በአፍጋኒስታን የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ ታሊባን ዓለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስለት ተማጸነ

በመሬት መንቀጥቀጡ የፈራረሱ ቤቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአፍጋኒስታን ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለውን ጉዳት ለመቋቋም ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግለት ታሊባን ጠይቋል።

በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ 1 ሺ ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 1500 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ደግሞ በፍርስራሾች ውስጥ ይገኛሉ።

በደቡባዊ ምስራቅ የምትገኘው ፓካቲካ የተሰኘችው ግዛት በአደጋው ክፉኛ የተመታች ሲሆን ተመድ ጊዜያዊ መጠለያዎችን ለመገንባት እና ምግብ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ነው።

አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመታደግ የሚደረገው ጥረት በከባድ ዝናብ እና ስራውን ለማከናወን በሚያስፈልጉ መሳሪያዎች እጥረት መስተጓጎል ገጥሞታል።

የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተበት ዋንኛ ነጥብ ዙሪያ ያሉ መንደሮች እና የሞባይል ስልክ መሸጫህንጻዎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ለቢቢሲ የገለጹት ከአደጋው የተረፉ እና የነፍስ አድን ሰራተኞች የሟⶇች ቁጥር ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል የሚል ስጋት አለን ብለዋል።

በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የተከሰተው ይህ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ በምዕራባውያን የሚደገፈው መንግስት ወድቆ ታሊባን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ታላቅ ክስተት ነው።

የመሬት መንቀጥቀጡ ኮሆስት በተሰኘችው ከተማ 44 ኪሎ ሜትር የሸፈነ እና ፓኪስታን እና ህንድ ድረስ የተሰማ ነው።

ቀድሞም በኢኮኖሚያዊ እና ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኘውን አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ ያለው የታሊባን ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አዱል ቃሃር ባልካሂ መንግሥት ያለው የገንዘብ አቅም እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችን በሙሉ ተደራሽ ማድረግ አይችልም ብለዋል።

የአርዳታ ተቋማት፥ ጎረቤት እና ሃያላን ሀገራት እረዱን ነው ያሉት ባለስልጣኑ ሆኖም “እርዳታው በከፍተኛ መጠን ሊያድግ ይገባዋል። ምክንያቱም ይህ በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ነው” ብለዋል።

የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ድርጅቱ አደጋውን ለመመከት በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ ነውብለዋል። ድርጅቱ የጤና ቡድን፥ የህክምና ቁሳቁስ፥ ምግብ እና ጊዜያዊ መጠለያዎች ወደ ስፍራው እየላከ መሆኑም ተገልጻል።