መርዝ ወይስ የልብ ስብራት? የኖቤል ተሸላሚው ገጣሚ ምሥጢራዊ አሟሟት

ቺሊያዊው ገጣሚ ፓብሎ ኔሩዳ
የምስሉ መግለጫ, ቺሊያዊው ገጣሚ ፓብሎ ኔሩዳ

ፍቅርን በተለያዩ ቃላቶች በመግለጽ ወደር የለውም የሚባለው ቺሊያዊው ገጣሚ ፓብሎ ኔሩዳ ከሞተ ግማሽ ምዕተ ዓመታትን አስቆጥሯል።

ቃላቶች ይታዘዙለታል፣ ፍቅርንስ እሱ ይናገረው ይላሉ ግጥሞቹን የሚያውቁ ባለሙያዎች።

ሥራዎቹም ዘመንን፣ ትውልድን፣ ባሕርን፣ ዘርን ተሻግረው በተለያዩ የዓለማችን ጫፎች ተነበዋል።

ከሥራዎቹ ጋር አብሮ አሟሟቱም እንቆቅልሽ መሆኑ ይነሳል።

ከሞተ ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ ነበር የቺሊው አምባገነን መሪ ጄኔራል አውግስቶ ፒኖቼ ከአሟሟቱ ጀርባ እንዳሉ መወራት የጀመረው።

በአሟሟቱ ላይ የተደረገው ምርመራ ከአስር ዓመታት በላይ ፈጅቷል።

የካናዳ፣ ዴንማርክ እና የሌሎች አገራት የፎረንሲክ ባለሙያዎች ገጣሚው ምን እንደገደለው ለማወቅ አስከሬኑን ቢመረምሩም በእርግጥ የሞቱን ትክክለኛ ምክንያት ሊሰጡ አልቻሉም።

ገጣሚው የተገደለው በጄኔራል አውግስቶ ፒኖቼ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገው የፓብሎ የቀድሞ ሹፌር እና የግል ረዳቱ ማኑኤል አርአያ ነው። እሱም በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ የገጣሚውን አሟሟት መቋጫውን ሳያይ በ77 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል።

“በአሟሟቱ ላይ ግልጽ መረጃ እንፈልጋለን” ሲል የፓብሎ ኔሩዳ የወንድም ልጅ የሆነው ሮዶልፎ ሬይስ በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።

“ውሳኔው ጉዳዩን በያዙት ዳኛ እጅ ነው። ሁላችንም የእሳቸውን ብያኔ እየጠበቅን ነው ያለነው” ሲልም አክሏል።

በፍቅር ግጥሞቹ ዝነኝነትን ያተረፈው ፓብሎ ኔሩዳ በሥነ ጽሁፍ ዘርፍ በአውሮፓውያኑ 1971 የኖቤል ሽልማት ማሸነፍ የቻለ የዓለማችን ድንቅ ፀሐፊ ነው።

ኔሩዳ ከሞተ ሃምሳ ዓመታትን አስቆጠረ። ጄኔራል ፒኖቼን ወደ ሥልጣን ያመጣው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተከሰተ ከ12 ቀናት በኋላ ነበር ሕይወቱ ያለፈው። በወቅቱም ዕድሜው 69 ነበር።

ገጣሚው በፕሮስቴት ካንሰር ሲሰቃይ የነበረ ሲሆን፣ የሞት የምስክር ወረቀቱም በበሽታው ሳቢያ ሕይወቱ ማለፉን አስፍሯል።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ በ2011 ለገጣሚው በመጨረሻዎቹ የሕይወት ዘመኑ በአሽከርካሪነት እና በረዳትነት ያገለገለው ማኑኤል አርአያ አዲስ መረጃ ይፋ አደረገ።

በጄኔራል ፒኖቼ ትዕዛዝ በመርዝ መርፌ ተወግቶ እንደተገደለ ይነገረል። ግድያውም ገጣሚው በጄኔራል ፒኖቼ አገዛዝ ላይ ተቃውሞን ለመምራት በግዞት ወደ ሜክሲኮ እንዳይሄድ ለማስቆምም ነው አለ።

