የኳታር የዓለም ዋንጫ፡ ኃያላኑን ቤልጂየም እና ጀርመን በጊዜ ተሰናበቱ

የጀርመን ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ቤልጂየም እና ጀርመን በጊዜ ሲሰናበቱ ብዙ ያልተጠበቁት ሞሮኮና ጃፓን ደግሞ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈለዋል።

ትላንት ምሽት የምድብ አምስት እና ስድስት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። 

በምድብ አምስት የምትገኘው ጃፓን ትላንት አወዛጋቢ በሆነ መንገድ ጎል በማስቆጠር ስፔንን አሸንፋ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች። 

አልቫሮ ሞራታ በ11ኛው ደቂቃ ስፔንን ቀዳሚ ማድርግ ቻለ።

ስፔኖች በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የበላይነት ተጠቅመው ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር አልቻሉም። 

በሁለተኛው አጋማሽ በሦስት ደቂቃ ልዩነት ዶአን እና አኦ ታናካ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ጃፓን አሸናፊ ለመሆን ችላለች። 

ታናካ ሁለተኛውን ጎል ከማስቆጠሩ በፊት ኳሱ ከሜዳ የወጣ ቢመስልም በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቫር) ኳሱ መስመሩን አለማለፉን በማሳወቁ ጎሉ ጸድቋል። 

በዚህም ጨዋታው 2 ለ1 ተጠናቋል። 

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ምድብ የሚገኙት ጀርምን እና ኮስታ ሪካ ያደረጉት ጨዋታም መልከ ብዙ ነበር። 

አራቱም ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋ የነበራቸው ሲሆን በጨዋታዎቹ ወቅት አራቱም ቡድኖች የማለፍ ዕድል የፈጠሩበት ጊዜም ተፈጥሯል። 

ጀርመን በቀድሞ አርሰናል ተጫዋች ግናብሪ አማካይነት ቀዳሚ መሆን ቻለች። 

በዚህ ወቅት ስፔን ጃፓንን 1 ለ 0 እየመራች ስለነበር ጀርመን እና ስፔን ተያይዘው ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያወልፉ መስሎ ነበር። 

በሁለተኛው አጋማሽ ኮስታ ሪካ በተከታታይ ባስቆጠረቻቸው ጎሎች ቀዳሚ መሆን ቻለች።

በዚህ ወቅት ስፔንም 2 ለ1 በመመራቷ ከምድቡ ኮስታሪካ እና ጃፓን ተያይዘው ሊያልፉ መስሎ ነበር። 

ጀርመን የኋላ ኋላ በሃቨርትዝ ሁለት ጎሎች እና በፉልክግ ተጨማሪ ጎል ጨዋታውን 4 ለ 2 ማሸነፍ ቻለች። 

ከዚህ ሁሉ ድራማ በኋላ ጃፓን ምድቡን በስድስት ነጥብ አንደኛ ሆና አጠናቃለች። 

ስፔን እና ጀርመን አራት አራት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል። 

ምስጋና ኮስታ ሪካ ላይ ላዘነበችው የጎል ናዳ ይሁንና ስፔን ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች። 

ጀርመን እና ኮስታሪካ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ። 

የምድብ ስድስት የመጨረሻ ጨዋታዎችም ትላንት ምሽት ተከናውነዋል። 

በዚህም ሞሮኮ ካናዳን በማሸነፍ ምድቡን በበላይነት ማጠናቀቅ ችላለች። 

የአትላስ አንበሶቹ በሃኪም ዛይች አማካይነት በአራተኛው ደቂቃ ቀዳሚ ለመሆን ቻሉ። 

ዩሴፍ ኤን-ነስሪ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የሞሮኮን ድል ይበልጥ አስተማማኝ አደረገው። 

የሞሮኮው ናይፍ አጉርድ በራሱ ላይ በማስቆጠሩ ካናዳ የማስተዛዘኛ ጎል ለማግኘት በቃች። 

ይህቺ ጎል የኳታሩ ዓለም ዋንጫ 100ኛ ጎል ሆና ተመዝግባለች። 

ጨዋታውም በሞሮኮ 2 ለ 1 የበላይነት ተጠናቋል።

ሉካኩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሮሜሉ ሉካኩ ተቀይሮ ገብቶ በተደጋጋሚ ያገኛቸውን ዕድሎች ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። 

በሌላ የምድቡ ጨዋታ ክሮሽያ እና ቤልጂየም ያለምንም ጎል አቻ ተለያይተዋል። 

ጨዋታው በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ በወጣችው ክሮሽያ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ባጠናቀቀችው ቤልጂየም መካከል ነበር። 

ቤልጂየም ማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ቢያሳልፋትም ውጤታማ መሆን ሳትችል ቀርታለች።

ከጉዳት የተመለሰው ሮሜሉ ሉካኩ ተቀይሮ ገብቶ በተደጋጋሚ ያገኛቸውን ዕድሎች ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። 

በመጨረሻም ክሮሽያ ለቀጣዩ ዙር የሚያስፈልጋትን አንድ ነጥብ አሳክታለች። 

በቅርቡ እንኳን የፊፋን የሃገራት ሰንጠረዥ ስትመራ የነበረችው አሁን ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው ቤልጂየም ‘ከወርቃማ ትውልዷ’ ተስፋን እንጂ ውጤት ማሳካት ሳትችል ቀርታለች።

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ ከጨዋታው በኋላ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተናግረዋል። 

ስፔናዊው አሰልጣኝ በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ አንድ ጎል ብቻ ያስቆጠረው ቡድናቸውን የተረከቡት በ2016 ነበር። 

“የመጨረሻ ጨዋታዬ ስለነበር ስሜታዊ ያደርጋል። ይህ ውሳኔ ከዓለም ዋንጫው በፊት የተወሰነ ነው” ብለዋል ማርቲኔዝ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ። 

ውጤቶቹን ተከትሎ ሞሮኮ በሰባት ነጥብ ምድቡን እየመራች ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች። 

ክሮሽያ በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። 

ቤልጂም እና ካናዳ ጥሎ ማለፉን ሳይቀላቀሉ መቅረታቸውን አረጋግጠዋል። 

ሰኞ ጃፓን እና ክሮሽያ በጥሎ ማለፉ ይገናኛሉ። 

ሞሮኮ ስፔንን ሰኞ ዕለት ትገጥማለች። 

የዓለም ዋንጫው የመጨረሻዎቹ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ። 

ዛሬ ምሽት 12፡00 ሰዓት ደቡብ ኮሪያ ከፖርቹጋል እና ጋና ከኡራጓይ ይጫወታሉ። 

ፖርቹጋል ከዚህ ምድብ ማለፏን አረጋግጣለች። 

ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ጋና ማሸነፍ ከቻለች ጥሎ ማለፉን ትቀላቀላለች። ደቡብ ኮሪያ እና ኡራጓይም ከምድቡ የማለፍ እድል አላቸው። 

ምሽት አራት ሰዓት ደግሞ ሰርቢያ ከስዊዘርላንድ እና ካሜሮን ከብራዚል የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ። 

ብራዚል ከዚህ ምድብ ማለፏን ቀድማ አረጋግጣለች። 

ሦስት ነጥብ ያላት ስዊዘርላንድን ጨምሮ ካሜሮን እና ሰርቢያም የማለፍ ተስፋ አላቸው።