የእስራኤል ባለሥልጣናት ጋዛ ‘በቅርቡ የነዳጅ፣ መድኃኒት እና የምግብ አቅርቦት አይኖራትም’ አሉ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
እስራኤል እና ሐማስ በገቡበት ግጭት ምክንያት የእስራኤል የእስራኤል ባለሥልጣናት ወደ ጋዛ የሚሄዱ የነዳጅ፣ የመድኃኒት እና የምግብ አቅርቦቶችን እንሚቋረጡ ተናገሩ።
እነዚህ መሠረታዊ አቅርቦቶች የሚቋረጡ ከሆነ ወትሮም በችግር ውስጥ በምትገኘው ጋዛ ሰርጥ ያለው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ቀውስ ክፉኛ ይባባሳል ተብሎ ተሰግቷል።
ትላንት ሰኞ እስራኤል የኤሌክትሪክ፣ ምግብ እና ውሃ አቅርቦት ልታቋርጥ እንደምትችል ገልጻ ጋዛ ላይ “ሙሉ ከበባን” አውጃለች።
ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እርዳታ በአካባቢው እንዳልደረሰ ነዋሪዎች ተናግርዋል።
እስራኤል ያካሄደችውን የአየር ድብደባን ተከትሎ ጭር ያሉት መንገዶች በፍርስራሾች ተሞልተው ታይተዋል።
በጥቃቱ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መጎዳታቸው ተዘግቧል።
የጋዛ አካባቢ 2.3 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች የሚኖሩበት ሲሆን፣ ለዓመታት ከእስራኤል ጋር በዘለቀው ግጭት ምክንያት 80 በመቶ የሚሆነው ነዋሪዎች የእርዳታ ጥገኛ ናቸው።
ጋዛ የምትመራው በሐማስ ቢሆንም የአየር ክልሉን እና የባሕር ዳርቻዎችን የምትቆጣጠረው እስራኤል ናት። በተጨማሪም ማን እና ምን ወደ ጋዛ ይለፍ የሚለውንም የምትወስነው እስራኤል ነች።
ግብፅም በጋዛ በኩል የምትዋሰንበት ድንበር ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ታደርጋለች።
ባለፈው ቅዳሜ አዲስ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ደግሞ መድኃኒት እና ምግብን ጨምሮ እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባውን አቅርቦት አቋርጣለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ስቴቨን ዱጃሪክ በርካታ የጤና ባለሙያዎች መገደላቸውን ወይም መጎዳታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ቢያንስ 7 የጤና ማዕከላት መውደማቸውን ጠቁመዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ በርካታ ሰዎች ከኤሌክትሪክ እና ከኢንተርኔት አቅርቦት ጋር ተቆራርጠዋል። በቅርቡም የምግብ እና የውሃ አቅርቦት አይኖርም።
ቃል አቀባዩ “የውሃ፣ የጽዳት እና የንጽህና መሠረተ ልማቶችን ማውደም 400 ሺህ ሰዎች የሚያገኙትን አገልግሎት ከግምት አለማስገባት ነው” ብለዋል።
ጨምረውም ጋዛ ላይ አንድ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ምንጭ የቀረ ሲሆን፣ በነዳጅ እጥረት ምክንያት በቀናት ውስጥ አገልግሎት ሊቆም እንደሚችል አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ100 ሺህ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ፍልስጤማውያን ምግብ ማድረሱን የጠቀሱ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በቀጣዮቹ ቀናት በስምንት እጥፍ እንደሚጨምር ገልጸዋል።
የቅዳሜውን ግጭት ተከትሎ እስራኤል ከጣለችው ዕገዳ በፊትም በጋዛ ከፍተኛ የምግብ ዋስት አቅርቦት ስጋት እና የውሃ እጥረት ነበር።
ሰኞ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት አገራቸው በጋዛ ላይ “ሙሉ ከበባ” ልትጥል እንደሚትችል ተናግረዋል።
“ኤሌክትሪክ አይኖርም፣ ምግብ አይኖርም፣ ጋዝም አይኖርም - ሁሉም ይዘጋል” ካሉ በኋላ “ከእንስሳት ጋር ነው እየተዋጋን ያለነው። እንደሚገባቸው ምላሽ እንሰጣለን” ብለዋል።
የእስራኤል የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ወደ ጋዛ የሚሄደው የውሃ አቅርቦት በአስቸኳይ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። “በፊት የነበረው ወደፊት አይኖርም” ሲሉም ታናግረዋል።
እነዚህ መግለጫዎች ከመሰማታቸው አስቀድሞ የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በእስራኤል ድርጊት ምክንያት ሆስፒታሎች የመድኃኒት፣ የሕክምና ቁሶች እና የነዳጅ አቀርቦት እጥረት እንደገጠማቸው አስታውቆ ነበር።
ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ እስራኤል የኃይል መስመሮችን መልሳ እንድታገናኝ እንዲሁም እንደ መድኃኒት እና ነዳጅ ያሉ ወሳኝ አቅርቦቶችን እንዲቀጥሉ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ባለፉት ቀናት ውስጥ እስራኤል ተከታታይ እና ከባድ የአየር ድብደባዎችን ጋዛ ላይ እየፈጸመች ነው። እሁድ ዕለት የተፈጸመው የአየር ጥቃት ግን ጋዛ ከረጅም ዓመታት በኋላ ያስተናገደችው ከባድ ጥቃት ነው።
እስራኤል የምትፈጽመው ጥቃት ሐማስን ኢላማ ነው ያደረገ ነው ይባል እንጂ ሲቪል ሰዎች እና ተቋማትም የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ ነው።
የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋዛ የሚገኙ ሁለት የስደተኛ መጠለያዎች በእስራኤል የአየር ጥቃት ተደብድበው በርካቶች መሞታቸው እና መጎዳታቸውን ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ጨምሮም በእስራኤል የአየር ድብደባ ሕጸናት እና አረጋውያንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የሚቀበለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትምህርት ቤት መመታቱን አስታውቋል።
ተመድ ትምህርት ቤቱ “በአስከፊ ሁኔታ መውደሙን” ያረጋገጠ ሲሆን፣ የሞተ ሰው እንደሌለ ገልጿል።
መስጂዶች እና መኖሪያ ቤቶች በአየር ድብደባው መመታታቸውን የሚያመለክቱ ዘገባዎችም እየወጡ ነው።
ራፋ በተባለችው የደቡባዊ ጋዛ አካባቢ ከአንድ ቤተሰብ 19 ሰዎች መገደላቸውን አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መረጃ 123,538 ሰዎች ጥቃቱ በፈጠረባቸው ፍርሃት እና መኖሪያ ቤታቸው በመውደሙ በጋዛ የውስጥ ተፈናቃይ መሆናቸውን ይፋ አደርጓል።
የተመድ የሰብአዊ እርዳታ ጽህፈት ቤት ወይም ኦቻ በበኩሉ 73 ሺህ ሰዎች በትምህርት ቤት ውስጥ መጠላላቸውን አስታውቋል።