የፓብሎ የቀድሞ ሹፌር እና የግል ረዳቱ ማኑኡል አርአያ
የምስሉ መግለጫ, የፓብሎ የቀድሞ ሹፌር እና የግል ረዳቱ ማኑኤል አርአያ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኔሩዳ ኮሚኒስት ነበር። በመፈንቅለ መንግሥቱ ከሥልጣን የወረዱት እና ሶሻሊስቱ የቺሊው ፕሬዝዳንት ሳልቫዶር አሌንዴ የቅርብ ጓደኛም ነበሩ።

“ኔሩዳን ገደሉት። ምክንያቱም ጄኔራል ፒኖቼ ከአገር እንዲወጣ አይፈልጉም ነበር” በማለት አርአያ በአንድ ወቅት ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

አርአያ በመርዝ ተገድሏል ማለቱንም ተከትሎ የኔሩዳ አስከሬን በአውሮፓውያኑ 2013 ተቆፍሮ እንዲወጣ ተደረገ። በአስከሬኑም ላይ ምርመራ መደረግም ተጀመረ።

ከቶሮንቶ ማክማስተር ዩኒቨርስቲ እና ከኮፐንሃገን ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ ሳይንቲስቶች ገጣሚው በካንሰር እንዳልሞተ፣ ነገር ግን በምን ምክንያት እንደሞተ ማወቅ መናገር ሳይችሉ ቀሩ።

ይህንንም ተከትሎ በአስከሬኑ ላይ ሌሎች ምርመራዎች እንዲደረጉ ትዕዛዝ ተላለፈ።

ሳይንቲስቶቹ በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ ሌላ ሪፖርት ይዘው መጡ። በኔሩዳ ጥርስ ላይ ክሎስትሪዲየም ቦቱሊኒየም የተባለ ንጥረ ነገር ምልክቶችን ማግኘታቸውን አሳወቁ።

“ቦቱሊዝም የተሰኘው ንጥረ ነገር በሰው ልጅ ዘንድ በገዳይነት ከሚታወቁት መርዞች መካከል አንዱን ቦቱሊኒየም ያመነጫል። የተለያዩ አገራትም እንደ ባዮሎጂካል የጦር መሳሪያ ይገለገሉበት ነበር” ብለዋል ባለሙያዎቹ።

ሆኖም ኔሩዳ በክሎስትሪዲየም ቦቱሊኒየም ስለመሞቱ የሚያረጋግጥ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ እንደሌለ “ወይም ሆን ተብሎ እሱን ለመግደል ጥቅም ላይ ስለመዋሉ” ማረጋገጥ አልተቻለም ሲሉ ሳይንቲስቶቹ ገልጸዋል።

የሳይንቲስቶቹ ሪፖርት ለቺሊ የፍትሕ ባለሥልጣናት ቀርቧል። ጉዳዩን በበላይነት እየመሩ ያሉት ዳኛ ፓውላ ፕላዛ በምርመራው ላይ ብያኔ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም መቼ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለም። ወይም በእርግጠኝነት የገጣሚውን አሟሟት ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅም ምን አልባት ተጨማሪ ምርመራዎችን ሊያዙ እንደሚችሉም ይጠበቃል።

የገጣሚው አሟሟት እንቆቅልሽ የኔሩዳ ቤተሰብን እንዲሁም ቺሊያውያንን ለሁለት ከፍሏል። ሮዶልፎ ሬይስ ገጣሚው አጎቱ መገደሉን ቢያምንም፣ የኔሩዳ የወንድም ልጅ በርናርዶ ሬየስ በበኩሉ አጠቃላይ ምርመራውን “አሳፋሪ” እንዲሁም ሐሰተኛ ዜና ሲል ነው የሚገልጸው።

የገጣሚውን ንብረት የሚያስተዳድረው የኔሩዳ ፋውንዴሽን በበኩሉ ገጣሚው በተፈጥሮ ምክንያት እንደሞተ አጥብቆ ይከራከራል።

የኔሩዳ የቀድሞ ባለቤት ማቲልዴ ኡሪቲያ ባሏ ተገድሏል ብላ አታምንም። ባሏ ከሞተ ከአስራ ሁለት ዓመት በኋላ ሕይወቷ ያለፈው ማቲልዴ ሕይወቱ ሳይጠበቅ እንዳለፈ ተናግራለች።

