ቲክቶክ ላይ ዶክተር ነኝ ብሎ የሕክምና ምክር ሲሰጥ የነበረው ደቡብ አፍሪካዊ ተከሰሰ

ታብሌት የያዘ የሕክምና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በቲክቶክ ማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ የአንድ ሆስፒታል ዶክተር ነኝ ብሎ አቅርቧል የተባለው ግለሰብ የወንጀል ክስ ተመሠረተበት።

በቲክቲክ ላይ እራሱን ዶ/ር ማቲው ላኒ ብሎ በሐሰት ማንነት እንደ ሕክምና ዶክተር ሲቀርብ የነበረው ግለሰብ በጤና ባለሥልጣናት ተደርሶበት ነው የተከሰሰው።

በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ይገኛል የተባለው ግለሰብ የሐኪሞችን ልብስ በመልበስ በአንድ የሕዝብ ሆስፒታል ውስጥ ሆኖ ቲክቶክ ላይ በመቅረብ የሕክምና ምክር ሲሰጥ ነበር ተብሏል።

ግለሰቡ “በደቡብ አፍሪካዋ ጉዋቲንግ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ሄለን ጆሴፍ ሆስፒታል ውስጥ በመግባት ሠራተኛ በመምሰል እየተንቀሳቀሰ ድርጊቱን መፈጸሙን የግዛቲቱ ጤና ቢሮ ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በዚህም ሳቢያ አንድ ሰው በደቡብ አፍሪካ የጤና ባለሙያዎች ምክር ቤት ሳይመዘገብ የሕክምና ሥራ ላይ ከተሰማራ የወንጀል ድርጊት ነው በማለት ባለሥልጣናት ግለሰቡን ከሰውታል።

ግለሰቡ “በርካታ ሐሰተኛ የሕክምና ሙያዎች እንዳሉት በመግለጽ፣ እራሱን በሆስፒታሉ ውስጥ ሠራተኛ አድርጎ በማቅረብ” የሌሎችን ሐኪሞች ስም በመጠቀም ነው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲቀርብ የነበረው ተብሏል።

ተከሳሹ ስሙን አስመስሎ የተጠቀመበት የሁለተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪም ግለሰቡ ማንነቴን ተጠቅሞ በስሜ ሲያጭበረብር ነበር በሚል በግለሰቡ ላይ ክስ መሥርቷል።

ዶክተር ነኝ እያለ በቲክቶክ ላይ ሲቀርብ የነበረው ግለሰብ፣ እዚያው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኘው የዋይትዋተርስራንድ የሕክምና ትምህርት ቤት ምሩቅ እንደሆነ እና በአገሪቱ የመድኃት ማምረቻ ድርጅት ያለው “ወጣቱ” ዶክተር እንደሆነ ሲገልጽ ነበር።

ተምሬበታለሁ ያለው ዩኒቨርስቲ ጉዳዩን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ ላይ ግለሰቡ ዶክተር ነኝ ብሎ የሚጠቀምባቸው ስሞች ያሉት ተማሪን “በቅርብ ዓመታት ውስጥ አስተምሮ ካስመረቃቸው ተማሪዎች ዝርዝር ውስጥ ማግኘት አልቻልኩም” ብሏል።

የዋይትዋተርስራንድ የሕክምና ትምህርት ቤት ጨምሮም ግለሰቡ ተመራቂው እንደሆነ እና የሕክምና ዶክተር ነኝ በማለት የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮቹን ሲያጭበረብር መቆየቱን አምኖ ድርጊቱን በአስቸኳይ እንዲያስተባብል ጠይቋል።

የጉዋቲንግ ግዛት ባለሥልጣናትም እንዲህ አይነቱን ሐሰተኛ ድርጊቶች ለመቆጣጠር ወደ ሕክማና ተቋማት የሚገቡ ሰዎችን ማንነት የመለየቱን ሥራ ማሻሻል እና የተቋማቱ ሠራተኞች የሚለዩበትን ሂደት ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ገልጿል።

ዶ/ር ማቲው ላኒ ሐሰተኛ መሆኑ ከታወቀ እና በባለሥልጣናት ክስ ከተመሠረተበት በኋላ ይጠቀምበት የነበረው የቲክቶክ ገጽ የማይታይ ሆኗል።

በተለያዩ አገራት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን በመጠቀም ሰዎች የተለያዩ የማጭበርበር ድረጊቶች ከመፈጸማቸው ባሻገር፣ ጤናን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ባለሙያ መስለው በመቅረብ የተሳሳቱ መረጃዎችን እውነተኛ አስመስለው በማቅረብ ተከታዮቻቸውን ለጉዳት እየዳረጉ መሆናቸው ይነገራል።