳስተጓጎሉ ያሳያሉ።

ኢድሪስ አርሳል የተባለ ተማሪ “ ሁኔታው በጣም አስፈሪ ነበር። ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ገጥሞኝ አያውቅም።” ሲል ለኤኤፍፒ ተናግሯል። ኢድሪስ ርዕደ መሬቱ ካጋጠመ በኋላ መጨረሻ ላይ ከመማሪያ ክፍሉ በሰላም የወጣ ተማሪ ነው።

ሔራት ከምሥራቃዊ የኢራን ድንበር 120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን የአፍጋኒስታን ባሕላዊ መዲና እንደሆነች ይታሰባል።

በግዛቷም 1.9 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል።

በአፍጋኒስታን በርዕደ መሬት ስትመታ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ፓክቲካ ግዛት 5.9 መጠን በተለካ ርዕደ መሬት ተመትታ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቤት አልባ ሆነዋል።