ሶማሊያ ቲክቶክ እና ቴሌግራምን አገደች፣ የኬንያ ምክር ቤት ቲክቶክን በማገድ ላይ ተወያየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሶማሊያ ቲክቶክ እና ቴሌግራም የተባሉትን ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እንዲሁም 1ኤክስቤት (1XBet) የተባለውን የስፖርት ውርርድ ገጽን እንዲዘጉ አዘዘች።
በወጣቶች ዘንድ ሰፊ ተጠቃሚ የላቸው ቲክቶክ እና ቴሌግራም የአሸባሪዎች መረጃ ማስተላለፊያ ሆነዋል ብሏል የሶማሊያ መንግሥት።
መተግበሪያዎቹ “አሸባሪ ድርጅቶች እና ቡድኖች አሰቃቂ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንዲሁም ፎቶግራፎችን በማሰራጨት ሕብረተሰቡን ለማሳሳት ጥቅም ላይ ውለዋል” ብሏል የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው መግለጫ።
የሶማሊያ የኮሚዩኒኬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ ያሉ የኢንተርኔት አግልግሎት አቅራቢዎች እስከ ሐሙስ ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም. ድረስ ትዕዛዙን ተግባራዊ የማያደርጉ ከሆነ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ቲክቶክ እና ቴሌግራምን እንዲሁም የስፖርት ውርርድ ገጹን የመዝጋት ውሳኔ የተሰማው የሶማሊያ መንግሥት አልሸባብን ለማጥፋት ዘመቻ ከጀመረች በኋላ ነው።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኘውን ጸንፈኛውን እስላማዊ ቡድን አል-ሸባብን በአምስት ወራት ውስጥ አጠፋለሁ ብለው ነበር።
በቅርቡ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ ኢንተርኔት እና ማኅበራዊ ሚዲያን በተመለከተ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና ኢንተርኔት በአጠቃላይ በተለይ በወጣቱ ላይ “ሕይወት እስከ ማሳጣት” የሚደርስ ጉዳት እያደረሰ ነው የሚል ሃሳብ በስፋት ተንጸባርቆ ነበር።
በኬንያም እንዲሁ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለውን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ቲክቶክን ለማገድ የሚያስችል ሃሳብ በምክር ቤቱ ቀርቧል።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በአንድ የፓርላማው በቀረበው የእገዳ ሃሳብ ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ የአገሪቱ እንደራሴዎች የኬንያን የባህል እና የሃይማኖት እሴቶችን አደጋ ላይ ጥሏል በተባለው ቲክቶክ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
ይህ የእግድ ጥያቄ የተነሳው ኬንያ ቲክቶክን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ ሕግ ስለሌላት ጉዳት የሚያስከትሉ እና ተገቢ ያልሆኑ ይዘቶች በመድረኩ ላይ በስፋት እንዲቀርቡ ምክንያት ሆኗል በሚል ነው።
በዚህም “ቲክቶክ በኬንያውያን በወጣቶች ዘንድ ተዘውታሪ በመሆኑ፣ ግጭቶችን በማባባስ፣ ልቅ ወሲብን በማስፋፋት፣ የጥላቻ ንግግሮችን፣ የብልግና ቃላትን፣ አደገኛ ባሕሪያትን በማስፋፋት ለአገሪቱ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች ጠንቅ እየሆነ ነው” በማለት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ሞሰስ ዊታንጉላ ተናግረዋል።
ቲክቶክ እንዲታገድ ጥያቄ ያቀረቡት ግለሰብም፣ ምክር ቤቱ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩን የሚያግደው ከሆነ፣ በወጣቶች ዘንድ እየተስፋፋ ያለውን ሱሰኝነት እና የአእምሮ ጤና ችግርን ለመከላከል ይቻላል ብለዋል። ጨምረውም የቲክቶክ መተግበሪያ በሕገወጥ መንገድ የኬንያውያንን ግላዊ መረጃ በመሰብሰብ እና በማጋራት ተጠያቂ ነው ብለዋል።
የቀረበውን ሃሳብ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የደገፉት ሲሆን ሌሎች ደግሞ እገዳው ኬንያውያንን ከቴክኖሎጂ የሚያርቅ እና በቲክቶክ ላይ ይዘቶችን በማቅረብ ገቢ የሚያገኙ ወጣቶችን የሚጎዳ ነው በማለት ተቃውመውታል።
ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸውን የምክር ቤቱ አባላትን ጨምሮ አንዳንድ እንደራሴዎች ደግሞ ተክቶክን ሙሉ ለሙሉ ከማገድ ይልቅ በይዘቶቹ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግ ደንብ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባይትዳንስ በተባለው የቻይና ኩባንያ ባለቤትነት የሚተዳደረው ቲክቶክ የተሰኘው መተግበሪያ እገዳ እና ክስ ሲገጥመው ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለይ ደግሞ በወጣቶች ዘንድ በርካታ ተጠቃሚዎችን ማፍራት የቻለው ቻይና ሰራሹ ቲክቶክ፣ የደኅንነት ስጋት አለበት በሚል ምዕራባውያን አገራት መተግበሪያውን በበጎ አይመለከቱትም።
በቅርቡ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ያሉ አገራት በመንግሥታዊ ተቋማት ላይ መተግበሪያው ጥቅም ላይ እንዳይውል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ምንም እንኳ አሜሪካ በመንግሥታዊ ተቋማት ላይ መተግበሪያውን መጠቀም አይቻልም በማለት ክልከላ ብታስተላልፍም በዓለም ቀዳሚው የቲክቶክ ተጠቃሚዎች አሜሪካውያን ናቸው።
እንደ ስታቲስታ ከሆነ ባለንበት የአውሮፓውያን 2023 ዓመት 113 ሚሊዮን አሜሪካውያን የቲክቶክ ተጠቃሚ በመሆን በዓለም ቀዳሚ ናቸው። ቲክቶክ በኢንዶኔዚያ 110 እንዲሁም በብራዚል 82 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።
ተጠቃሚዎች አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ቀርጸው ከሙዚቃ ጋር እያዋሃዱ እንዲሰሩ እና ለሌሎች እንዲያጋሩ የሚያስችለው መተግበሪያው፣ ካሉት በአጠቃላይ 1.7 ቢሊዮን ተጠቃሚዎቹ መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ባሉት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ናቸው።












