በኢራቅ ግዙፍ የማስታወቂያ ስክሪን ላይ የወሲብ ፊልም በመታየቱ ባለሥልጣናት እርምጃ ወሰዱ

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ውስጥ በሚገኝ ጎዳና ላይ ባለ ግዙፍ የማስታወቂያ ስክሪን ተጠልፎ ልቅ የወሲብ ቪዲዮ መታየቱ የአገሪቱን ባለሥልጣናት አስቆጥቶ እርምጃ እንዲወስዱ አደረገ።
መሃል ባግዳድ በተተከለው ግዙፍ ስክሪን ላይ የወሲብ ቪዲዮው ከታየ በኋላ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በመላው ባግዳድ ያሉ የማስታወቂያ ስክሪኖች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
በርካታ እንቅስቃሴ ያለባቸው ሁለት አውራ ጎዳናዎች በሚገናኙበት መንገድ ላይ የተተከለው ግዙፍ ስክሪን ከተጠለፈ በኋላ፣ ልቅ የወሲብ ፊልም ሲታይበት የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተሰራጭተዋል።
ከክስተቱ ጋር በተያያዘ አንድ ግለሰብ የስክሪኑን ማዕከላዊ ሥርዓት ጠልፎ ፊልሙን አሳይቷል ተብሎ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የባግዳድ ፖሊስ አስታውቋል።
እንደ ፖሊስ መግለጫ ከሆነ ግለሰቡ የማስታወቂያ ስክሪኖቹን የሚያስተዳድር ኩባንያ ቅጥር ሠራተኛ ሲሆን፣ በክፍያ ምክንያት ከቀጣሪው ድርጅት ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብቷል ብሏል።
ፖሊስ እንደሚለው ግለሰቡ ስክሪኑን ጠልፎ ፊልሙን ያሳየው ኩባንያውን ለመጉዳት በበቀል ተነሳስቶ ነው።
የፈረንሳዩ ዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) በስም ያልጠቀሳቸው አንድ የፖሊስ አባል ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ዕለት ባጋጠመው ክስተት ልቅ ፊልሙ ለረዥም ደቂቃዎች ታይቷል።
“የስክሪኑን ሶኬት ነቅለን እስክናጠፋው ድረስ ጠላፊው ልቅ የወሲብ ፊልሙን ለበርካታ ደቂቃዎች አሳይቷል” ብለዋል የፖሊስ አባሉ።
ይህ “ከሥነ-ምግባር ያፈነገጠ” ድርጊት ነው ያሉት የአገሪቱ ባለሥልጣናት፣ በባግዳድ ከተማ የሚገኙ የማስታወቂያ ስክሪኖች በሙሉ እንዲዘጉ ትዕዛዝ እንዲሰጡ ምክንያት ሆኗል ብለዋል ይህ የፖሊስ አባሉ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል።
በመላው ባግዳድ የተሰቀሉት ግዙፍ ስክሪኖች ምርት እና አገልግሎቶችን እንዲሁም የፖለቲከኞችን የምረጡኝ ቅስቀሳ ለሕዝብ የሚቀርቡባቸው መድረኮች ናቸው።
የከተማዋ አስተዳዳሪዎች ስክሪኖቹ ዝግ እንዲሆኑ መወሰናቸውን ተከትሎ፣ ከእሁድ ንጋት ጀምሮ ግዙፎቹ የማስታቂያ ስክሪኖች ጥቁር ሆነው ታይተዋል።












