ከጃፓን የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉ የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሸልማት አሸነፉ

በአለም ላይ በአሰቃቂነቱ የሚጠቀሰው አሜሪካ በጃፓን የፈጸመችው የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ያቀፈው ኒሆን ሂዳንክዮ የተሰኘው ድርጅት የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነ።
ከሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የቦምብ ጥቃት የተረፉት ሰዎች ስብስብ የሆነው ይህ ድርጅት በአለም ላይ ያለውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለማስወገድ እያደረገ ላለው ጥረት ከኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሽልማት ዕውቅና ተሰጥቶታል።
“ድርጅቱ በዓለም ላይ ጸረ-ኒውክሌር እንቅስቃሴ እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል” ሲሉ የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢ ጆርገን ዋትን ፍሬድነስ ተናግረዋል።
በአቶሚክ ቦምብ የደረሰውን እልቂት ምስክርነት በመስጠት የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች እንደገና ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት ከፍተኛ ስራ መስራታቸው ተዘክሯል።
በአውሮፓውያኑ 1956 የተመሰረተው ይህ ድርጅት በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ምክንያት የደረሱ አሰቃቂ እልቁቶችን እና ስቃይ ምስክርነትን እንዲሰጡ ከጥቃት የተረፉትን ወደተለያዩ አገራት በመላክ ይሰራል።
ስብስቡ ስራቸውን የጀመሩት የሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ውድመት ከደረሰ ከአስር ዓመታት በኋላ ነው።
ቡድኑ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለኖቤል ሽልማት ታጭቶ የነበረ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2005 ከኖቤል ኮሚቴ ልዩ እውቅና እንደተሰጣቸው ድረ-ገጹ ያትታል።
በአውሮፓውያኑ 1945 አሜሪካ የዩራኒየም ቦምብ በሂሮሺማ ከተማ አዘነበች።
ዓለም በአሰቃቂነቱ የሚያወሳው የጃፓኖቹ ሂሮሺማና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ የአሜሪካ የአውቶሚክ ቦምቦች ዘንበውበታል፣ የሰው ልጅ እንደ ቅጠል ረግፈውበታል።
በእነዚህ የቦምብ ጥቃቶች ምን ያህል ሰዎች እንዳለቁ ትክክለኛ ቁጥር ባይኖርም ከሂሮሺማ 350 ሺህ ሕዝብ ውስጥ 140 ሺህዎቹ ሞተዋል። በናጋሳኪም እንዲሁ 74 ሺህዎች ተፈጅተዋል።
በአውቶሚክ ቦምቡ ጥቃቱ ምክንያት ጃፓን በ1937 እጅ ሰጥታለች። እንዲሁም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ክፍል የሆነውና በእስያ የነበረውን ጦርነት ማብቂያን ያበሰረ ነው ቢሉም አንዳንዶች በዚህ ሃሳብ አይስማሙም።
የቡድኑ አንደኛው ኃላፊ የሆኑት ቶሺዪኩ ሚማኪ ከሽልማቱ በኋላ ለጋዜጠኞች “በህልሜም ቢሆን ይህንን አላስብም ነበር” ሲሉ መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ባለፈው ዓመት በእስር ላይ የምትገኘው ኢራናዊቷ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ናርጅስ ሞሃማዲ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ነበረች።
ናርጅስ የሽልማቱ አሸናፊ የሆነችው በኢራን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በመታገል እንዲሁም ሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮ እና ነጻነት የሚያገኙበትን ዓለም ለመፍጠር ባደረገችውም ትግል እንደሆነም ኮሚቴው አስታውቆ ነበር።
ከሁለት ዓመት በፊት የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የነበሩት ሜሞሪያል የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን፣ ዩክሬናዊ የሰብዓዊ ተሟጋች ማዕከል ‘ሴንተር ፎር ሊበርቲስ ‘ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኘው የመብት ተሟጋች አሌስ ቢያሊያትስኪ ነበሩ።
ሩስያ በዩክሬን ላይ ወረራ ፈጽማ ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉት ትግልም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የኖቤል የሰላም ሽልማት ከተቋቋመበት ከአውሮፓውያኑ 1901 ጀምሮ 110 ግለሰቦች እና 30 ድርጅቶች አሸናፊ ሆነዋል።
ከዚህ ቀደም ፓኪስታናዊቷ የትምህርት ተሟጋች ማላላ ዩሳፋዚ እንዲሁም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሽልማቱ አሸናፊ ሆነዋል።












