ኢራን በእስራኤል ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ድጋፏን ሰጥታ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሐማስ ታጣቂዎች ከፍተኛ ቅንጅት ታይቶበታል የተባለውን ጥቃት በእስራኤል ላይ መፈጸማቸውን ተከትሎ የኢራን ስም በተደጋጋሚ እየተነሳ ይገኛል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ኢራን በጥቃቱ ተሳትፎ ነበራት ወይ? የሚለው ጥያቄ ከተለያዩ ወገኖች እየተመላለሰ የሚነሳ ሆኗል።
ዋል ስትሪት ጆርናል ስማቸውን ያልጠቀሳቸው የሐማስ እና የሊባኖሱ ሽምቅ ተዋጊ ሄዝቦላህ አባላትን ዋቢ አድርጎ ኢራን ጥቃቱ እንዲካሄድ ከሳምንት በፊት ፍቃድ መስጠቷን አስነብቧል።
ነገር ግን የአሜሪካ መከላከያ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑ አንድ ግለሰብ በጥቃቱ ኢራን ነበራት ስለተባለው ሚና የሚያረጋግጥ “ምንም መረጃ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ አላገኘችም” ብለዋል።
ከዚህ ጥቃት ጀርባ ኢራን መኖሯ ከተረጋገጠ ግጭቱን ቀጣናዊ በማድረግ ሊያሰፋው ይችላል።
ምንም እንኳን የኢራን መሪዎች ለደረሰው ጥቃት ድጋፋቸውን እንዲሁም አድናቆታቸውን ቢገልጹም ምንም አይነት ተሳትፎ የለንም በሚልም ምላሽ የሰጡት በፍጥነት ነው።
“ከኢራን ሚና ጋር የተገናኘው ውንጀላ በፖለቲካዊ ምክንያቶች ላይ የተመሠረተ ነው” ሲል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኢራን “በሌሎች አገሮች ውሳኔ ላይ ጣልቃ አልገባችም” ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
በኢራን ላይ ሰበብ የምትፈልገው አሜሪካ ኢራን ከጥቃቱ ጀርባ ስለመኖሯ የሚያሳይ ማስረጃ “እካሁን አላገኘንም” ብላለች።
ነገር ግን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን “በእርግጠኝነት ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት አላቸው” ሲሉ የሐማስን እና የኢራንን ግንኙነት ጥብቅ መሆን ገልጸውታል።
ከእስራኤል አንጻር ከሐማስ ጋር ተመሳሳይ አቋም ያላት የባሕረ ሰላጤዋ አገር ኢራን ለበርካታ ዓመታት ለፍልስጥኤማዊው ቡድን ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች።
የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ሮኬቶች እና ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያም ለሐማስ ለግሳለች።
ኢራን ጋዛን ለሚያስተዳድረው ሐማስ የምታደርገውን የመሳሪያ አቅርቦት መስመርን ለማስተጓጎልም እስራኤል ለበርካታ ዓመታት ጥራለች።
ይህ የአቅርቦት መስመር ሱዳን፣ የመን እንዲሁም በቀይ ባሕር ያሉ መርከቦች እና በሲናይ በረሃ ያሉ የቤዱዊን አዘዋዋሪዎችን ያሳተፈ ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA/EFE/REX
ኢራን እስራኤልን በጠላትነት ከማየቷ አንጻር በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ያለውን የአይሁድ መንግሥት ጥፋት እና ጉዳትን ማየት ፍላጎቷ ነው።
“ኢራን ተሳትፋለች ብሎ መገመት ብዙም ማሰብ አያስፈልገውም” ሲሉ የእስራኤል የውጭ የስለላ ድርጅት፣ ሞሳድ የቀድሞ ከፍተኛ መኮንን ሃይም ቶመር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በእስራኤል እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል የሰላም ስምምነት ሊደረግ ነው ለሚሉ ሪፖርቶች የተሰጠ የኢራን ምላሽ ነው” ሲሉም ጥቃቱን ገልጸውታል።
ነገር ግን ሃይም ቶመር ኢራን የቅዳሜው ጥቃት እንዲፈጸም በቀጥታ ትዕዛዝ ሰጥታለች የሚለውን ሃሳብ መቀበል “ትንሽ አስቸጋሪ ነው” ይላሉ።
