በእስር ላይ የምትገኘው ኢራናዊት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሸልማት አሸነፈች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በእስር ላይ የምትገኘው ኢራናዊቷ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ናርጅስ ሞሃማዲ የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆናለች።
ናርጅስ የሽልማቱ አሸናፊ የሆነችው በኢራን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በመታገል እንዲሁም ሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮ እና ነጻነት የሚያገኙበትን ዓለም ለመፍጠር ባደረገችውም ትግል እንደሆነም ኮሚቴው አስታውቋል።
ናርጅስ በምታደርገው ትግልም በርካታ ጊዜ በቁጥጥር ስር ውላለች። በኢራን መንግሥት 13 ጊዜ በቁጥጥር ስር ውላ አምስት ጊዜ ጥፋተኛ የተባለች ሲሆን በአጠቃላይም የ31 ዓመታት እስራት እንዲሁም 154 የጅራፍ ግርፋት ተፈርዶባታል።
ናርጅስ ያለፉትን አብዛኛውን ሁለት አስርት አመታት በእስር ነው ያሳለፈችው። በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት ተቃራኒ በሆነ ተግባር እና በኢራን መንግሥት ላይ ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ክስ 12 ዓመት ተፈርዶባት ኢቪን ማረሚያ በእስር ትገኛለች።
የኖቤል ኮሚቴውም ሽልማቱን ባበረከትም ወቅት “የናርጅስ የጀግንነት ትግል ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏታል” ብሏል።
“እኔ አሁን እየተናገርኩ ባለሁበት ወቅት እሷ በእስር እየማቀቀች ትገኛለች” ሲሉም በኦስሎ የሚገኘው የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ኀላፊ የሆኑት ቤሪት ሪስ አንደርሰን ተናግረዋል።
ናርጅስ ቢቢሲ አለምን የተሻለች ለማድረግ የሚጥሩ 100 ሴቶችን በሚመርጥበት ፕሮግራሙም በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ ተካታለች።
ባለፈው ዓመት የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የነበሩት ሜሞሪያል የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን፣ ዩክሬናዊ የሰብዓዊ ተሟጋች ማዕከል ‘ሴንተር ፎር ሊበርቲስ ‘ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኘው የመብት ተሟጋች አሌስ ቢያሊያትስኪ ነበሩ።
ሩስያ በዩክሬን ላይ ወረራ ፈጽማ ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉት ትግልም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ናርጅስ 11 ሚሊዮን የስዊድን ክሮነር (አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ) ዶላር ታገኛለች። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲወዳዳር 10 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል። በተጨማሪም ተሸላሚዎች ዲፕሎማ እና የኖቤል ኮሚቴው 18 ካራት ወርቅ ሜዳሊያም ይሸለማሉ።
የኖቤል የሰላም ሽልማት ከተቋቋመበት ከአውሮፓውያኑ 1901 ጀምሮ 110 ግለሰቦች እና 30 ድርጅቶች አሸናፊ ሆነዋል።
ከዚህ ቀደም ፓኪስታናዊቷ የትምህርት ተሟጋች ማላላ ዩሳፋዚ እንዲሁም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሽልማቱ አሸናፊ ሆነዋል።












