አቶ ኢሳያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ ተመረጡ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በትናንትናው እና በዛሬው እለት ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አቶ ኢሳያስ ጅራ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው በድጋሚ ተመረጡ።
ላለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸንን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ኢሳያስ ጅራ 94 ድምፅ በማግኘት እንደተመረጡ ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ሶስት እጩዎች ቀርበው የነበረ ሲሆን በእጩ ተወዳዳሪነት የቀረቡት አቶ መላኩ ፈንታ 27 ድምፅ እንዲሁም አቶ ቶኪቻ ዓለማየሁ 17 ድምፅ አግኝተዋል።
ሦስቱ ለፕሬዚዳንትነት የቀረቡት ዕጩዎች ሁለት ክልልን እና አንድ የከተማ አስተደደርን ወክለው ነው የተወዳደሩት።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዳኛቸው ነገሮን (ዶ/ር) የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል።
በዛሬው ምርጫ በተጨማሪም ስድስት ወንዶችና ሶስት ሴቶች፣ ዘጠኝ የስራ አስፈጻሚዎች የተመረጡ ሲሆን እነዚህም አዲሱ ቃሚሱ፣ ዳኛቸው ነገሮ፣ ሸረፋ ደለቾ፣ ሙራዶ አብዶ፣ አሰር አብርሃም፣ ሃቢባ ሲራጅ፣ ፋይዛ ረሻድ፣ብዙአየሁ ጀንበሩ ናቸው።
ፌዴሬሽኑን በቀጣይነት የሚመሩት ፕሬዝዳንት ስፖርቱን ማሳደግ፣ ማዘመን እንዲሁም ብሔራዊ ቡድኑ ደረጃውን የጠበቀ መጫወቻ ሜዳ እንዲኖረው ማድረግ ከሚጠበቁበት ዐበይት ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ።
ይህ ጠቅላላ ጉባኤ መጀመሪያ ጎንደር ከተማ እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደርጓል።
አቶ ኢሳያስ ጅራ ላለፉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንት የመሩ ሲሆን፣ ለቀጣይ አራት ዓመታት እንዲመሩ በድጋሜ ተመርጠዋል።
ከፌደሬሽኑ ውጪ የሴካፋ፣ የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ውድድር ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
አቶ ኢሳያስ የኦሮሚያ ክልልን ወክለው ነው የተወዳደሩት።
ከአራት ዓመት በፊት በ2010 ዓ.ም፣ የጂማ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ሥራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ ባለበት ወቅት ነው ተወዳድረው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት የሆኑት።
ከ20 ዓመታት በላይ በስፖርት አመራርነት የቆዩት አቶ ኢሳያስ፣ በጂማ እና በሰበታ እግር ኳስ ቡድኖች በአመራርነት ሠርተዋል።
ባለፉት ዓመታት “ደረት የሚያስነፋም ባይሆን አንገት የማያስደፋ ሥራ” መስራታቸውን ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት ተናግረው ነበር።
“ተጨባጭና በአይን የሚታይ ሥራ ሰርተናል” የሚሉት አቶ ኢሳያስ ዳግም ቢመረጡ የጀመሯቸውን መልካም ነገሮች ማስቀጠል፣ ሊሰሯቸው አቅደው በተለያየ ምክንያት ያልተሳኩትን ደግሞ ማከናወን እቅዳቸው ነው።
ከእቅዳቸው መካከል ዐቢይ የሆነው “የክለቦች አደረጃጀት ላይ መሥራት” መሆኑን ተናግረዋል።












