ሐማስ በእስራኤል ላይ ለፈጸመው ጥቃት ምክንያቱ ምንድን ነው?

የሐማስ ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፍልስጥኤማዊው ታጣቂ ቡድን ሐማስ ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ የፈጸመው ጥቃት በመጠኑ እና ባደረሰው ጉዳት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው።

ክስተቱ በድንገት ያጋጠመ ቢሆንም ለአስርታት በፍልስጥኤማውያን እና በእስራኤል መካከል የዘለቀው ውጥረት ውጤት ነው።

ሐማስ እንደሚለው ለዚህ ጥቃት በርካታ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አራቱን እንመልከት።

ጋዛ

ጋዛ በእስራኤል በግብፅ እና በሜድትራኒያን ባሕር መካከል የምትገኝ 41 ኪሎ ሜትሮች ርዝመት እና 10 ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ናት። በውስጧም 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ሲሆን፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ተጠጋግቶ ከሚኖርባቸው ስፍራዎች መካከል አንዷ ናት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ከጋዛ ነዋሪዎች 80 በመቶዎቹ በዓለም አቀፍ እርዳታ ላይ ጥገኛ ሲሆኑ፣ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ኑሯቸው የተመሠረተው በዕለታዊ የምግብ እርዳታ ላይ ነው።

ጋዛ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ አቅርቦት እና የጤና አገለግሎትን የመሳሰሉ መሠረታዊ አቅርቦቶች ከፍተኛ ችግር እንዳለ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

እስራኤል የጋዛን የአየር ክልል እና የባሕር ጠረፍን የምትቆጣጠር ሲሆን፣ ወደ ግዛቲቱ በሚገቡ እና በሚወጡ ሸቀጦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ታደርጋለች።

በተመሳሳይም ግብፅ ከጋዛ ጋር በሚያዋስናት ድንበር በኩል ምን እንደሚገባ እና እንደሚወጣ ትቆጣጠራለች። ሁለቱም አገራት ይህንን የሚያደርጉት ለደኅንነታቸው ሲሉ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከግጭቱ በፊት በእንዲህ ያለ ጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ የቆየችው ጋዛ አሁን ሐማስ ከፈጸመው ጥቃት በኋላ፣ የእስራኤል መንግሥት የምግብ፣ የውሃ እና የነዳጅ አቅርቦቶችን በማቋረጥ ጋዛ ሙሉ ለሙሉ ዝግ እንደምትሆን አሳውቋል።

ሐማስ ከፍልስጥኤም አስተዳደር ታማኝ ኃይሎች ጋር አለመግባባት እና ግጭት ውስጥ ከገባ ከአውሮፓውያኑ ከ2007 በኋላ ጋዛን እያስተዳደረ ይገኛል።

በ2014 (እአአ) ሐማስ ከእስራኤል ጋር ለአጭር ጊዜ የቆየ ግጭት ካደረገ በኋላ፣ እስራኤል ግዛቷን ከታጣቂዎች የሮኬት ጥቃት እና ሰርጎ ገቦች ለመጠበቅ በሚል በጋዛ ዙሪያ የመከላከያ ቀጠና አወጀች። ይህ ቀጠናም የጋዛ ነዋሪዎች የሚኖሩበትን እና የሚያርሱትን የመሬት ይዞታ ቀንሶታል።

ካርታ

የአል-አቅሳ መስጂድ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚገኘው የአል-አቅሳ መስጂድ በእስራኤል እና በፍልስጥኤማውያን መካከል ላለው ውጥረት ዋነኛ ማሳያ ነው። በተራራማ ስፍራ ላይ የሚገኘው ይህ መስጂድ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሦስተኛው ቅዱስ ቦታ ሲሆን፣ ቴምፕል ማውንት ለሚሉት አይሁዳውያንም ቅዱስ ስፍራ ነው።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አል-ቃሳም ብርጌድ አዛዥ የሆኑት ሙሐመድ አል-ዳይፍ ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ እንደተናገሩት፣ እስራኤላውያን “በአል-አቅሳ መስጂድ ላይ በየዕለቱ ለሚፈጽሙት ጥቃት” እና “በመስጂዱ ግቢ ውስጥ ነብያችንን ለመስደብ ላሳዩት ድፍረት” አጸፋ ነው ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህም የእስራኤል ሃይማኖታዊ ብሔርተኞች ወደ ቅዱስ ስፍራው የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ጉብኝት መጨመሩ ፍልስጥኤማውያንን አሳስቧቸዋል።

በመስጂዱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በፍልስጥኤማውያን ሃይማኖተኞች እና በእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች ተከስተዋል። ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ዙሪያ የተፈጠረን አለመግባባት ተከትሎ የእስራኤል ፖሊሶች የጭስ ቦምብ እና የጎማ ጥይቶችን በመጠቀም መስጂዱን ወረውት ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2021 ላይ የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች በመስጂዱ ላይ የፈጸሙትን ወረራ ተከትሎ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ለ11 ቀን የዘለቀ መጠነ ሰፊ ግጭት ተካሂዶ ነበር።

በሊባኖስ የሐማስ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ኦስማን ሐምዳን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፍልስጥኤማውያን መስጂዱን በተመለከተ የእስራኤል መንግሥት ያለው ፍልጎት እንደሚያሳስባቸው እና የሚደረግ ማንኛውም ለውጥ “ግልጽ ቀይ መስመር መጣስ ነው” ብለዋል። የእስራኤል ባለሥልጣናት በበኩላቸው የአምልኮ ነጻነትን እንደሚያከብሩ ገልጸዋል።

የአል-አቅሳ መስጂድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአል-አቅሳ መስጂድ

የአይሁዳውያን ሰፈራዎች

የ1967ቱን (እአአ) ጦርነት ተከትሎ እስራኤል ግዛቶችን ወራ ከያዘች በኋላ፣ በአብዛኛው በዌስት ባንክ አካባቢዎች የአይሁዳውያን ሰፈራ እየጨመረ መጥቷል። እንደተባበሩት መንግሥታት ግምት በአውሮፓውያኑ 2022 በወረራ በተያዘው አካካቢ 700 ሺህ የሚደርሱ አይሁዳውያን ሰፍረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እና አብዛኞቹ የዓለም አገራት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የአይሁዳውያኑ ሰፈራ ሕገወጥ ናቸው ቢሉም፣ እስራኤል ግን በዚህ አትስማማም።

በዚህ ዓመት በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ውስጥ የሚገኙ ጽንፈኛ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በሰላማዊ ፍልስጥኤማውያን ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በየወሩ ከ100 በላይ ጥቃቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ካለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ወዲህ 400 የሚሆኑ ሰዎች ከመሬታቸው ተፈናቅለው ተባረዋል ብሏል።

የሐማሱ ኦስማን ሐምዳን እንደሚሉት እስራኤል “ፍልስጥኤማውያንን ከዌስት ባንክ የማባረር ዕቅድ አላት” በማለት ፍልስጥኤማውያን ይሰጋሉ።

ከአወዛጋቢዎቹ የአይሁዳውያን ሰፈራዎች አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከአወዛጋቢዎቹ የአይሁዳውያን ሰፈራዎች አንዱ

የእስራኤል እና የአረቦች ግንኙነት

በአውሮፓውያኑ 1979 እና በ1994 በተፈረሙ የሰላም ስምምነቶች አማካይነት እስራኤል ከጎረቤቶቿ መካከል ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ከግብፅ እና ከዮርዳኖስ ጋር ብቻ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዩናይትድ አረብ ኤምሬትን ከመሳሰሉ ከአካባቢው ቁልፍ አገራት ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ላይ ለመድረስ መንገድ ከፍታለች።

የሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢል ሳልማን ፎክስ ኒውስ ለተባለ የአሜሪካ ቴሌቪዥን በቅርቡ እንደተናገሩት፣ አገራቸው ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ መደበኛው ደረጃ ለማድረስ “በየዕእለቱ እየተቀራረብን ነው” ብለዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ከእስራኤል ጋር የሚደረስ የትኛውም ስምምነት የፍልስጥኤማውያን አገርን በመመሥረትን ዙሪያ የሚታዩ እርምጃዎችን መሠረት ያደረገ ነው የሚል አቋም ነበራት። አሁን ያሳየችውን ለውጥ የተቃወመው ሐማስ፣ እንዲህ ያለው እርምጃ እስራኤል የፍልስጥኤማውያንን ጥያቄ እንድትቀበል የሚደርስባትን ጫና የሚያቀል ነው ብሏል።

ሐማስ በእስራኤል ጥቃቱን በፈጸመበት ዕለት፣ የቡድኑ መሪ ኢስማኤል ሃኒያህ ከአይሁዳዊቷ አገር ጋር እርቅ በማውረድ ግንኙነታቸውን በማሻሻል ላይ ያሉ አረብ አገራትን ተችተዋል።

“ከእስራኤል ጋር ግንኙነታችሁን ለማሻሻል የፈረማችኋቸው ስምምነቶች ለግጭቱ መፍትሄ ሊሆን አይችልም” ብለዋል።