እስራኤል በሊባኖስ የሚገኙ የተመድ የሰላም አስከባሪዎች ላይ መተኮስ እንድታቆም አሜሪካ ጠየቀች

የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ጦር በሊባኖስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሊባኖስ የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች ላይ በ48 ሰዓታት ውስጥ የደረሱ ሁለት ክስተቶችን ከሰሙ በኋላ እስራኤል በሊባኖስ ከሔዝቦላህ ጋር ባላት ግጭት ወደ ሰላም አስከባሪዎች መተኮስ እንድታቆም ጠየቁ።

አርብ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሊባኖስ የሚገኙ ሁለት የሲሪላንካ ዜግነት ያላቸው የተባበሩት መንግሥታት ወታደሮች ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ወታደሮቹ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ገልጾ ነበር።

በሊባኖስ ናቆራ አካባቢ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የጦር ካምፕ አካባቢ የሚንቀሳቀስ የእስራኤል ሠራዊት፣ ስጋት የሚሆን ነገር በመለየታቸው ተኩስ መክፈታቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

አክሎም ክስተቱ “በከፍተኛ ደረጃ” ምርመራ እንደሚደረግበት ቃል ገብቷል።

ሐሙስ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ጦር አባላት የሆኑ ሁለት ኢንዶኔዢያውያን የእስራኤል ታንክ በተኮሰባቸው ጥይት ከቅኝት ማማቸው ላይ ወድቀው ተጎድተው ነበር።

የፈረንሳይ፣ጣልያን እና ስፔን መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ የእስራኤልን ድርጊት በፍጥነት ሊቆም የሚገባው፣ ምንም ማስተባበያ ሊሰጥበት የማይችል ሲሉ ኮንነውታል።

የስሪላንካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ሁለት ዜጎቹን ያቆሰለበትን የእስራኤል ጦር ጥቃትን “በጥብቅ አውግዞታል።”

የተባበሩት መንግሥታት ሠላም አስከባሪ ዋና ኃላፊ በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ የሰላም አስከባሪዎች ይዞታዎች ላይ በቀጥታ ጥቃት መከፈቱን እንደሚያምን ገልጾ፣ በድርጊቱ ማን ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

ዤን ፔሪ ላክሮክስ ለቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም “ለምሳሌ በተተኮሰ ጥይት የቅኝት ማማ መመታቱን፣ የደህንነት ካሜራዎች መውደማቸውን ስናይ በቀጥታ ወደ እኛ መተኮሳቸውን ያሳየናል” ሲሉ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የምታደርገው ወረራ በቀጠለበት በአሁኑ ሰዓት ሔዝቦላ ወደ እስራኤል የሚያስወነጭፋቸው ሚሳዔሎች እና ሮኬቶችም አላቋረጡም።

አርብ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በአንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ 100 ሮኬቶች ከሊባኖስ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል አቅጣጫ መተኮሳቸውን ገልጿል።

በተጨማሪም ሁለት ሰው አልባ የአየር መሳርያዎች ከሊባኖስ ወደ እስራኤል ድንበር ጥሰው ሲገቡ አንዱ በመከላከያ ሠራዊቱ እንዲከሽፍ መደረጉን ተናግሯል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስትር በበኩሉ የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ ሲዶን ባደረገው ጥቃት የሁለት ዓመት ሴት ልጅን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቋል።

የሊባኖስ ጦር በበኩሉ የእስራኤል ኃይሎች በደቡባዊ ሊባኖስ ካፍራ የሚገኝ የሠራዊቱ ካምፕ ላይ ጥቃት ከፍተው ሁለት ወታደሮችን መግደላቸውን ገልጿል።

ሐሙስ ዕለት በዋና ከተማዋ ቤይሩት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በእስራኤል ሁለት የአየር ጥቃቶች በወደሙ ሕንጻዎች ፍርስራሾች ውስጥ የተረፉ ካሉ በሚል ሲፈልጉ ነበር።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ ጥቃቱ ያለምንም ማስጠንቀቅያ መድረሱን እና 22 ሰዎች ገድሎ 117 ማቁሰሉን ተናግረዋል።

እስራኤል በጥቃቱ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በደቡባዊ ሊባኖስ የእግረኛ ጦሩን ያሰማራው ከሔዝቦላህ ጋር በሚያደርገው ጦርነት ታጣቂ ኃይሉ ወደ እስራኤል የሚተኩሳቸው ሚሳኤሎች በጨመሩበት ወቅት ነው።

የእስራኤል ጦር አርብ ዕለት በናቆራ በተባበሩት መንግሥታት ካምፕ ላይ ጥቃት የደረሰው፣ ዒላማ የተደረገው አካል ከካምቡ በ50 ሜትር ርቀት ላይ በመገኘቱ እንደሆነ አስታውቋል።

በወቅቱ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች መከላከያ ምሽግ ባለበት ስፍራ እንዲቆዩ እንደተነገራቸውም አክሎ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ በበኩሉ ለእስራኤል ድንበር ቅርብ በሆነው እና በላቦኔህ በሚገኘው ካምፑ የእስራኤል ጦር መኪና መከላከያዎችን ገጭቶ መጣሉን አስታውቋል።

እነዚህ ክስተቶች ሁኔታው “አደገኛ እየሆነ መምጣቱን” ያሳያሉ ሲል ተናግሯል።

ሚካቲ የአርብ ዕለቱን ጥቃት ተከትሎ “በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ላይ በቀጥታ የደረሰ ወንጀል” ሲሉ ተናግረዋል።

እስራኤል የተባበሩት መንግሥታት ሠላም አስከባሪዎች ቀጠናውን ማረጋጋት አለመቻላቸውን ትናገራለች።

አክላም አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ እና ከሔዝቦላህ ጋር የጀመረችውን ጦርነት በአካባቢው እንድትቀጥል ትጠይቃለች።

በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን የሰላም አስከባሪው “አደጋን ለማስወገድ” በሰሜን በኩል 5 ኪሎ ሜትር ለቅቆ እንዲወጣ ቢጠይቁም፣ የተባበሩት መንግሥታት ግን በስፍራው እንደሚቆይ አስታውቋል።

በሊባኖስ ከ50 አገራት የተውጣጡ 10 ሺህ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እንዲሁም 800 ሲቪል ሰራተኞች ሰፍረው ይገኛሉ።

እነዚህ ሰላም አስከባሪዎች እኤኤ ከ1978 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠውን የእስራኤል እና የሊባኖስ ድንበርን እንዲሁም በሊታኒ ወንዝ አካባቢ ቅኝት ያደርጋሉ።