በአፍጋኒስታን በቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ርዕደ መሬት ተከሰተ

በቅዳሜው ርዕደ መሬት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

የምስሉ መግለጫ, በቅዳሜው ርዕደ መሬት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል

በአፍጋኒስታን ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ከተሰማ ከጥቂት ቀናት በኋላ በተመሳሳይ አካባቢ ዳግም ርዕደ መሬት ተከስቷል።

ሁለተኛው ርዕደ መሬት ዛሬ ርዕቡ ማለዳ የተከሰተ ሲሆን፣ የመጀመሪያው መንቀጥቀት ተከስቶ ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰው ደግሞ ባለው ቅዳሜ ነበር።

የመሬት መንቀጥቀጡ ዋነኛ ማዕከል ኼራት ተብላ ከምትጠራው ከተማ 28 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኝ ስፍራ ነው።

ዛሬ የተከሰተው የመሬት ነውጥ ያስከተለው የጉዳት መጠን እስካሁን አልታወቀም። ሆኖም በርካቶች በመጀመሪያው መንቀጥቀጥ ምክንያት ቤታቸው በመውደሙ ላለፉት ቀናት ከቤት ውጪ ለመተኛት መገደዳቸው ይታወቃል።

በተጨማሪም ቀደም ባለው ርዕደ መሬት ሳቢያ ለችግር ለተጋለለጡ አፍጋናውያን የሚሆን ብርድ ልብስ፣ የምግብ እና ሌሎች አቅርቦቶች እጥረትም ተከስቷል።

የቅዳሜ ጠዋቱ ርዕደ መሬት ኼራት ከተሰኘችው ከተማ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ዚንዱጃን በተባለች አካባቢ ነበር የተከሰተው።

ከዚንዱጃን የወጡ ምሥሎች እንደሚያሳዩት በአካባቢው ያሉ መኖሪያ ቤቶች የተከሰተውን አይነት ጠንካራን ርዕደ መሬትን መቋቋም የማይችሉ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ ፈራርሰው አሳይተዋል።

ቅዳሜ የተከሰተው ርዕደ መሬት በ6.3 ማግኒቲዩድ የተለካ ሲሆን፣ በጭቃ የተሰሩ ቤቶች በብዛት የሚገኙባቸው መንደሮች ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል።

አደጋው ከተከሰተ ቀናት ቢቆጠርም የመንደሮቹ ነዋሪዎች አሁንም የደረሱበት ያልታወቀ ከ500 በላይ ሰዎችን ከፍርስራሽ ውስጥ ለመፈለግ አካፋ እና ባዶ እንዲሁም እጃቸውን እየተጠቀሙ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ገልጾ ነበር።

በአደጋው ምክንያት መንገዶች በመዘጋታቸው እና የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው ለተጎጂዎች እርዳታ በአፋጣኝ ሊደርስላቸው አልቻለም። በትንሹም ቢሆን እርዳታ መጓጓዝ የጀመረው ባለፈው ሰኞ ነበር።

በዚህም የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ኔክ መሐመድ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ “ወደዚህ መጥተን ምንም የተረፈ ነገር እንደሌለ አይተናል።ሁሉም ነገር ወደ አፈርነት ተቀይሯል። ሴቶች እና ሕጻናትን ከፍርስራሹ ውስጥ ለማውጣት በአካፋ እና ባለን ማንኛውም ነገር መቆፈር ጀምረናል” ብለዋል።

የታሊባን መንግሥት እና የእርዳታ ድርጅቶች መጀመሪያ ላይ የሟቾቹን እንዲሁም የጠፉ ሰዎችን ቁጥር ለመገመት ተቸግረው ነበር።

ባለሥልጣናትም በእንደዚህ ዓይነት መንደሮች ውስጥ ምን ያህል ሰዎች ይኖሩ እንደነበር የሚገልጽ መረጃ ስለሌላቸው የሟቾችን ቁጥር በትክክል ለማወቅ አልተቻለም።

አፍጋኒስታን ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት የሚመታት አገር ናት።