ኔሩዳ ቢያንስ ለስድስት ዓመታት ያህል እንደሚኖር በዶክተሮች ተነግሮት ነበር ብላለች።

ኔሩዳ በአገሪቱ የተከሰተው መፈንቅለ መንግሥት የቆመለትን ፖለቲካ እና ያምንበት የነበረውን ሁሉ ሲሸረሽር እና ሲያፈርሰው ልቡ ተሰብሮ እንደሞተም ታምናለች።

አቃብያነ ሕግ ገጣሚውን በመጨረሻዎቹ ጊዜያት ያገኙት የነበሩ ጓደኞቹን እንዲሁም በርካታ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ዲፕሎማቶች እና ፖለቲከኞችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

አንዳንዶቹ በጠና ታሞ እንደነበር ተናግረዋል። በመጨረሻው ሰዓታት ከኔሩዳ ጋር በሆስፒታል ውስጥ የነበረችው የቅርብ ጓደኛው አይዳ ፊጌሮአ “እንደሚሞት ለእኔ ግልጽ ነበር” ብላለች።

 የኔሩዳ የቀድሞ ባለቤት ማቲልዴ ኡሪቲያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኔሩዳ የቀድሞ ባለቤት ማቲልዴ ኡሪቲያ

ሌሎቹ ግን እንደሚሞት እርግጠኛ አልነበሩም።

በቺሊ የሜክሲኮ አምባሳደር የነበሩት ጎንዛሎ ማርቲኔዝ ኮርባላ ገጣሚው ሕይወቱ ከማለፉ አንድ ቀን በፊት አይቶት ነበር።

“በዚያ ወቅት ወደ ሜክሲኮ ስለሚደረገው እና ስለአይቀሬው ጉዞ ዝግጅት ከፓብሎ ኔሩዳ ጋር ተነጋገርን” በማለት አምባሳደሩ ለመርማሪዎች ተናግረዋል።

አክለውም “በእርግጥ አገሩን ለቆ ለግዞት የመዳረጉ ሃሳብ ጎድቶታል። ነገር ግን ውጭ አገር ሆኖ መጫወት የሚችለውን ሚና ተረድቶታል” ብለዋል።

“በህመም ወይ በስቃይ ውስጥ እንደነበረ የሚጠቁም ምንም ነገር አላየሁም። መናገር የማይችልበት ወይም ራሱን መከላከል የማይችልበት ደረጃ ላይ አልነበረም። በጭራሽ እየሞተ አልነበረም” ሲሉም ተናግረዋል።

የቀድሞ አሽከርካሪው አርአያ ገጣሚው ኔሩዳ በመርዝ ተገድሏል ያለው ገጣሚው ከሞተ ከአርባ ዓመታት በኋላ ነው።

በርካቶች አርዓያ የሚያውቀውን ለመናገር ለምን 40 ዓመታት ፈጀበት ሲሉም ይጠይቃሉ። አሽከርካሪው በበኩሉ ቺሊ በአምባገንን አገዛዝ ስር በነበረችበት 17 ዓመታት እንዲህ ዓይነቱን ክስ ማቅረብ በጣም አደገኛ እንደነበር ተናግሯል።

ከዚያም በኋላ በነበሩት በ1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ የቺሊ ሚዲያዎች ታሪኩን እንዲዘግቡ ለማሳመን እየሞከረ እንደነበር አስረድቷል። ነገር ግን “እንዴት ጉዳዩን እንደምሄድበት አላውቅም ነበር። የሆነ ሆኖ ማንም ማዳመጥ አልፈለገም ነበር” ብሏል።

አርአያ ከመሞቱ ከሳምንታት በፊት ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ “ኔሩዳ ተገድሏል። ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ተናግሬያለሁ እስከ ዕለተ ሞቴም እናገራለሁ” ብሎ ነበር።