በአፍጋኒስታኑ ርዕደ መሬት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
ቅዳሜ ዕለት በተከሰተው እና በአፍጋኒስታን የሚገኙ መንደሮችን ወደ ፍርስራሽነት በቀየረው ከባድ ርዕደ መሬት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሞቱ።
የነፍስ አድን ሠራተኞች አሁንም ከፍርስራሽ ውስጥ ሰዎችን ለማውጣት እየጣሩ ነው።
በ6.3 ማግኒቲዩድ የተለካው ርዕደ መሬት በሔራት ግዛት በጭቃ የተሰሩ ቤቶች በብዛት የሚገኙባቸው መንደሮች ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል።
አደጋው ከተከሰተ አራተኛ ቀኑን ቢይዝም የመንደሮቹ ነዋሪዎች አሁንም የደረሱበት ያልታወቀ ከ500 በላይ ሰዎችን ከፍርስራሽ ውስጥ ለመፈለግ አካፋ እና ባዶ እጃቸውን እየተጠቀሙ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
መንገዶች በመዘጋታቸውና የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው እርዳታ በአፋጣኝ ሊደርስላቸው አልቻለም። በትንሹም ቢሆን እርዳታ መጓጓዝ የጀመረው ትናንት ነው።
በዚህም የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚሉ ስጋቶች አሉ።
ርዕደ መሬቱ ከሔራት ከተማ 40 ኪሎ ሜትር የምትርቀውን ዚንዳጃን የምትባል የገጠር ወረዳ ክፉኛ የመታ ሲሆን እንደ የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ከሆነ ሁሉም ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
ከመንደሮቹ የወጡ ምስሎችም ቤቶቹ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረው አሳይተዋል።
ኔክ መሐመድ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ “ ወደዚህ መጥተን ምንም የተረፈ ነገር እንደሌለ አይተናል።ሁሉም ነገር ወደ አፈርነት ተቀይሯል።ሴቶች እና ሕጻናትን ከፍርስራሹ ውስጥ ለማውጣት በአካፋ እና ባለን ማንኛውም ነገር መቆፈር ጀምረናል።” ብለዋል።
የታሊባን መንግሥት እና የእርዳታ ድርጅቶች መጀመሪያ ላይ የሟቾቹን እንዲሁም የጠፉ ሰዎችን ቁጥር ለመገመት ተቸግረው ነበር።
ባለሥልጣናትም በእንደዚህ ዓይነት መንደሮች ውስጥ ምን ያህል ሰዎች ይኖሩ እንደነበር የሚገልጽ መዝገብ አይኖራቸውም።
አካባቢው በጦርነቱ እና ድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች መኖሪያ በመሆኑም ምን ያህል ሰዎች እንደሚኖሩ ለማወቅ ለአካባቢው አስተዳዳር አዳጋች ነው።
በታመሙ ሰዎች የተያዙት ሆስፒታሎችም አሁን ላይ ቁጥራቸው ከ1 ሺህ 600 በላይ የደረሱ የተጎዱ ሰዎችን ለማስተናገድ እየተፈተኑ ነው።
አብዛኞቹም ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የህክምና ቡድን ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ ወደሚገኙበት ሔራት ሪጂናል ሆስፒታል ተልከዋል።

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
በአፍጋኒስታን የድርጅቱ ተወካይ ሆነው እያገለገሉ ያሉት ፒሩ ኮክሌይ “ እዚህ የሚመጡት አብዛኞቹ ህሙማን አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው አይደሉም።
ሆኖም አብዛኞቹ ተመልሰው የሚሄዱበት ቤት ስሌላቸው ነው እዚሁ ሆስፒታል ውስጥ የቀሩት።ባለሥልጣናት የሚያርፉባቸውን አማራጭ ቦታዎች እየፈለጉላቸው ነው።” ብለዋል።
ፒሩ ጨምረውም የሕክምና ቡድኑ ወደ ሆስፒታሉ በተላኩ ህሙማን ህጻናት ላይ ማተኮሩን ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት እንደገለጸው አብዛኞቹ ከአደጋው ተርፈው በሆስፒታሉ ሕክምና እየተደረገላቸው ያሉት ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው።
ከሟቾቹ መካከልም አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን ሐኪሞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የታሊባን መንግሥት ከአደጋው የተረፉ ሰዎች አስቸኳይ ምግብ፣ የመጠጥ ውሃ ፣ መድሃኒት፣ አልባሳት እና መጠለያ ድንኳኖች እንደሚያስፈልጋቸው ተናግሯል።
የአፍጋኒስታን ቀይ መስቀል ማኅበር፣ ኤምኤስኤፍ፣የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኒሴፍን ጨምሮ በርካታ የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ እየላኩ ነው።
ሆኖም ድርጅቶቹ መንቀሳቀሻ ገንዘብ የሌላት አገሪቱ ተጨማሪ ድጋፍ ትፈልጋለች ብለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2021 ታሊባን ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ አፍጋኒስታን በምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ለመንግሥት ይሰጥ የነበረው እርዳታም ቆሟል።
ሆኖም ቅዳሜ ዕለት ከተከሰተው ርዕደ መሬት በኋላ ጥቂት አገራት እጃቸውን ዘርግተውላታል።
የቻይና ቀይ መስቀል ማኅበር ለአስቸኳይ ጊዜ 200 ሺህ ዶላር የሚሆን ገንዘብ መስጠቱን የቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ጎረቤት አገሯ ፓኪስታንም ከአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገረች መሆኑን ገልጻ፣ ከአደጋው እንድታገግም በሚደረገው ጥረት የሚቻላትን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብታለች።
አፍጋኒስታን በተደጋጋሚ በርዕደ መሬት ተመታለች።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ፓክቲካ ግዛት በ5.9 ማግኒቲዩድ ርዕደ መሬት ተመትታ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት አልባ ሆነዋል።












