እስራኤልን ባስደነገጠው የሐማስ ጥቃት የተቀሰቀሰው ቀውስ ወዴት ያመራ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከ50 ዓመታት በፊት ግብፅ እና ሶሪያ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸሙበት ተመሳሳይ ዕለት ሐማስም ያልተጠበቀ ከባድ ጥቃት ፈጽሞ ጦርነት ተቀስቅሷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው ውጥረት እየጨመረ ቢመጣም ከዚህ በፊት እንደታየው ጋዛን የሚያስተዳድረው ሐማስም ሆነ እስራኤል ግጭት እንዲፈጠር አይፈልግጉም ተብሎ ሲታመን ቆይቷል።
ነገር ግን ባለፉት ወራት ሐማስ መጠነ ሰፊ የተቀናጀ ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጅ እንደነበር ቅዳሜ ዕለት የተፈጸመው ያልተጠበቀ ክስተት ማሳያ ሆኗል።
ሐማስ ከጋዛ የከፈተው የሮኬት ጥቃት ከድንበር አካባቢዎች ባሻገር በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ርቆ ቴል አቪቭ እና ኢየሩሳሌም የደረሰ ሲሆን፣ ፍልስጥኤማውያን ተዋጊዎችም በባሕር፣ በአየር እና በምድር ወደ በርካታ ደቡባዊ የእስራኤል ክፍሎች ዘልቀው መግባት ችለዋል።
በሐማስ የተጋሩ ቪዲዮዎች በእስራኤል ወታደራዊ ኬላ ላይ ተሰማርተው እና ታንክ ላይ የነበሩ የእስራኤል ወታደሮች መማረካቸውን እና መገደላቸውን አሳይተዋል።
በዚህ ሁሉ ሳቢያ እስራኤላውያን በጥቃቱ በእጅጉ ደንግጠዋል፤ ለዘመናት በብቃታቸው ሲተማመኑባቸው የነበሩት የደኅንነት ተቋሞቻቸው ሊጠብቋቸው እና ሊረዷቸው ከጎናቸው ባለመቆማቸው ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
በእስራኤል ላይ ምሬት ያላቸው ፍልስጥኤማውያን በበኩላቸው ለሐማስ ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው፣ የእስራኤል የአጸፋ ጥቃት ደግሞ የጋዛ ነዋሪዎችን ለአደጋ አጋልጧቸዋል።
ከፍተኛ ውድመትን ባለፉት ሦሰት ቀናት ባስከተለው የእስራኤል የአየር ጥቃት የተጎዱ ሰዎች የፍልስጥኤም ሆስፒታሎችን አጥለቅልቀዋቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሜዲትራኒያን ባሕርን ተጎራብታ የምትገኘው ጋዛ 2.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጥኤማውያን የሚኖሩባት ሲሆን፣ ሐማስ በምርጫ አሸንፎ የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ሲሆን ግብፅ እና እስራኤል መውጫ መግቢያዋን ዘግተው ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉባት ቆይተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2021 በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ከባድ ግጭት ከተካሄደ በኋላ በግብፅ፣ በኳታር እና በተባበሩት መንግሥታት አሸማጋይነት በጋዛ ላይ ተጥሎ የነበረው ክልከላ ላልቶ በአካባቢው መረጋጋት ተመልሶ ነበር።
ሐማስ የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲጀምር የፍልስጥኤማውያንን መብት እና አገርነት ለማስመለስ እንደ ዋና ግብ አድርጎ የተነሳው እስራኤልን ማውደም ነው። ቡድኑ ይህንንም አቋሙን የሚያራምደው ደግሞ በድብቅ ሳይሆን በይፋ ነው።
ነገር ግን ጋዛን ማስተዳደር ሲጀምር ከታጣቂ ቡድንነት ይልቅ ወደ ፖለቲካዊ ቡድንነት የመሸጋገር ዕድል ይኖረዋል የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ የቅዳሜ ዕለቱ ጥቃት ግን ጥያቄን አስከትሏል።
ቅዳሜ ዕለት ጥቃቱ ሲጀምር የሐማስ ታጣቂ ቡድን አዛዥ ሞሐመድ ዳይፍ “የእስራኤልን ወረራ ጠራርጎ ለማስወገድ” ፍልስጥኤማውያን እና ሌሎች አረቦች እንዲሳተፉ ጥሪ አድርገዋል።
እስራኤልም ከሐማስ ጋር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ግንባሮች ጦርነት ሊገጥማት እንደሚችል ያለጥርጥር ታስባለች።

ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከሚገመቱት መካከል ከሁሉ የከፋው ደግሞ፣ ይህ ሐማስ የቀሰቀሰው ግጭት በሊባኖስ የሚገኘውን ኃይለኛውን ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህን ተሳታፊ ሊያደርገው ከቻለ ነው።
የእስራኤል ሠራዊት ግዙፍ ተጨማሪ ወታደሮች እንዲሰማሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል። በተጨማሪም በጋዛ ላይ የሚያካሂደውን የአየር ድብደባ ባጠናከረበት ጊዜ፣ ጋዛ ውስጥ በእግረኛ ወታደሮች ዘመቻ ለማካሄድ ዕቅድ እንዳለው እያመለከተ ነው።
ሐማስ የከፈተውን ዘመቻ ተከትሎ የማረካቸውን የእስራኤል ወታደሮችን እና የያዛቸውን ሲቪል ሰዎችን ከእስራኤል ጥቃት እራሱን የሚከላከልባቸው ሰብአዊ ጋሻ ሊያደርጋቸው ወይም እንደ መደራደሪያ መሳሪያዎቹ ሊጠቀምባቸው ይችላል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የኳታር አሸማጋዮች በሐማስ ታጣቂዎች ተይዘው ወደ ጋዛ ስርጥ የተወሰዱ እስራኤላውያን ሴቶች እና ሕጻናትን ለማስለቀቅ ጥረት እያደረጉ ነው።
ከሐማስ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት እያደረጉ ያሉት አደራዳሪዎች በሐማስ የተያዙትን አስራኤላውያንን፣ እስራኤል ውስጥ በእስር ላይ በሚገኙ 36 ፍልስጥኤማውያን ሴቶች እና ሕጻናት ልውውጥ እንዲደረግ ሃሳብ አቅርበዋል።
አሁን እንደሚታየው በሐማስ ጥቃት የቆሰለችው አስራኤል የደኅንነት ተቋማቷን ብቃት ከመፈተሽ ባሻገር፣ በሐማስ እና በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ዘመቻን በአጭሩ የምትገታው አትመስልም።
በተቀናጀ ጥቃት በሮኬቶች የእስራኤል ከተሞችን ሲያርድ የቆየው ሐማስ ጦርነቱን ወደ አስራኤል ግዛት ወስዶ በተለያዩ የእስራኤል መንደሮች ውስጥ ፍልሚያ አድርጓል።
ቡድኑ ይህንን መጠነ ሰፊ ጥቃት ሲያቅድ የእስራኤል አጸፋ ቀላል ይሆናል ብሎ ስለማይጠብቅ ከፊቱ ሊመጣ ስለሚችለው ከባድ ጊዜ እራሱን ሳያዘጋጅ አይቀርም።
እንደከዚህ ቀደሙ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እና የተባበሩት መንግሥታት ተቀባይነት አግኝተው ጣልቃ በመግባት ሊራዘም የሚችለውን ግጭት ካላስቆሙት፣ ውስብስብ እና ዘላቂ ቀውስ በመካከለኛው ምሥራቅ ብሎም በዓለም ላይ ማስከተሉ አይቀርም።