“በእርግጥ ኢራን ለሐማስ ቁጥር አንድ መሳሪያ አቅራቢ ናት። ሶሪያ ውስጥ ሥልጠና እየሰጧቸው ነበር። እንዲሁም በኢራን ውስጥም እንዳሰለጠኗቸው ይነገራል።”
እስራኤል ባለፉት ወራት የሐማስ አመራሮች እንቅስቃሴን ትከታተል እንደነበር የቀድሞው ከፍተኛ መኮንን ያስረዳሉ።
“የድርጅቱ ወታደራዊ ክንፍ ኃላፊ የሆኑት እንደ ሳሌህ አል አሮሪ እንዲሁም ሌሎች የሐማስ አመራሮች ወደ ሊባኖስ እና ኢራን ተደጋጋሚ በረራዎችን አድርገዋል። ከኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ ኾሚኒን ጋር ጭምር እንደተወያዩ እናውቃለን” ብለዋል።
ሆኖም ጥቃቱ አሁን ለምን ተፈጸመ? የሚለውን ለማስረዳት “ጥብቅ ግንኙነታቸው” በቂ አልነበረም ይላሉ።
“ሐማስ በእስራኤል ውስጥ ያለውን ውስጣዊ ግጭት በጥልቀት ተረድቶ እየተከታተለው ነበር” በማለት ያስረዳሉ።
“ኢራን የሎጂስቲክስ እና ወታደራዊ ድጋፎችን ብታደርግም የአሁኑ ውሳኔ ቢያንስ 75 በመቶው በሐማስ አመራሮች በገለልተኛነት የተወሰነ ነው ብዬ አስባለሁ” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, reuters
በቴል አቪቭ ዩኒቨርስቲ የኢራን ጥናት መምህር የሆኑት ራዝ ዚምት በዚህ ይስማማሉ።
“ይህ የፍልስጥኤም ታሪክ ነው” የሚል መልዕክትም መምህሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ሐማስ ለማጥቃት የወሰነው መሬት ላይ ካለው ፍልስጥኤም እውነታ ላይ ተመሥርቶ በራሱ ፍላጎት እንደሆነ መምህሩ ያስረዳሉ።
“ሐማስ የኢራንን እርዳታ ተጠቅሟል? አዎ በእርግጠኝነት! ኢራን ይህንን እርምጃ ትፈልገዋለች? አዎ። ሐማስ ዘመቻውን ለማካሄድ የኢራን ፍቃድ ያስፈልገዋል? በጭራሽ” ይላሉ።
የቀድሞ የሞሳድ ባለሥልጣን ሃይም በበኩላቸው ሐማስ በአሁኑ ዘመቻ ከተጠበቀው በላይ እንደሠራ ይናገራሉ።
ዋል ስትሪት እንደዘገበው ኢራን ጥቃቱ እንዲፈጸም የፈቀደችው ባለፈው ሰኞ ቤይሩት በተደረገ ስብሰባ ላይ ነው።
ዘገባው ስማቸውን ያልጠቀሳቸው የሐማስ እና የሄዝቦላህ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መኮንንኖች ከሐማስ ጋር በመሆን ከነሐሴ ወር ጀምሮ የቅዳሜውን ውስብስብ የአየር፣ የየብስ እና የባሕር ዘመቻ በአንድነት ሲያቀናብሩ እንደነበር አስነብቧል።
የሐማስ ጥቃት ከዚህ ቀደም በጋዛ ሰርጥ ያለውን የእስራኤልን ድንበር ለማፍረስ ከተጠቀማቸው ያልተሳኩ ሙከራዎች በተለየ የረቀቀ መሆኑን የወጡ ቪዲዮዎች ያሳያሉ።
ሮኬቶች፣ ድሮኖች፣ ተሽከርካሪዎች እና በአየር ላይ የመንሳፈፊያ ፓራሹቶችን በተመሳሳይ ጊዜ በመጠቀም የዘመቻው ዕቅድ አውጪዎች ምናልባት ዩክሬንን ጨምሮ ሌሎች የቅርብ ጊዜ የውጊያ መንገዶችን እንዳጠኑ ጠቁሟል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት አሁኑ ከተከሰተው አንጻር ቀጥሎ ምን እንደሚፈጠር በተለያየ አቅጣጫ ለመመልከት እየሞከሩ እንዲሁም የኢራን ተሳትፎንም በበለጠ ለመረዳትም እየጣሩ ይገኛሉ።
በሊባኖስ የኢራን አጋር የሆነው ሄዝቦላህ እስራኤል በወረራ በተቆጣጠረቻቸው የጎላን ኮረብታማ ስፍራዎች ላይ ሁለት አነስተኛ ጥቃቶችን ፈጽሟል። የእስራኤል ጦር በምላሹ በሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን ለመምታት ሄሊኮፕተሮችን መጠቀሙን አስታውቋል።
የሐማስ እንቅስቃሴ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን እውነታ የሚቀይር ክስተት ነው። በተለይም የእስራኤል ምላሽ ለሐማስ ትልቅ ፈተና የሚጋርጥ ከሆነ ኢራን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እና ትብብር ከምታደርግበት ወደ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንድትሸጋገር ሊያስገድዳት ይችላል።















